ፈልግ

2023.05.31 udienza che il Papa ha avuto con il giudice Mohamed Abdelsalam il 29 maggio

የዓለም ሃይማኖቶች በአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ እሴቶችን እና እውቀቶችን እንደሚለዋወጡ ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊን እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ልዩ ተወካይን በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል። ቅዱስነታቸው ከእንግዶቹ ጋር በቫቲካን ተገናኝተው በተነጋገሩበት ወቅት፣ የአየር ንብረት ለውጥ በማስመልከት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመጪው ህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12/2023 ዓ. ም. በዱባይ በሚካሄደው 28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ የእምነት ማኅበረሰቦችም ተገኝተው ወሳኝ አስተዋጽዖ በሚያደርጉበት መንገድ ላይ ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዳኛ መሐመድ አብደል ሰላም፣ ከሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ እና ከአምባሳደር ማጂድ አል-ሱዋይዲ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ልዩ ተወካይ እና የ28ኛው ዙር የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ተወካይ ጋር፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ዝግጅት ላይ የእምነት ቡድኖችን ማሳተፍ በተመለከተ ተወያይተዋል።

ቅዱስነታቸው እንግዶቹን ግንቦት 21/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው ማነጋገራቸውን ያስታወቀው መግለጫው፣ በውይይታቸው ወቅትም የ28ኛው ዙር የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ  ግቦችን ለማሳካት የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችን እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን በማሳተፍ የጋራ ተነሳሽነት ለመጀመር በሚያግዙ ሃሳቦች ላይ መወያየታቸውን ገልጿል። ጉባኤው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከመጪው ህዳር 30 እስከ ታህሳስ 12/2023 ዓ. ም. በዱባይ እንደሚካሄድ እና ትኩረቱም “ዓለም አቀፍ የምግብ ሥርዓቶችን መጠበቅ” በሚል ርዕሥ ላይ እንደሚሆን መግለጫው አክሎ አስታውቋል።

የጋራ ተነሳሽነት

የሐይማኖቶች የጋራ ተነሳሽነት ተወካዮች በቫቲካን ባደረጉት ውይይት ሁሉም የሐይማኖት ተቋማት መሪዎች እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የጋራ ቤታችን የሆነች ምድራችንን የመጠበቅ የጋራ ግብን ለማሳካት እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርቧል። መግለጫው በማከልም “ሀይማኖቶች በመንግሥታት፣ ባሕሎች እና ግለሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት በማስተሳሰር እና የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ አዲስ አድማሶችን ለመክፈት ሃይማኖቶች የሚጫወቱትን ሚና ለማጎልበት ያለመ ነው” ሲል ገልጿል። የአየር ንብረት ለውጥን አስከፊ መዘዞች ለመፍታት የሃይማኖት መሪዎች እና ተቋማት ተግባራዊ መፍትሄዎችን በማምጣት ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

የሃይማኖት ተቋማት መድረክ

የሙስሊም ሽማግሌዎች ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ፕሬዝዳንት ልዩ ተወካይ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ በዱባይ በሚካሄደው 28ኛው የተባበሩት መንግሥታት ጉባኤ ላይ የሃይማኖት ተቋማት እና የባሕል የውይይቶች መድረክ የመፍጠር ዕድልንም ታሳቢ አድርገዋል። የውይይት መድረኩ እውቀትን ለመለዋወጥ፣ በሃይማኖቶች እና ባሕሎች መካከል የውይይት መድረክ ሆኖ በማገልገል፣ የአየር ንብረት ቀውስን ለመቅረፍ ሃይማኖታዊ አመለካከቶች እና እሴቶች ያላቸውን ወሳኝ ሚና ለማጉላት ያለመ እንደሆነ ታውቋል።

01 June 2023, 13:09