ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጋናውን ፕሬዝዳንት አቶ አኩፎ-አዶን በቫቲካን ተቀብለው አነጋገሩ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጋና ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት አቶ ናና አዶ አኩፎ አዶ ጋር ቅዳሜ ሐምሌ 15/2015 ዓ. ም. ቫቲካን ውስጥ በጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ መገናኘታቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል አስታውቋል። ፕሬዝዳንት ናና አዶ አኩፎ አዶ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ከተገናኙ በኋላ ከቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እና በቅድስት መንበር የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ከሆኑት ሊቀ ጳጳስ አብነ ፖል ሪቻርድ ጋላገርን ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን መግለጫ ክፍሉ አስታውቋል። ንግግራቸውም በቅድስት መንበር እና በጋና መንግሥት መካከል ባለው መልካም ግንኙነት ላይ ያተኮረ እንደነበር ተገልጿል።
ውይይታቸው በዋናነት በጋና ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት መካከል ያለውን ትብብር ለማሳደግ ያተኮረ ሲሆን፥ በተለይም በትምህርት እና በጤና አጠባበቅ መስክ ላይ ከመነጋገራቸው በተጨማሪ በጋና ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይም መወያየታቸው ተነግሯል። ከሰላም ጋር በተያያዙ ጉዳዮችም ችግሮችን በዓለም አቀፍ ደረጃ መፍታት እና በምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የፀጥታ ሁኔታን ለማሻሻል ትኩረት መስጠት እንደሚገባ እና ሌሎች ወቅታዊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮችም ተዳሰዋል።