ፈልግ

ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ እና አቶ ማቴዮ ብሩኒ የጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ እና አቶ ማቴዮ ብሩኒ የጋራ መግለጫ በሰጡበት ወቅት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የእሑዱን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በግል እንደሚያቀርቡ ተገለጸ

የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ቅዳሜ ሰኔ 3/2015 ዓ. ም. እኩለ ቀን ላይ በሰጠው መግለጫ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየእሑዱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የሚያቀርቡትን የኅብረት ጸሎት ሆስፒታል ውስጥ ሆነ በግል እንደሚያቀርቡት አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ከሐኪሞቻቸው የቀረበላቸውን ምክር በመከተል በየእሁዱ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የሚያደርሱትን ሳምንታዊ የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከምዕመናኑ ጋር በመንፈስ በመተባበር በግል የሚያቀርቡት መሆኑን የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል።   

ይህ ምክርም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሐኪሞቻቸው የተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና መልካም ውጤት እንዲያስገኝ እና በሆድ ግድግዳ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ ተብሎ የቀረበ መሆኑን የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የቀዶ ጥገና ሐኪም ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ እና የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ በጋራ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ በመግለጫቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥሩ ሁኔታ በማገገም ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ የሕክምና ቡድኑ በተቻለ መጠን በሆድ ግድግዳ ላይ ጫናን ከሚፈጥር ማንኛውንም ዓይነት የአካል እንቅስቃሴ እንዲገደቡ ማድረጉን አስረድተዋል።

የቅዱስነታቸው የደም ዝውውር እና የራጅ ውጤቶች መልካም መሆናቸውን እና ምንም ዓይነት ከባድ የጤና ችግሮች እንደሌለባቸው ዶ/ር አልፊዬሪ አረጋግጠው፥ የፈውስ ሂደቱ በጥሩ ሁኔታ እንደሚቀጥል እና የአካል ጥንካሬያቸው ወደ ተለመደው ሐዋርያዊ ተግባር እንኪመልሳቸው ድረስ የሚቀጥለውን ሳምንት ሆስፒታል ውስጥ እንዲቆዩ መመከራቸውን አክለው ተናግረዋል።

10 June 2023, 17:22