ፈልግ

የቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ ምስ የቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ ምስ  (© Biblioteca Apostolica Vaticana)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ ታላቅ መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ጥበብን አስታወሱ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ካኅን፣ የነገረ መለኮት እና የፍልስፍና ሊቅ የነበረው የቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊኖ ቅድስና 700 ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ መልዕክት ልከዋል። ቅዱነታቸው ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን ሰባት መቶኛ የመታሰቢያ በዓል ምክንያት በማድረግ በጻፉት መልዕክት፥ ቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ ታላቅ መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ጥበብ የነበረው የቤተ ክርስቲያን ሰው እንደ ነበር አስታውሰው፣ በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮችን ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በበዓሉ እንዲገኙ ልዩ መልዕክተኛ አድርገው መርጠዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ ካኅን፣ ታላቅ መንፈሳዊ እና ሰብዓዊ ጥበብን በጸሎት እና በጽሑፍ ማጋራት የቻለ የቤተ ክርስቲያን ሰው እንደ ነበር አስታውሰዋል። የቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ ታላቅነትን ሐምሌ 4/2015 ዓ. ም. በላቲን ቋንቋ በጻፉት መልዕክት ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በዚህ መልዕክታቸውም በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮች ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ፥ በመካከለኛው ጣሊያን ፎሳኖቫ ከተማ በሚገኝ ገዳም ውስጥ ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. በሚከበረው ሰባት መቶኛ የቅድስና ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ እንዲገኙ መርጠዋቸዋል።

“ቅዱስ ቶማስ ዳኩዊናስ በጥበቡ ሳይኮራ ነገር ግን ዘወትር እራሱን ለበጎ ሥራ ያውል ነበር" ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የቅዱስ ዶሜኒኮስ ገዳም አባል የነበረ መነኩሴ ቅዱስ ቶማስ ዳኩዊናስ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች ዶ/ር አንጀሊከስ ብለው እንደሚጠሩት አስታውሰው፥ ቅዱስ ቶማስ ዳኩዊናስ በአስደናቂ ባህል የተሞላ ሰው ነበር” በማለት ሰኔ 23/2015 ዓ. ም. በጻፉት እና በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ በተፈረመው መልዕክት ላይ ገልጸዋል። “ቅዱስ ቶማስ ዳኩዊናስ በፍልስፍና እና በነገረ-መለኮት ትምህርቶች ከፍተኛ ዕውቀቶችን በመቅሰም በሚያስደንቅ እውቀት የተሞሉ ብዙ ሥራዎችን በመጻፍ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች አስተምሯል” ብለው፥ መለኮታዊ ምስጢራትን ማስተዋል እና አክብሮት በተሞላባቸው ግልጽ ምክንያቶች በመታገዝ በእምነት ሲመረምር ነበር” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው ሰኔ 21/2015 ዓ. ም. ለላቲና፣ ለሶራ እና ለፍሮሲኖኔ ብፁዓን  ጳጳሳት በላኩት መልዕክት ላይ እንደገለጹት፥ ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. ከሚከበረው ሰባት መቶኛ የቅድስና ዓመት መታሰቢያ በዓል በተጨማሪ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2024 ዓ. ም. የሞተበት 750 ኛ ዓመት እና እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2025 ዓ. ም. የተወለደበት ስምንት መቶኛ ዓመት እንደሚከበር አስታውሰዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም፥ ለቅድስና እና ለቤተ ክርስቲያን ዶክተርነት ያበቁ የቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስ አስተምህሮ ቤተ ክርስቲያን አሰባስባ ለማክበር የወጠነቻቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች በታላቅ አክብሮት እና የመንፈስ ደስታ ተቀብለናል" ብለዋል።

የበዓሉ አከባበር

በመካከለኛው ጣሊያን ፎሳኖቫ ከተማ በሚገኝ ገዳም ውስጥ ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን የመታሰቢያ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚመሩት በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮችን ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ እንደሚሆኑ ታውቋል። ፎሳኖቫ ቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ ያረፈበት እና አጽሙ የሚገኝበት ሥፍራ እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ላይ የሚሳተፉት በሙሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለቅዱስ ወንጌሉ ያላቸውን ልዩ ፍቅር በአዲስ ኃይል እና በአዲስ ቅንዓት በጸሎት እንዲገልጹ፣ እንዲሁም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው በእምነት ቅንዓት እንዲጸኑ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ቅዱስ ቶማስ ዘአኩዊናስን የሚያስታውሱ ሌሎች ዝግጅቶች

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት ሰኔ ተጽፎ ሰኔ 21/2015 ዓ. ም. በተሰራጨበት ዕለት መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ብጹዕ አቡነ ክሮቻታ፣ ብጹዕ አቡነ አንቶናዞ እና ብጹዕ አቡነ ስፕሪያፊኮ የመታሰቢያ መስዋዕተ ቅዳሴው የሚቀርበው የማኅበራቸው ባልደረባ የሆነው ቅዱስ ዶሚኒኮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

ይህን ምክንያት በማድረግ በካከለኛው ጣሊያን ላቲና ከተማ ማክሰኞ ሐምሌ 4/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ የአስተንትኖ ጸሎት ሥነ ሥር ዓት የተካሄደ ሲሆን፥ ዓርብ ሐምሌ 7/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በፎሳኖቫ ገዳም የጸሎት ሥነ ሥር ዓት እንደሚኖር እና ሐምሌ 11/2015 ዓ. ም. በቅድስት መንበር የቅድስና ጉዳዮችን ጳጳሳዊ ምክር ቤት አስተባባሪ የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ማርቼሎ ሰመራሮ በሚመሩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት መታሰቢያ በዓሉ እንደሚጠናቀቅ ታውቋል። 

12 July 2023, 16:57