ፈልግ

የረሃብ ቀውስ ለማስወገድ የምግብ ምርት መጨመር "FAO" የረሃብ ቀውስ ለማስወገድ የምግብ ምርት መጨመር "FAO"   (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዓለማችን ረሃብን ለማጥፋት ቆራጥ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት በላኩት መልዕክት በዓለማችን ውስጥ ረሃብ መስፋፋቱን ገልጸው እየደረሰ ያለውን ቀውስ ለማስወገድ ቆራጥ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ ድርጅቱ ባዘጋጀው 43ኛ ጉባኤ ላይ ለተገኙት አባላት አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን በመቅረፍ ሰብዓዊ ክብርን ለሰው ልጅ በሙሉ ለመስጠት ሁሉም ሀገራት የተቀናጀ ጥረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ አሳስበውዋል። የቅዱስነታቸውን መልዕክት ለጉባኤው በንባብ ያሰሙት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ ቺካ አሬላኖ ናቸው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በጦርነቶች እና ግጭቶች እንዲሁም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዙ የተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በድህነት እና በምግብ እጦት እየተሰቃዩ እንደሚገኙ ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ገልጸው፥ በዚህ ምክንያት “በዓለማችን ውስጥ እየቀነሰ ከመሄድ ይልቅ እየተስፋፋ ያለውን የረሃብ አደጋ ለማጥፋት ቆራጥ እና ብቁ እርምጃ መውሰድ ይገባል” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ማሳሰብባቸውን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ብጹዕ አቡነ ቺካ አሬላኖ ለመንግሥታቱ የምግብ እና የእርሻ ድርጅት 43ኛ ጉባኤ ተሳታፊዎች በንባብ አሰምተዋል። 

ረሃብ የሰውን ክብር የሚነካ ከባድ ጥቃት ነው

“ድህነት፣ እንደ ምግብ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የጤና እንክብካቤ፣ ትምህርት፣ መኖሪያ ቤት ያሉ የአንደኛ ደረጃ ግብዓቶች አቅርቦት እጦት እና አለመመጣጠን የሰውን ልጅ ክብር በእጅጉ የሚነካ ነው” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በድጋሚ ተናግረው፥ “ይህም በምድራችን ውስጥ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚ እና ወታደራዊ ውጥረቶች ከሚያስከትሉት የጅምላ መፈናቀል ጋር ተዳምሮ የሰዎችን ክብር እና የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ያዳክማል” ብለዋል።

ርዕዮተ ዓለማዊ ቅኝ አገዛዝ መዋጋት

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ እስከ 2030 ድረስ ረሃብን ከዓለም ገጽ በማጥፋት ለሁሉም የሰው ልጅ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ቢነሳም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ዕቅዱ እንደማይሳካ ባለሙያዎች ገልጸዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኃላፊነቱን በተቀመጠለት ጊዜ መወጣት አለመቻሉ የመነሻ ዓላማዎችን በመቀየር የማኅበረሰቦችን ትክክለኛ ፍላጎት ወደማያሟሉ አዳዲስ ፕሮግራሞች ሊያመራ እንደማይገባ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ላይ ገልጸው፥ የባሕል ብዝሃነትን እና ልዩነትን የሚቀይር እንዲሁም በዕድገት ስም የሚዘረጋ “የርዕዮተ ዓለም ቅኝ አገዛዝ” ሥርዓት መወገድ አለበት ብለዋል።

የቅድስት መንበር ቁርጠኝነት ማንም ሰው የዕለት እንጀራ እንዳይጎድል ነው

“ስለዚህ የመላው ሰብዓዊ ቤተሰብ የጋራ ትብብር የግድ አስፈላጊ በመሆኑ፣ አሁን የሚታዩት ግዙፍ ተግዳሮቶች ሁሉን አቀፍ እና ሁለገብ አካሄድን የሚጠይቁ  በመሆናቸው ለግጭትም ሆነ ለተቃውሞ ቦታ ሊኖር አይገባም” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር አያይዘው መንግሥታት፣ የንግድ እና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ እና ግለሰቦች ጋር በመሆን የጋራ ጥረት እንዲያደርጉ በመጠየቅ፥ ሁሉንም በተለይም ድሃውን ወገን የሚጠቅሙ ቀስቃሽ እርምጃዎችን ማስተባበር እንደሚገባ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፥ በዓለማችን ላይ ማንም ሰው የዕለት እንጀራ እንዳይነፈግ እና ምድራችን የሚያስፈልጋትን ጥበቃ አግኝታ የሰው ልጅ ደስታን እንዲያገኝ ከፈጣሪው የተሰጠው ምድር ወደ ውብ የአትክልት ስፍራነት እንዲመለስ ለማድረግ ቅድስት መንበር የበኩሏን አስተዋጽኦ አጠናክራ እንደምትቀጥል ገልጸዋል።

 

04 July 2023, 17:06