ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከወጣቶች ጋር በቫቲካን ውስጥ  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከወጣቶች ጋር በቫቲካን ውስጥ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወጣቶች መጪውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በትኩረት እንዲያከብሩት አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአርጄንቲና ኮርዶባ ሀገረ ስብከት የመጡ ወጣት ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ለወጣቶቹ ባደረጉት ንግግር፥ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን የሚከረበውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ወጣቶቹ በትኩረት እንዲያከብሩ አሳስበው፥ በበዓሉ ወቅት ማንንም ወደ ጎን ሳይሉ መገናኘት እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"እንደ ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጥነት በመነሳት ቤተሰቦቻቸውን እና ምቾቶቻቸውን በመተው ከተለያዩ የዓለማች ክፍሎች ከመጡት ወጣቶች ጋር ለመገናኘት መምጣታቸውን በማስታወስ፥ ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት ከአርጄንቲና ኮርዶባ ሀገረ ስብከት ለመጡት ወጣት ተወካዮች ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል።

"ሁላችንም አሸናፊዎች ነን"

ፌስቲቫሉን አሸናፊ ወይም ተሸናፊ ከሌለበት እና ልዩ ከሆነው የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ ጋር ያወዳደሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “ከራሳችን ወጥተን ከሌሎች ጋር ስንገናኝ፣ ያለንን ለሌሎች ስናጋራ እና ሌሎች የሚያቀርቡልን ለመቀበል ዝግጁ ስንሆን ሁላችንም አሸናፊዎች በመሆን ‘የወንድማማችነትን ጽዋ’ አንድ ላይ ማንሳት እንችላለን” በማለት ገልጸዋል።

ቡድን መፍጠር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወጣቶቹ ኢየሱስን ክርስቶስን እስከ መጨረሻው ድረስ የተከተሉትን የብዙ ክርስቲያኖች ፈለግ እንዲመለከቱ አሳስበው፥ “ይህ የሚያስተምረን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ጋር መሆንን እና እስከ መጨረሻው ደቂቃ ድረስ ንቁ ሆኖ በኅብረት መጓዝን ነው” ብለዋል።

ሁላችንም አንድ ነን

ወጣቶቹ መጪውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫልን በትኩረት እንዲያከብሩት አሳስበው፥ በዓሉ የተለያዩ ፊቶችን፣ ባሕሎችን እና ተሞክሮዎች በተለያዩ የእምነት መገለጫዎች የሚበለጽጉበት አጋጣሚ እንደሆነ አስረድተዋል።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም፥ “ከሁሉም በላይ ዓለም እኛ አንድ መሆናችንን እንዲያምን የኢየሱስ ክርስቶስን ምኞት መለማመድ ትችላላችሁ” ብለው፥ “የሕይወትን ትርጉም ላላገኙ ወይም መንገዳቸውን ለሳቱት ሌሎች በርካታ ወጣቶች የወንጌልን ደስታ መመስከር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን እና የዓለም ዋንጫ

ከአርጄንቲና ኮርዶባ ሀገረ ስብከት ከመጡት ወጣቶች አንዱ የሆነው ወጣት ማርቲን አሎንዞ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመገናኘቱ የተሰማውን ስሜት ሲገልጽ፥ “ሁላችንም ፈርተን ቢሆንም ቅዱስነታቸው ቤተኛነት እንዲሰማን አድርገውናል” ብሎ፥ ለአንድ ደቂቃ እንኳ ቢሆን ከእያንዳንዱ የቡድኑ አባል ጋር ለመነጋገር መፈለጋቸውን ገልጿል።

ወጣት ማርቲን በማከልም ቅዱስነታቸው የትውልድ አገራቸው ከሆነች አርጄንቲና መምጣታችንን በመገንዘብ፥ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል እና የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታን በማወዳደር መናገራቸውን ገልጾ፥ እንደ አርጄንቲናዊ ባለፈው ታህሳስ ወር በኳታር በተካሄደውን የዓለም የእግር ኳስ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድናቸው ማሸነፉን አስታውሷል። ትዝታው አሁንም በአእምሮአችን ውስጥ አዲስ ስሜት ፈጥሮ ይገኛል” ያለው ማርቲን፥ “እግር ኳስ በአርጄንቲና ውስጥ ከስፖርትነት በላይ በመሆኑ ቅዱስነታቸው ሁለቱን ዓለም አቀፍ በዓላት በንፅፅር ማቅረባቸው ፍትሃዊ ይመስለኛል” ብሏል።

"እምነት በሁሉም ቦታ አለ"

ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን ውስጥ በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ የማይገኙ ወጣቶችም የዝግጅቱ አካል ሊሆኑ እንደሚችሉ በመናገር ቃለ ምልልሱን የደመደመው ወጣት ማርቲን፥ እምነትን በተግባር ለመኖር ብዙ መንገዶች እንዳሉ ተናግሮ፥ እምነትን በሁሉም ሥፍራ እና አንዳንድ ጊዜ በዘፈቀደ ቦታ ላይ እንደሚገኝ አስረድቷል።

17 July 2023, 15:20