ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እውነተኛ ውበት ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት የሚያነሳሳ መሆኑን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም ዙሪያ የመጡ ታዋቂ የሥነ-ጥበብ ሰዎችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸውል። ዓርብ ሰኔ 16/2015 ዓ. ም. ቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ ለሥነ-ጥበብ ሰዎች ባደረጉት ንግግር፥ እውነተኛ ውበት እግዚአብሔርን ለማወቅ ያለንን ፍላጎት በማነሳሳት ክብር ለእርሱ እንድንሰጥ ያግዘናል ብለዋል። ቅዱስነታቸው ይህን የተናገሩት በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ የተመረቀው እና ዘመናዊ የጥበብ ሥራዎችን የያዘው የቫቲካን ሙዚዬም 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ እንደነበር ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"በእውነተኛ ውበት መካከል እግዚአብሔርን ማወቅ እንጀምራለን" በማለት ቫቲካን ውስጥ በሚገኝ የሲስቲን ጸሎት ቤት ዓርብ ሰኔ 16/2015 ዓ. ም. ለሥነ-ጥበብ ሰዎች ባደረጉት ንግግር፥ “የሥነ-ጥበብ ሰዎች ለዓለም በሚያቀርቡት መንፈሳዊ የስዕል ሥራዎቻቸው የእግዚአብሔር ሕልም ተካፋዮች" ናቸው በማለት ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ታዋቂ ለተባሉ የሥነ-ጥበብ ሰዎች ባደረጉት ንግግር የጥበብ ሥራቸው የሁሉ አባት ለሆነው እግዚአብሔር ክብርን የሚሰጥ፣ ለምስክርነትም የሚያበቃቸው እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ በመግለጽ በጸሎታቸው አስታውሰዋል። ታዋቂ የሥነ-ጥበብ ሰዎቹ ጥሪያቸውን ተቀብለው በቫቲካን በመገኘታቸው አመስግነው በመካከላቸው በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታንም ገልጸዋል። ቤተ ክርስቲያን ከሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች ጋር ለዘመናት የቆየውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት እና ወዳጅነት አስታውሰዋል።

ቅዱስ መንፈስ ወደ ፊት እንዲራመዱ ያግዛል

“የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የጉዞ አቅጣጫች ሁልጊዜም መንፈስ ቅዱስ መሆኑን ያስታውሱናል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ "የጥበብ ሥራችሁ በነፋስ ኃይል በመታገዝ ወደ ፊት እንደሚገፋ ጀልባ እና ቤተ ክርስቲያንም ከሥነ-ጥበብ ጋር ያላት ወዳጅነት ልማዳዊ እና ተፈጥሯዊ ነው" ብለዋል። “የአርቲስት ሁኔታ ከሕፃን፣ አልፎ ተርፎም ከባለራዕይ ሁኔታ የተለየ አይደለም” በማለት በአንድ ወቅት የሥነ-ጥበብ ሰው ሮማኖ ጓርዲኒ የተናገረውን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስታውሰው፥ “ለጓርዲኒ የጥበብ ሥራ የምንራመድበት፣ የምንተነፍስበት፣ የምንንቀሳቀስበት እና ከፊት ለፊታችን ሰዎች ሲመጡ የምንገናኝበትን ቦታ የሚከፍትልን” ነው በማለት አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፥ ሰዎች ከሥነ-ጥበብ ጋር ሲገናኙ ድንበሮች ክፍት እንደሚሆኑ እና የልምድ እና አንዱ ሌላውን የሚረዳበት ወሰን እየሰፋ እንደሚሄድ ተናግረዋል። ሁሉም ነገር የበለጠ ክፍት እና ተደራሽ በሚመስል ሁኔታ፥ አንድ ሕጻን በምናባዊነት ተሞልቶ እውነታን የሚገነዘብበት ባለ ራዕይ ውስጣዊ ስሜትን እንለማመዳለን” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ሲያደርጉ
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎችን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር ሲያደርጉ

እነሆ አዲስ ነገር እፈጥራለሁ!

"የሥነ-ጥበብ ባለሞያ እንደ ሕጻን ምንም ጥፋት የለበትም" ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ለመጀመሪያ የፈጠራ ውጤቱ እና ለአዲስነቱ ነፃነትን በመስጠት ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ አዲስ ነገር ወደ ዓለም ያመጣል” ብለው፥ በችሎታቸው ልዩ ነገርን በመሥራት ዓለምን በአዲስ ነገር የሚያበለጽጓት መሆኑን አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኢሳ. 43:19 ላይ እግዚአብሔርም፥ “እነሆ አዲስ ነገርን አደርጋለልሁ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፣ ይህን እናንተም አታውቁምን? በምድረ በዳም መንገድን፣ በበረሃም ወንዞችን እዘረጋለሁ” ማለቱን በመጥቀስ፣ "የሥነ-ጥበብ ባለሞያ የፈጠራ ሥራ እግዚአብሔር ለፍጥረቱ ያለውን ፍቅር ተካፋይ ነው ማለት ይቻላል” ብለው፥ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች የእግዚአብሔር ሕልም ተካፋዮች መሆናቸውንም አስረድተው፥ ማየት ብቻ ሳይሆን ማለም መቻል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች ከቅዱስነታቸው ጋር በተገናኙበት ወቅት
የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች ከቅዱስነታቸው ጋር በተገናኙበት ወቅት

የማለም ችሎታ

የሥነ-ጥበብ ሰው ጓርዲኒ ባለ ራዕይ እና የአርቲስቶች መገለጫ መሆኑን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አርቲስቶች ያላቸውን ነገሮችን በጥልቀትም ሆነ ከሩቅ የማየት ችሎታን በመጥቀስ፣ አርቲስቶች ዓይናቸውን እንደሚፈትኑ፣ አድማሱን እንደሚመለከቱ እና ጥልቅ እውነታዎችን እንደሚገነዘቡ ተናግረዋል። አርቲስቶች ይህን በማድረጋቸው በአሁኑ ወቅት በጣም ተወዳጅ የሆነውን ሰው ሠራሽ እና ዝቅተኛ ዋጋ ያለውን ማራኪነት ውድቅ ለማድረግ መጠራታቸውን እና በሰዎች መካከል የኑሮ አለመመጣጠንን የሚያስከትሉ የተሳሳቱ ኤኮኖሚያዊ ሥርዓቶችን ለመዋጋት መጠራታቸውን ተናግረዋል። የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች ከእንደዚህ ዓይነት ውበት ራሳቸውን በማራቅ የጥበብ ሥራዎቻቸው የኅብረተሰቡን ህሊና የሚተች እና እውነታዎችን በትክክል የሚገልጽ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት አርቲስቶችም እንዲሁ ከማይመች ሁኔታ ጋር የሚጋፈጡ፣ የውሸት ተረቶችን እና አዳዲስ ጣዖቶችን፣ ፍሬ የሌላቸው የሽንገላ ንግግሮችን የሚወቅሱ ናቸው” ብለዋል።

የሰው ልጅ ሰብዓዊ ልኬት

የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች እውነተኛ ሃይማኖታዊ ማንነት እንዲኖራቸው ጥሪ ያቀረቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች እንደ ባለራዕይ አስተዋይ ኅሊና ያላቸው፣ የሰውን ልጅ ሕይወት የሚያከብሩ፣ ለማኅበራዊ ፍትህ እና ለድሃው ማኅበረሰብ የሚቆረቆሩ፣ የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጉዳት የሚጠብቁ እና የሰብዓዊ ወንድማማችነት አጋር አድርጌ እቆጥራቸዋለሁ” ብለዋል።

ከአርቲስቶች መካከል እንዱ ለቅዱስነታቸው የሙዚቃ ትርኢት ሲያቀርብ
ከአርቲስቶች መካከል እንዱ ለቅዱስነታቸው የሙዚቃ ትርኢት ሲያቀርብ

“እግዚአብሔር ለሰው ልጅ በሙሉ እንደሚራራ ሁሉ ለሰው ልጅ ሰብዓዊነት ትልቅ ሥፍራን እሰጣለሁ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ኪነ ጥበብ ወደ እምነት እንደሚቀርብ ተናግረው፥ በሰው ልጆች መካከልም ሰላምን ለማምጣት እንደሚያግዝ አስረድተው፣ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች በጨለማ ውስጥ ብርሃን እንዲሆኑ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

እግዚአብሔርን የማወቅ ጉጉት

“በእውነተኛ ውበት በመታገዝ እግዚአብሔር ለማወቅ እንጓጓለን” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ብዙዎች ዛሬ ኪነ ጥበብን ወደ ውበት ለመለወጥ ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረው፥ ከንቱ፣ ሰው ሠራሽ እና አልፎ ተርፎም ታማኝነት የጎደለው የውበት ዓይነትም አለ” ብለው፣ “ልዩነቱን ለይቶ ለማወቅ አስፈላጊው መስፈርት ውበቶችን አንድ ላይ በማስማማት መመልከት ነው” ብለዋል። "እውነተኛ ውበት የስምምነት ነጸብራቅ እንደሆነ፣ መስማማት የውበት ተግባራዊ በጎነት፣ ጥልቅ መንፈሱም ዓለምን አንድ የሚያደርግ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው" ብለዋል።

የድሆችን የዝምታ ልመና ተርጓሚዎች እንዲሆኑ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም ዙሪያ ለመጡት ታዋቂ የሥነ-ጥበብ ሰዎች ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ፥ የሥነ-ጥበብ ባለሞዎች ድሆችን እንዳይረሱ፣ በተለይም ለኢየሱስ ክርስቶስ ልብ ቅርብ የሆኑትን፣ ዛሬ በብዙ ዓይነት ድህነት የተጎዱ ሰዎችን እንዳይረሱ አደራ ብለዋል። ድሆችም ኪነ-ጥበብ እና ውበት እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸው፥ “አንዳንድ ሰዎች በከባድ ችግር ውስጥ ሆነው ኪነ ጥበብን የበለጠ እንደሚፈልጉ እና ብዙውን ጊዜም ከኪነ ጥበብ ሌላ እራሳቸውን የሚሰሙበት ድምጽ የላቸውም” ብለዋል።

ለእግዚአብሔር ያላቸውን ክብርን በሥራቸው መግለጽ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሥነ-ጥበብ ባለሞዎችን አመስግነው፣ ያላቸንም አክብሮት አረጋግጠዋል። የጥበብ ሥራዎቻቸው ለዚህ ምድር ሰዎች በሙሉ የተገባ ሆኖ እንዲገኝ እና የሁሉ አባት አፍቃሪ የሆነውን እግዚአብሔር እንደሚያከብርሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸው፥ በጥበብ ሥራቸው የእግዚአብሔር ምስክሮች እንዲሆኑ በጸሎታቸው እንደሚያግዟቸው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአርቲስቶች ጋር ቆይታ ሲያደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከአርቲስቶች ጋር ቆይታ ሲያደርጉ

 

24 June 2023, 16:43