ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “ቅድስት ሜሪ ማኪሎፕ የኢየሱስን ፍቅር ወደ አውስትራሊያ አምጥታለች” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ሰኔ 21/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበዋል። ጣሊያንን ጨምሮ ከተለያዩ አገራት የመጡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች የቅዱስነታቸውን አስተምህሮ ተከታትለውታል። ቅዱስነታቸው በዛሬው የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፥ “ቅድስት ሜሪ ማኪሎፕ የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር ወደ አውስትራሊያ አምጥታለች” ብለዋል። ክቡራት ክቡራን ተከታታዮቻችን ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ያቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን በፊት በዕለቱ ያስተነተኑበትን የቅዱስ ወንጌልጥቅስ ከዚህ ቀጥሎ እናቀርብላችኋለን፥

“ከዚህ በኋላ ወደ ቅፍርናሆም መጡ። ቤት ከገባ በኋላም “በመንገድ ላይ የምትከራከሩት ስለምን ነበር ብሎ ጠየቃቸው። ከተቀመጠ በኋላ አሥራ ሁለቱን ጠርቶ “መጀመሪያ ለመሆን የሚፈልግ ከሁሉ መጨረሻና የሁሉም አገልጋይ ይሁን” አላቸው። ትንሽ ልጅ አምጥቶ በመካከላቸው አቆመ። አቅፎትም “ከእነዚህ ሕጻናት አንዱን በስሜ የሚቀበል ሁሉ እኔን ይቀበላል፤ እኔንም የሚቀበለኝ ሁሉ የሚቀበለው እኔን ሳይሆን የላከኝን ነው” አላቸው። (ማር. 9: 33. 35-37)

ክቡራት ክቡራን ተከታታዮቻችን ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ያቀረቡትን ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ሙሉ ትርጉም እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን:-

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

"ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ! በዛሬው ተከታታይ የሐዋርያዊ ቅንዓት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ፣ በዘመናት ሁሉ በየቦታው የኖሩትን፣ ለወንጌል ሲሉ ሕይወታቸውን በሙሉ ለአገልግሎት በመስጠት አርአያ የሚሆኑ ወንድና ሴት ሰዎችን እናገኛቸዋለን። በዚህ ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ በርካታ ትናንሽ እና ትላልቅ ደሴቶች ወደሚገኙበት ኦሼንያ ውስጥ እንሄዳለን። ብዙ የአውሮፓ ስደተኞች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያለቸውን እምነት ወደ አካባቢው አገራት በማምጣታቸው ብዙም ሳይቆይ በአጭር ጊዜ ሥር በመስደድ ብዙ ፍሬ አፈራ። ከእነዚህ ስደተኞች መካከል የቅዱስ ልብ ቅዱስ ዮሴፍ እህቶች ማኅበር መሥራች እና ሕይወቷን በሙሉ በገጠራማው የአውስትራሊያ ግዛቶች ውስጥ ለሚገኙ ድሃ ሕዝቦች ዕውቀትን እና ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ያስተማረች ሜሪ ማኪሎፕ የተባለች ድንቅ መነኩሴ ትገኝበታለች።

ሜሪ ማኪሎፕ በአውስትራሊያ ሜልበርን ከተማ አቅራቢያ ከስኮትላንድ ወደ አውስትራሊያ ከተሰደዱ ወላጆች የተወለደች ናት። ሜሪ ማኪሎፕ ከሕጻንነቷ ጀምሮ እግዚአብሔርን ለማገልገል እና ስለ እርሱ በቃል ብቻ ሳይሆን ከሁሉ በላይ በእግዚአብሔር በተለወጠ ሕይወቷ በተግባር ልትመሰክር የተጠራች እንደሆነች ይሰማት ነበር። ከሞት የተነሳውን ኢየሱስ ክርስቶስ ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘችው እና ለደቀ መዛሙርቱ መልካም ዜና እንድትናገር በእርሱ እንደተላከችው እንደ መግደላዊት ማርያም፣ ሜሪ ማኪሎፕም የምሥራቹን ቃል ለሌሎች እንድትሰብክ እና ከሕያው እግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙ ለመሳብ የተላከች እንደሆነች እርግጠኛ ነበረች።

ሜሪ ማኪሎፕ የዘመኑን ምልክቶች በጥበብ በማስተዋል፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የእምነት ትምህርት የቅዱስ ወንጌል ትምህርት አካል መሆኑን በመገንዘብ፣ ለእርሷ የተሻለው መንገድ ወጣቶችን ማስተማር እንደሆነ ተገነዘበች። በመሆኑም እያንዳንዱ ቅዱስ በተወሰነ የታሪክ ቅጽበት የቅዱስ ወንጌል ገጽታን ለማንፀባረቅ እና ለመምሰል የእግዚአብሔር እቅድ ተልዕኮ ያለው ነው” ማለት ይቻላል። ሜሪ ማኪሎፕም ይህን የእግዚአብሔር እቅድ ተልዕኮ በዋነኛነት የገለጸችው ትምህርት ቤቶችን በማቋቋም ነበር።  

ሜሪ ማኪሎፕ ለወንጌል ያላት ቅንዓት አንዱ አስፈላጊ ገጽታ፥ ድሆችን እና የተገለሉ ሰዎችን መንከባከብ ነበር። ይህ ቅንዓትም ሌሎች ወደማይሄዱበት ወይም መሄድ ወደማይችሉበት አካባቢዎች እንድትሄድ አነሳሳት። ሜሪ ማኪሎፕ የቅዱስ ዮሴፍ በዓል በተከበረበት ዕለት እንደ ጎርጎሮስውያኑ በመጋቢት 19/1866 ዓ. ም. በደቡብ አውስትራሊያ በአንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ የመጀመሪያውን ትምህርት ቤት ከፈተች። በአውስትራሊያ እና በኒው ዚላንድ ገጠራማ አካባቢዎች እርሷ እና እህቶቿ በመሠረቱት ትምህርት ቤት ውስጥ ብዙዎች ትምህርታቸውን ተከትለዋል።

የትምህርት ዋና ዓላማ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ የአንድን ሰው ሁለንተናዊ ዕድገት ማረጋገጥ እና ይህም የእያንዳንዱን አስተማሪ ጥበብ፣ ትዕግስት እና ልግስናን እንደሚጠይቅ ሜሪ ማኪሎፕ እርግጠኛ ነበረች። በእርግጥም ትምህርት ጭንቅላትን በሃሳብ መሙላት ሳይሆን በሰብዓዊ እና በመንፈሳዊ የዕድገት ጎዳና ላይ የሚገኙ ተማሪዎችን በማበረታታት፣ ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለው ወዳጅነት ምን ያህል ልብን እንደሚያሰፋ እና ሕይወትን የበለጠ ሰብዓዊ እንደሚያደርግ ማሳየት ነው። ቤተሰቦችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና መላውን የኅብረተሰብ ክፍል አንድ የሚያደርግ የትምህርት ሥርዓት ውል እንደሚያስፈልግ ከተረዳን ጠቃሚ ነው።

ሜሪ ማኪሎፕ ወንጌልን ለድሆች ለማዳረስ ያሳየችው ቀናኢነት፣ በአዴላይድ ከተማ ውስጥ ከከፈተችው የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል ጀምሮ የተጣሉ ሕጻናትን በመሰብሰብ የተለያዩ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን እንድትሠራ አድርጓታል። ሜሪ ማኪሎፕ በእግዚአብሔር ዕርዳታ ላይ ብዙ እምነት ያላት ሰው ነበረች። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የእግዚአብሔር እርዳታ እንዳለ ዘወትር እርግጠኛ ነበረች። ነገር ግን ይህ በሐዋርያዊ ሥራዎችዋ መካከል ሊመጡ ከሚችሉ ጭንቀትች እና ችግሮች ሊያድናት አልቻለም። መልካም ምክንያቶችም ነበሯት። ለአገልግሎት የምታወጣቸውን ወጭዎች መክፈል መቻል ነበረባት፤ ከሀገረ ስብከቱ ጳጳስ እና ካህናት ጋር መገናኘት፣ ትምህርት ቤቶችን ማስተዳደር እና የማኅበርተኞችዋን ሙያዊ እና መንፈሳዊ ትምህርቶችን ማስተባበር እና መከታተል ነበረባት። በኋላም የጤና ችግሮችም ነበሯት። ሆኖም ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ የተልዕኮው ዋና አካል የሆነውን መስቀልን በትዕግስት ተሸክማ መረጋጋት ችላለች።

ሜሪ ማኪሎፕ በቅዱስ መስቀል ክብረ በዓል ላይ ለአንድ የማኅበሯ እህት፥ "ልጄ ሆይ! ለብዙ ዓመታት መስቀልን መውደድ ተምሬአለሁ" በማለት ተናግራ ነበር። ሜሪ ማኪሎፕ መከራ በሚዛበት እና ጨለማ ውስጥ በምትገኝበት ጊዜ ደስታዋም በተቃውሞ እና በንቀት ሲቀንስ ፈጽሞ ተስፋን አልቆረጠችም። ጌታም “የጭንቀትን እንጀራ እና የመከራን ውኃ” ቢሰጣትም በድል ለመወጣት እርግጠኛ ሆና ቆየች። (ኢሳ. 30:20) እግዚአብሔር ራሱ ብዙም ሳይቆይ ለቅሶዋን መልሶ በጸጋ ሞላው። የሜሪ ማኪሎፕ ሐዋርያዊ ቅንዓት ምስጢርም ይህ ነበር።"

28 June 2023, 14:37