ፈልግ

በሆስፒታል የሚገኙት ሕጻናት ለቅዱስነታቸው የላኩትን የመልካም ምኞት መግለጫ ምሥል በሆስፒታል የሚገኙት ሕጻናት ለቅዱስነታቸው የላኩትን የመልካም ምኞት መግለጫ ምሥል  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጥሩ ሁኔታ በማገገም ላይ እንደሚገኙ ተነገረ

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. ጠዋት ላይ በሰጠው መግለጫ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ግንቦት 30/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ከተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና ወዲህ ላለፉት ቀናት በመልካም ሁኔታ ሆነው ዕረፍት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የመግለጫ ክፍሉ የዓርብ ዕለት ውሎአቸውን በማስመልከት ከሕክምና ባለሙያዎች ቡድን ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በሰጠው መግለጫ፥ የቅዱስነታቸው የድህረ-ቀዶ ጥገና ሕክምና ሂደት በመደበኛነት መቀጠሉን፣ የደም ግፊታቸው መጠን ቋሚ እንደሆነ እና በደም ሥር በኩል የሚሰጥ የመድኃኒት ዕርዳታን አቋርጠው ውሃ መውሰድ መጀመራቸውን ገልጿል።

መግለጫ ክፍሉ አክሎም፥ ቅዱስነታቸው ዓርብ ዕለት ከሰዓት በኋላ የነበረውን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መካፈላቸውን፣ ቀለል ያሉ ተግባራትን ሲያከናውኑ ውለው ማምሻውን በጸሎት ሥነ-ሥርዓት ቅዱስ ሥጋውን እና ደሙን መቁረባቸውን አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሰዓታት ውስጥ በሚደርሷቸው በርካታ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች ልባቸው መነካቱን መግለጫ ክፍሉ ገልጾ፥ በተለይም ሆስፒታል ውስጥ የሚገኙት ሕጻናት ለቅዱስነታቸው ያላቸውን ወዳጅነት ለመግለጽ የላኩትን የመልካም ምኞት መግለጫ ሥዕላዊ መልዕክቶችን ተቀብለው ምስጋና ማቅረባቸውን አስታውቋል።

ለእነዚህ ሕፃናት እንዲሁም ለሕክምና ባለሙያዎች፣ ለነርሶች እና እና በየቀኑ ሕመምን በእጃቸው እየነኩ ሸክሙን ለማስወገድ ጥረት በማድረግ ላይ ለሚገኙ እና የጸሎት ድጋፍን በማድረግ ላይ ለሚገኙት ምዕመናን ምስጋና ማቅረባቸውን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ገልጿል።

10 June 2023, 17:17