ፈልግ

አዲስ የተመረጡ ካርዲናሎች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሲያቀርቡ አዲስ የተመረጡ ካርዲናሎች የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት ሲያቀርቡ  (Vatican Media) ርዕሰ አንቀጽ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ይፋ ያደረጉት የአዳዲስ ካርዲናሎች ምርጫ አስገራሚ መሆኑ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ሐምሌ 2/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ካቀረቡት የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ባደረጉት ንግግር የካርዲናልነት ማዕረግ የሚሰጣቸው የቤተ ክርስቲያን አባቶች መመረጣቸውን ይፋ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በመጭው መስከረም 19/2016 ዓ. ም. የአዳዲስ ካርዲናሎች ሹመት እንደሚፈጸም የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ በጥቅምት ወር ላይ ሊካሄድ ለታቀደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ትኩረት በመስጠት አዲስ የተመረጡት ካርዲናሎች በዓለም ዳርቻዎች ከምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መመረጣቸውን አስታውቀዋል።

ብዙዎች በእርግጠኝነት እንደጠበቁት የጎርጎሮሳውያኑ 2023 ዓ. ም. አዳዲስ ካርዲናሎችን በመምረጥ እንደሚጠናቀቅ ሲነገር፥ በአሥር የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት ውስጥ ቅዱነታቸው ዘጠኝ የካርዲናሎች ምርጫ ጉባኤዎችን ማካሄዳቸው ታውቋል። ነገር ግን በመጭው መስከረም ወር ላይ 21 ካርዲናሎች የመሰየማቸው ዜናን በሐምሌ ወር ውስጥ ማንም ያልጠበቀው መሆኑ ተገልጿል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው እሑድ ሐምሌ 2/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ካቀረቡት የመልዓከ እግዚአብሔር ጸሎት ቀጥለው ባደረጉት ንግግር፥ በመስከረም 19/2016 ዓ. ም. ከዓለም ዙሪያ ለተመረጡት ብፁዓን ጳጳሳት የካርዲናልነት ማዕረግ እንደሚሰጥ ማሳወቃቸው ይታወሳል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክትም፥ “በሮም ሀገረ ስብከት ውስጥ አዳዲስ ካርዲናሎች መካተታቸው በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር እና በዓለም ዙሪያ በምትገኛ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን የማይነጣጠል አንድነት መኖሩን ያረጋግጣል” ማለታቸው ይታወሳል።

የካርዲናሎቹ ሹመት የሚካሄደው ከሁለት የሲኖዶስ ጉባኤዎች መካከል የመጀመሪያው ጉባኤ በሚጀምርበት ዋዜማ ላይ እና ከአንድ ዓመት በፊት የተካሄደውን ስምንተኛ የካርዲናሎች ሹመት ሥነ-ሥርዓት ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል። አዲስ በሚሾሙ ካርዲናሎች መካከል 18ቱ ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በታች በመሆኑ ምክንያት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን መምረጥ እንደሚችሉ ታውቋል። የ21 አዳዲስ ካርዲናሎች ስም ዝርዝር ስንመለከት በቅድስት መንበር ሥር በሚገኙ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ማለትም በጳጳሳዊ ምክር ቤት የእምነት አስተምህሮ ጽሕፈት ቤትን፣ በቅድስት መንበር የብጹዓን ጳጳሳት ጽሕፈት ቤትን እና የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን እንዲመሩ በቅርቡ የተመደቡት ብፁዓን ጳጳሳት ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በታች መሆኑ በቅድስት መንበር ተረጋግጧል።

የቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ የሆኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እስከ ዛሬ ካደረጓቸው ምርጫዎች መካከል አስገራሚ የሚባሉት በሶርያ የቅድስት መንበር እንደራሴ በመሆን እየሠሩ የሚገኙት የብፁዕ ካርዲናል ማሪዮ ዘናሪ ሹመት እና በተመሳሳይ ሚና ሁለት መነኮሳት መመረጣቸው አስፈላጊ እና አዲስ ክስተት መሆኑ ተመልክቷል። በተለይ ለሰሜን አሜሪካ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዲስ ካርዲናልን በመምረጥ ረገድ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በመተባበር ትልቅ ሚና የተጫወቱት እና በመጫወት ላይ የሚገኙት የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ክሪስቶፍ ፒዬር ለካርዲናልነት ማዕረግ መመረጣቸው ትኩረትን መሳቡ ተመልክቷል።

የካርዲናልነት ማዕረግ የተቀበሉት የመጀመሪያው የቅድስት አገር ኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ አቡነ ፒዬርባቲስታ ፒዛባላ ሲሆኑ፣ በቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም ውስጥ የምትገኝ የላቲን ሥርዓት የምትከተል ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥላቻ፣ ግጭት እና አመጽ በሚነሳባት ቅድስት ከተማ ኢየሩሳሌም ውስጥ የምትገኝ ብትሆንም፥ ዛሬ በኩላዊት ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ በመሳተፍ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመተባበሯ ተጨማሪ ምስጋናን የሚያሰጥ እንደሆነ ተነግሯል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለፈው የካቲት ወር የጎበኟት የደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ እስጢፋኖስ ሙላ የካርዲናልነት ሹመት ለቀጣናው እና ለግንባር ቀደም አብያተ ክርስቲያናት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ሲሆን፣ በደቡብ አፍሪካ የኬፕ ታውን ሊቀ ጳጳስ እስጢፋኖስ ብሪስሊን እና በታንዛኒያ የታቦራ ከተማ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ፕሮታሴ ሩጋምብዋ፣ ሦስቱም የአፍሪካ ሜትሮፖሊታን ጉባኤዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ካርዲናሎችን ማግኘታቸው ታውቋል። ከዚህም በተጨማሪም አዲሱ የሆንግ ኮንግ ጳጳስ አቡነ እስጢፋኖስ ቻው ሳው-ያን እና የቅዱስ ዶን ቦስኮ ሳሌሺያን ማኅበር ጠቅላይ አለቃ ክቡር አባ አንገል ፌርናንዴዝ አርቲም አዲስ በተመረጡት ካርዲናሎች ውስጥ መካተታቸው ትኩረት መሳቡ ታውቋል።

ዕድሜያቸው ከ80 ዓመት በላይ ከሆናቸው መካከል የቀድሞው የስደተኞች እና የመንገደኞች ሐዋርያዊ እንክብካቤ ጳጳሳዊ ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ አጎስቲኖ ማርኬቶ እና በሁለተኛው ቫቲካን ጉባኤ የክርስቲያኖች አንድነት ምሁር፣ በአርጄንቲና ቦይኔስ አይሬስ የፖምፔይ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የንስሐ አባት አባ ሉዊስ ፓስካል ድሪ ሲሆኑ፥ እነዚህን ሁለቱ አባቶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ መሪነት ከመመረጣቸው አስቀድሞ በደንብ የሚያውቋቸው መሆኑ ታውቋል።

በመጭው መስከረም 19/2015 ዓ. ም. የካርዲናልነት ማዕረግ የሚቀበሉትን ጨምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን የሚመርጡ ካርዲናሎች ቁጥር ወደ 137 እንደሚያድግ ታውቋል። ይህ ቁጥርም በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ በተቀመጠው 120 በላይ ሲሆን፣ ነገር ግን ይህ ጣሪያ በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እና በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት በነዲክቶስ 16ኛ ወቅት በብዙ አጋጣሚዎች በልጦ ሲገኝ ተመልክቷል። ከመጭው መስከረም በኋላ በሚኖረው አሃዛዊ መረጃ መሠረት 15 የጣሊያን ካርዲናሎችን ጨምሮ አውሮፓ 53 መራጭ ካርዲናሎች እንደሚኖራት ታውቋል። ሰሜን አሜሪካ 11 እና ካናዳ 4 በድምሩ 15 መራጭ ካርዲናሎች እንደሚኖራቸው፣ ላቲን አሜሪካ 24 መራጭ ካርዲናሎች፣ አፍሪካ  19 መራጭ ካርዲናሎች፣ እስያ 23 መራጭ ካርዲናሎች እና ኦሼኒያ 3 መራጭ ካርዲናሎች እንደሚኖራቸው ታውቋል።

11 July 2023, 16:38