ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ምዕመናን ቅዱስ ቁርባንን የሕይወታቸው ማዕከል ሊያደርጉት ይገባል!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ምዕመናን በየወሩ በጸሎት እንዲተባበሯቸው በማሳሰብ የሚያቀርቡትን ወርሃዊ የጸሎት ሃሳባቸውን ይፋ አድርገዋል። ለሐምሌ ወር ብለው ያቀረቡት የጸሎት ሃሳብ ቅዱስ ቁርባንን መሠረት ያደረገ ሲሆን በዚህም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ቅዱስ ቁርባንን የሕይወታቸው ማዕከል እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ አውታረ-መረብ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤተ በኩል ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክታቸው "ከመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት በኋላ ያለን ሕይወት አስቀድሞ ከነበረን ጋር ተመሳሳይ ከሆነ ችግር መኖሩን ያስረዳል" ብለው “ቅዱስ ቁርባን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኝበት እና በእጅጉ የሚለውጠን በመሆኑ የቅዱስ ቁርባን ሥርዓትን እንደ አስገዳጅ ሥርዓት ሳይሆን ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ለመገናኘት የተጋበዝንበት ሥርዓት ነው” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመቀጠልም “ራሱን ለእኛ የሚያቀርበው፣ ስለ እኛ ሲል ራሱን አሳልፎ የሰጠው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታችን እርሱን እንዲመገብ፣ የወንድሞቻችን እና የእህቶቻችን ሕይወትም እርሱን እንዲመገብ ወደ እራሱ ይመራናል” ብለዋል።

“የዚህ ወር የቪዲዮ መልዕክት ሦስት ዋና ተዋናዮችን ያሳየናል” ያለው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ፥ ሦስቱ ምዕመናን በመስዋዕተ ቅዳሴው ጸሎት ወቅት የተቀበሉትን ቅዱስ ቁርባን ከቤተ ክርስቲያን ውጭ በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ወደሚገኙ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው እንደሚያመጡ እና ይህም ከቅዱስ ቁርባን የተቀበሉትን የፍቅር ስጦታ ለሌሎች መልሰው እንደሚሰጡ ያመለክታል” ብሏል። የሰዎችን ዕለታዊ ሕይወት የሚገልጽ የሐምሌ ወር የቪዲዮ ቅንብሩ በሰሜን አሜሪካ ዴትሮይት ሀገረ ስብከት መዘጋጀቱን የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤቱ ሀገረ ስብከቱ ላደረገው ትብብር ምስጋናውን አቅርቧል።

የሐምሌ ወር የጸሎት ሃሳብ፥ ቅዱስ ቁርባንን የሕይወት ማዕከል ማድረግ
የሐምሌ ወር የጸሎት ሃሳብ፥ ቅዱስ ቁርባንን የሕይወት ማዕከል ማድረግ

ትብብሩ ድንገተኛ አልነበረም ያሉት በሰሜን አሜሪካ የዴትሮይት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አሌን ሄንሪ ቪኜሮን፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስን እና በቪዲዮ ምስል አማካይነት የሚያስተላልፉትን የጸሎት ጥሪ ለመደገፍ ዕድል በማግኘታችን ምስጋናቸውንን እናቀርባለን ብለው፥ “በተለይም በቅዱስ ቁርባን ዙሪያ ይህን የቪዲዮ መልዕክት ለማዘጋጀት በመጥየቃችን ታላቅ ክብር ይሰማናል” ብለዋል። ሀገረ ስብከታቸውን ጨምሮ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ካቶሊካዊ ሀገረ ስብከቶች በቅዱስ ቁርባን ምስጢር ላይ በማትኮር፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ቁርባን ውስጥ እንደሚገኝ ያለንን እምነት ለማሳደግ በቁርጠኝነት የተሰማሩበት አስፈላጊ ጊዜ ነው” በማለት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አሌን ሄንሪ ቪኜሮን ገልጸዋል። ሊቀ ጳጳስ አቡነ አሌን በማከልም “ይህ ቪዲዮ በዓለም አቀፉዊት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለምንገኝ ሁላችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንድንገናኝ እና እርሱ በቅዱስ ቁርባን በኩል ላበረከተልን ውድ ስጦታ የምንመሰግንበት እንዲሆን እንጸልያለን” ብለዋል።

ከራሳችን ወጥተን ወደ ሌሎች ዘንድ መሄድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሐምሌ ወር ባቀረቡት የጸሎት ሃሳብ ስለ ቅዱስ ቁርባን ሲያስረዱ፥ “ቅዱስ ቁርባን እኛ ከራሳችን ወጥተን ሌሎችን በፍቅር እንድናገኛቸው ድፍረት የሚሰጠን ስጦታ ነው” ብለዋል። ይህንንም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ ወር 2021 ዓ. ም. ባቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ ሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ሕዝቡን አጥግቦ የመገበው ዳቦን በማከፋፈል ሳይሆን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በፋሲካ እራት ላይ ራሱን ቆሮሶ በሰጣቸው ዳቦ በኩል እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባቀረቡት ስብከት “የሕይወታችን ዓላማ ራስን ለሌሎች በመስጠት ላይ እንደሆነ እና ከሁሉ በላይ ሌሎችን ማገልገል እንደሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ አሳይቶናል” ብለዋል። “ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት፥ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በቅዱስ ቁርባን በኩል መገናኘት እንድንችል ሊያበረታቱን፣ ሌሎችን ለመውደድ እና ራሳችንን በእርሱ እንድንለውጥ የሚያስችል አቅምን የምንቀበልበት ምስጢር ነው” በማለት የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

ቅዱስ ቁርባን የሕይወታችን ማዕከል

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ፣ አባ ፍሬደሪክ ፎርኖስ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሐምሌ ወር የጸሎት ሃሳብን መሠረት በማድረግ በሰጡት አስተያየት፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የት ማተኮር እንዳለብን እና በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊው ምን እንደሆነ ያስታውሱናል” ብለዋል። አባ ፍሬደሪክ አክለውም “ቅዱስ ቁርባን ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የምንገናኝበት እንደሆነ ቅዱስነታቸው ይነግሩናል” ብለው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ሊለውጠን፣ ሌሎችን የመውደድ ችሎታውን ሊሰጠን ስለሚፈልግ በዚህም ኃይልን በማግኘት ራሳችንን በተልዕኮው አገልግሎት ላይ ማድረግ እንችላለን” ብለዋል።

ለመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ክብርን መስጠት እና የካህንን ስብከት ከልብ ማድመጥ
ለመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ክብርን መስጠት እና የካህንን ስብከት ከልብ ማድመጥ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ቅርንጫፍ የሆነው የወጣቶች ቅዱስ ቁርባን እንቅስቃሴም በበኩሉ፥ ለመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ክብርን በመስጠት፣ የካህንን ስብከት ከልብ በማድመጥ ከሞት ከተነሳው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል እና የጋራ ግንኙነት መፍጠር እንደሚገባ ጋብዞናል። እንቅስቃሴው በማከልም፥ እራሳችንን በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሚገኘው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲለውጠን ስንፈቅድ፣ ሕይወታችንን እንደ እርሱ በመኖር ዓለምን ያዳነበት የርህራሄ ተልዕኮ መካፈል እንደምንችል ገልጾ፥ ወደዚህ የሕይወት ለውጥ ልምምድ በመቅረብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በጸሎት  እንድንተባበር፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ጥሪ አውታረ-መረብ አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ቅርንጫፍ የሆነው የወጣቶች ቅዱስ ቁርባን እንቅስቃሴም አሳስቧል።

ከቅዱስ ቁርባን የተቀበሉትን የፍቅር ስጦታ ለሌሎች ማካፈል
ከቅዱስ ቁርባን የተቀበሉትን የፍቅር ስጦታ ለሌሎች ማካፈል
04 July 2023, 16:59