ፈልግ

ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ እና አቶ ማቴዮ ብሩኒ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ እና አቶ ማቴዮ ብሩኒ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከቀዶ ጥገና ሕክምና በኋላ በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ተገለጸ

ረቡዕ ግንቦት 30/2015 ዓ. ም ከዓት በኋላ ለቀዶ ጥገና ሕክምና ሆስፒታል የገቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሕክምናው ያለ ምንም ችግር ተከናውኖላቸው አሁን በጥሩ መንፈስ ላይ መሆናቸውን የቀዶ ጥገና ሐኪማቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሮም ከተማ በሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሐኪም ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፥ “ለቅዱስነታቸው የተደረገላቸው የቀዶ ጥገና ዕርዳታ ያለ አንዳች ችግር መከናወኑን ገልጸው፥ ሕክምናው የሚጠይቀው ያህል እንክብካቤ ከተደረገላቸው በኋላ ሙሉ በሙሉ ያገግማሉ” ብለዋል። ዶ/ር ሴርጆ አክለውም ለቅዱስነታቸው አሁን የተደረገው የቀዶ ጥገና ዕርዳታ ከዚህ በፊት “ሄርኒያ” ለተባለ የሆድ ቀዶ ጥገና ከተደረገላቸው በኋላ የተፈጠረውን ጠባሳ ለማስወገድ የተደረገ ሕክምና ዕርዳታ እንጂ ድንገተኛ ሕመም አለመሆኑን አስረድተዋል።

ድንገተኛ ሕመም አይደለም!

“ለቅዱስነታቸው የተደረገው የቀዶ ጥገና ሕክምና ዕርዳታው ድንገተኛ ቢሆን ኖሮ ለሌላ ቀጥሮ ማክሰኞ ግንቦት 29/2015 ዓ. ም. ወደ ሆስፒታል በመጡ ጊዜ ወዲያው ሕክምና ይደረግላቸው ነበር" ብለው፥ ከዚህ በፊት የ “ሄርኒያ” ሕመምን ከታከሙ በኋላ የተፈጠረው ጠባሳ አልፎ አልፎ ሕመም እንዲሰማቸው በማድረጉ ምክንያት የሕክምና ቡድኑ ቀጠሮ አስይዟቸው እንደነበር ገልጸዋል። ለቅዱስነታቸው በተደረገላቸው በዛሬው የቀዶ ጥገና ሕክምና አማካይነት አልፎ አልፎ የሕመም ስሜት የሚፈጥር ውስጣዊ ጠባሳ መገኘቱን ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። ዶ/ር ሴርጆ አክለውም በሆድ ግድግዳ ላይ የነበረው ጠባሳ በፕላስቲክ ቀዶ ጥገና በመታገዝ መስተካከሉንም አስረድተዋል።

ምንም ዓይነት ውስብስብ ነገሮች የሉትም!

"ቀዶ ጥገናው እና አጠቃላይ የማደንዘዣ ዕርዳታው ያለ ምንም ችግር መካሄዱን የገለጹት ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ፣ ቅዱስነታቸው ለተደረገላቸው የሕክምና ዕርዳታ ሁሉ ጥሩ ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል። ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ዶ/ር ሴርጆ ሲመልሱ፥ ከእንዲህ ዓይነቱ ቀዶ ጥገና ለማገገም በሆስፒታል ውስጥ ሰባት ቀናት ያህል እንደሚወስድ ገልጸው፥ ከዕድሜያቸው አኳያ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሁሉንም ዓይነት ጥንቃቄዎች እንደሚያደርጉላቸው ገልጸው፥ ከቀዶ ሕክምና በኋላ ያለውን የማገገሚያ ጊዜን በሚቀጥሉት ቀናት ውስጥ እንደሚወስኑ ተናግረዋል።

የመግለጫ ሥነ-ሥርዓቱን ያስተባብሩት የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ቀደም ሲል በበኩላቸው እንደተናገሩት፥ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር የተያዙ የተለያዩ ቀጥሮዎች በሙሉ እስከ ሰኔ 11/2015 ዓ. ም. ድረስ መሰረዛቸውን አረጋግጠዋል። ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ በዛሬው ሂደትም ሆነ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2021 ዓ. ም.  ባደረጉት የመጨረሻው ሕክምና ዕርዳታ ወቅት ቅዱስነታቸውን ምንም ዓይነት ችግር እንዳላጋጠማቸው ገልጸው፥ እንዲሁም ሌሎች በሽታ አምጪ ተህዋሲያን ወይም የሕመም ዓይነቶች በቅዱስነታቸው እንዳልተገኘባቸው ተናግረዋል።

ለሆስፒታሉ ሠራተኞች ምስጋናቸውን አቅርበዋል

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሐምሌ ወር 2021 ዓ. ም. ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሕክምና ዕርዳታን ያደረጉት፥ ሮም በሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል የቀዶ ጥገና ሐኪም ዶ/ር ሴርጆ አልፊዬሪ በመግለጫቸው ማጠቃለያ፥ በዛሬው ወይም ከሁለት ዓመት በፊት ባደረጉት የሕክምና ዕርዳታ ወቅት ቅዱስነታቸው ምንም ዓይነት እክል አጋጥሟቸው እንደማያውቅ እና ጠቅላላ ማደንዘዣም በመልካም ሁኔታ መከናወኑን ገልጸው፥ በእነዚህ ጊዜያት በሙሉ ከጎናቸው በመሆን ድጋፋቸውን እና ሙያዊ ብቃታቸውን በትጋት እና በታታሪነት ላሳዩት የጄሜሊ ሆስፒታል ሠራተኞች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።  

08 June 2023, 10:52