ፈልግ

ቅዱስነታቸው ከሕክምና ዕርዳታ በኋላ ሆስፒታል ለቅቀው ሲወጡ ቅዱስነታቸው ከሕክምና ዕርዳታ በኋላ ሆስፒታል ለቅቀው ሲወጡ   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለጄሜሊ ሆስፒታል የሕክምና ቡድን የምስጋና መልዕክት ላኩ

በቅርቡ ለቀዶ ጥገና ሕክምና ሆስፒታል ገብተው የነበሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሆስፒታል ቆይታቸው የሕክምና ዕርዳታን ላበረከተው የባለሞያዎች ቡድን ምስጋና አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ምስጋናቸውን ያቀረቡት ለሆስፒታሉ ፋውንዴሽን ፕሬዝዳንት ለዶ/ር ማርኮ ኤሌፋንቲ በጻፉት መልዕክት ነው።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ ዘጠኝ ቀናት የቆዩበትን የጄሜሊ ሆስፒታል በማስታወስ እንደተናገሩት፥ ሆስፒታሉ “የስቃይ እና የተስፋ” ቦታ እንደሆነ ገልጸው፥ እንክብካቤን እና ትኩረት በማድረግ ለረዷቸውን የሆስፒታሉ ሠራተኞች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።    

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ " አጎስቲኖ ጄሜሊ ዩኒቨርስቲ ፋውንዴሽን" ፕሬዝዳንት ለሆኑት ለዶ/ር ማርኮ ኤሌፋንቲ በላኩት መልዕክት የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ ከቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ ላደረገላቸው እንክብካቤ እና ክትትል ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕክምና ዕርዳታ ሆስፒታል የገቡት ረቡዕ ግንቦት 30/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ እንደነበር ሲታወስ፥ ሆስፒታል ውስጥ በቆዩባቸው ዘጠኝ ቀናት ውስጥ በተሰጣቸው የሕክምና ዕርዳታ ከቀድሞው በተሻለ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የቀዶ ጥገና ሐኪማቸው የሆኑት ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ከሆስፒታል የወጡትም ሰኔ 9/2015 ዓ. ም. እንደነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕክምና ዕርዳታን ለማግኘት ሆስፒታል ሲገቡ የአሁኑ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን፥ ከዚህ ቀደም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ ወር 2021 ዓ. ም. የአንጀት ቀዶ ጥገና ሕክምናን ለማድረግ፥ በኋላም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በመጋቢት ወር 2023 ዓ. ም. የብሮንካይተስ ሕክምናን ለማደረግ ሦስት ቀናት ሆስፒታል ቆይተው መውጣታቸው ይታወሳል።

የስቃይ እና የተስፋ ቦታ

“የስቃይ እና የተስፋ ቦታ” ባሉት ሆስፒታል ውስጥ ከተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ዕርዳታ በኋላ የነበራቸው የማገገሚያ ቀናት እንደረዳቸው፣ በሆስፒታሉ ውስጥ የተመለከቱት የቤተሰባዊነት፣ የወንድማማችነት እና በእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ መደሰታቸውን ተናግረው መላው የጄሜሊ ሆስፒታል ማኅበረሰብ ላሳየው መንፈሳዊ ቅርበት ልባዊ አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ማጠቃለያው ላይ የሆስፒታሉ ማኅበረሰብ የጸሎት ድጋፍ ጠይቀው፥ ዶ/ር ማርኮ ኤሌፋንቲን እና ቤተሰቡን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው አረጋግጠውላቸዋል።

ከሆስፒታሉ የቦርድ ዳይሬክተሮች ይፋ የሆነው መልዕክት እንደገለጸው፥ የሕክምና ቡድን አባላት  በሙሉ በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ መልዕክት የተሰማቸውን የደስታ ስሜት ለመላው የሆስፒታሉ ሠራተኞች ማጋራቱን አስታውቋል።

27 June 2023, 16:12