ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለኤድና ብርታትን በመመኘት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ልከውላታል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በከባድ ሕመም ለምትሰቃይ ፖርቱጋላዊት አዳጊ ወጣት ኤድና የቪዲዮ መልዕክት ልከዋል። አዳጊ ወጣቷ ኤድናም በበኩሏ ለቅዱስነታቸው ያላትን ፍቅር በገለጸችበት መልዕክቷ፥ ከሐምሌ 25-30/2015 ዓ. ም. በፖርቱጋል መዲና ሊዝበት በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ መገኘት ባለመቻሏ የተሰማትን ሐዘን ገልጻለች።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የ17 ዓመት ዕድሜ አዳጊ ወጣት ኤድና ባደረባት ከባድ ሕመም ምክንያት በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ከፈጣሪዋ ጋር እንደምትገናኝ አውቃለች። ላለፉት ስምንት ዓመታት ለኤድና የሕክምና ዕርዳታን ሲሰጥ የቆየው ሐኪም ኤድና በሕይወት የምትቆየው ለአጭር ቀናት ብቻ እንደሆነ ነግሯታል። ኤድና ያለፈው ሐሙስ ሰኔ 15/2015 ዓ. ም. ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በላከችላቸው መልዕክት ይህን ገልጻ፥ በመልዕክቷም፥ "ዶክተሬ ከኢየሱስ ክርስርቶስ ጋር የምገናኝበትን ቀን በውል ባያውቅም ነገር ግን በቅርቡ እንደሚሆን ነግሮኛል" ስትል በተረጋጋት መንፈስ ገልጻለች።

ኤድና ከሐምሌ 25-30/2015 ዓ. ም. በፖርቱጋል መዲና ሊዝበት በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ ለመገኘት አስቀድማ የተመዘገበች ቢሆንም በሥፍራው በአካል በመገኘት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር መሆን እንደማትችል ተናግራለች። ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር በፌስቲቫሉ ላይ ለመገናኘት በሙሉ ልቧ የተመኘችው ኤድና በተፈጠረው አጋጣሚ ሐዘን ቢሰማትም ነገር ግን በቅን እምነት እና በፈገግታ መሆኑን ከአሥር ዓመታት በላይ የሚያውቋት በሊዝበን የቅዱስ ማክስሚሊያን ኮልቤ ቁምስና ምዕመናን መስክረዋል።

“ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በፖርቱጋል እንደሚከበር ስሰማ ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኝ ነበር” የምትለው አዳጊ ወጣት ኤድና፥ “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቴሌቪዥን ሲናገሩ ባየኋቸው ቁጥር ጥሩ ስሜት ይሰማኛል፣ በዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ እንዳልገኝ የሚከለክለኝ ምንም ዓይነት ሕመም እንደሌለብኝ ሆኖ ይሰማኛል” በማለት በመልዕክቷ ላይ ገልጻለች። ኤድና አክላም “ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለእኔ እና ለቤተሰቤ ምን ያህል አስፈላጊ መሆናቸውን እንዲያውቁ ለመጻፍ እፈልግ ነበር” በማለት ተናግራለች።

ኤድና ለቅዱስነታቸው የላከችው መልዕክት
ኤድና ለቅዱስነታቸው የላከችው መልዕክት

ኤድና ሆስፒታል ውስጥ ሆና የጻፈችውን መልዕክት ካነበቡ በኋላ በሰጡት ከአንድ ደቂቃ በላይ በዘለቀው ቪዲዮ፥ “አመሰግናለሁ!” የሚለውን ቃል ስድስት ጊዜ በመደጋገም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልስ ሰጥተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችሶስ ለኤድና በላኩት የቪዲዮ መልስ፥ መልዕክቷ እንደደረሳቸው ገልጸው፣ ስለ ርኅራሄዋ እና በልቧ ውስጥ ስላለው ሰላም ምስጋናቸውን ካቀረቡ በኋላ ይህ ሰላም እርሷን በሚመለከቱት እና ከእርሷ ጋር በሚያወሩት ሰዎች ልብ ውስጥ እንደተዘራ ዘር ነው” በማለት ተናግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ኤድናን በጉዞዋ ወቅት በጸሎት እንደሚደግፏት፣ በጸሎት እንደሚተባበሯት ገልጸው፥ ዘወትር የሚጠብቀን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚመለከቱ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበውላታል።

አዳጊ ወጣቷ ኤድና በመልዕክቷ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንዲጸልዩላት የጠየቀቻቸው ሲሆን፣ ቅዱስነታቸው በቪዲዮው መልዕክታቸው፣ ኤድናም በጸሎትዋ እንድታስታውሳቸው አደራ ብለው፣ ወደ አምላኳ ለመደረ በምታደርገው ጉዞዋ ብርታት እንዲሆናት በማለት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ልከውላታል።

 

24 June 2023, 16:35