ፈልግ

የጸሎት ድጋፍ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች ለቅዱስነታቸው በመላክ ላይ ይገኛሉ የጸሎት ድጋፍ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች ለቅዱስነታቸው በመላክ ላይ ይገኛሉ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ በመልካም የማገገም ሂደት ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

ረቡዕ ግንቦት 30/2015 ዓ. ም. ከዓት ለቀዶ ጥገና ሕክምና ሆስፒታል የገቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሁን ላይ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታውቋል። ቅዱስነታቸው የቀዶ ጥገና ሕክምና ከተደረገላቸው በኋላ በመልካም የማገገም ሂደት ላይ እንደሚገኙ እና ያለፉትንም ምሽቶች ጥሩ እንቅልፍ ተኝተው ማሳለፋቸውን መግለጫ ክፍሉ አክሎ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መግለጫ ክፍሉ ዓርብ ሰኔ 2/2015 ዓ. ም. ጠዋት ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ፥ ቅዱስነታቸው ሌሊቱን ጥሩ እንቅልፍ ተኝተው ማደራቸውን ገልጾ፥ ረቡዕ ግንቦት 30/2015 ዓ. ም. ከዓት በኋላ ካደረጉት የቀዶ ጥገና ሕክምና ወዲህ በመልካም ሁኔታ በማገገም ላይ እንደሚገኙ ገልጿል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ የቅዱስነታቸውን የድህረ-ቀዶ ሕክምና ዕርዳታ ከሚከታተል የሐኪሞች ቡድን ያገኙትን መረጃ ዋቢ በማድረግ በጻፉት መልዕክት፥ ቅዱስነታቸው ቀለል ያሉ ፈሳሽ ምግቦችን መመገብ መጀመራቸውን፥ የደም ግፊት እና የመተንፈሻ አካላት መለኪያ መሣሪያዎች መደበኛ ውጤቶችን ማሳየታቸውን ተናግረው፥ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በነበረው አጭር የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ቅዱስ ቁርባን መቁረባቸውንም ገልጸዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በመላው ዓለም ከሚገኙ ካቶሊካው ምዕመናን እና በጎን ከሚመኙላቸው ሰዎች በሙሉ የጸሎት ድጋፍ እና የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክቶች እንደተላከላቸው በሰሙ ጊዜ ቅዱስነታቸው በምላሹ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበው ምዕመናኑ በጸሎታቸው ሳያቋርጡ እንዲያስታውሷቸውም አደራ ብለዋል።   

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ በሆስፒታል የሚቆዩበትን የጊዜ መጠን ተጠይቀው “በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ ይወሰናል” ብለው የነበሩት ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ፥ “በመደበኛው የጥንቃቄ ማድረጊያ ጊዜ መጠን መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሆስፒታል ውስጥ ከ 5 እስከ 7 ቀናት ሊቆዩ ይችላሉ” በማለት ተናግረዋል።

09 June 2023, 14:16