ፈልግ

ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን እና የ “አረንጓዴ እና የሰማያዊ” ፌስቲቫል ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን እና የ “አረንጓዴ እና የሰማያዊ” ፌስቲቫል   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በእግዚአብሔር ፊት ምድራችንን ከውድመት የመጠበቅ ኃላፊነት አለብን!” አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን ጋር አንድ ላይ ለሚከበር የ “አረንጓዴ እና ሰማያዊ” ፌስቲቫል አዘጋጆች እና ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር፥ “የማያቋርጥ የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው አስከፊ አደጋዎች ምድርን የመጠበቅ ኃላፊነት በእግዚአብሔር ፊት አለብን” ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዓለም አቀፍ የአካባቢ ቀን በተከበረበት ሰኞ ግንቦት 28/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ለተገኙት የአረንጓዴ እና ሰማያዊ ፌስቲቫል ተሳታፊዎችን እና አስተባባሪዎችን ቅዱስነታቸው ባደረጉት ንግግር “የአየር ንብረት ለውጥ ያስከተለው አስከፊ ውጤት በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ ያደርገናል” ብለዋል። ሰኞ ግንቦት 28/2015 ዓ. ም. በሮም፥ ቀጥሎም ከግንቦት 29 – ሰኔ 1/2015 ዓ. ም. ድረስ በሚላን ሊቀርቡ የታቀዱት ዝግጅቶች የአየር ንብረት ለውጥን በአስቸኳይ ለመዋጋት ቁርጠኝነት ያላቸውን ከጣሊያን እና ከዓለም አቀፍ ደርጃ የተወጣጡ ባለ ሙያዎችን ያሰባሰበ እንደሆነ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባለሙያዎችን በቫቲካን ተቀብለው ባነጋገሯቸው ወቅት አካባቢን ለመጠበቅ በሚያደርጉት ቁርጠኝነት ብርታትን ተመኝተው፣ በተጨማሪም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና በጎ ፈቃድ ያላቸው ሰዎች የጋራ መኖሪያ ምድራችንን ከጉዳት በመጠበቅ ረገድ ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበው፣ ዓለምን እያወደሟት ያሉ እጅግ ኃይለኛ የተፈጥሮ አደጋዎች መኖራቸውን በመናገር ተጨባጭ እርምጃን በመውሰድ የጋራ ሃላፊነታችንን ልንገነዘብ ይገባል ብለዋል።

ቅዱስነታቸው ለፌስቲቫሉ አዘጋጆች እና ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ "የአየር ንብረት ለውጥ ባለሞያዎች በእነዚህ አሥርት ዓመታት ውስጥ የተቀመጡት ምርጫዎች እና ድርጊቶች በሺዎች በሚቆጠሩ ዓመታት ላይ ተጽእኖ እንደሚኖራቸው በግልፅ ማስረዳታቸውን ተናግረው፥ “ተግባራችንም በጋራ መኖሪያ ምድራችን እና በሚኖሩት ሰዎች ላይ ተጽእኖ እንዳለው ዕውቀታችንን ማስተላለፍ ነው” ብለዋል።

በእግዚአብሔር ፊት ያለን ኃላፊነት

“ይህም ፍጥረትን በአደራ በሰጠን በእግዚአብሔር ፊት፣ በጎረቤቶቻችን እና በመጪው ትውልድ ፊት ያለንን የኃላፊነት ስሜት ይጨምራል” ብለዋል። ከድህረ-ኢንዱስትሪ አብዮት ወዲህ ያለው የሰው ልጅ፥ በታሪክ ውስጥ እጅግ በጣም ኃላፊነት ከጎደላቸው እንደ አንዱ ሊታወስ ይችላል” በማለት አስታውሰዋል። በሌላ ወገንም በ 21ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረው የሰው ልጅ ከባድ ሃላፊነቶቹን በልግስና የወሰደ በመሆኑ ሊታወስ እንደሚችል ተናግረዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ ክስተት በተለይ ለአደጋው ዝቅተኛ አስተዋጽኦን የሚያደርጉትን ድሆችን እና አቅመ ደካሞችን፣ ከሁሉም በላይ በአደጋው ለሚሠቃዩ ሰዎች ኃላፊነት እንዳለብን አጥብቆ ያሳስበናል” ብለዋል።በፊታችን ያለውን ተግዳሮት መጠን እና አጣዳፊነት በመገንዘብ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአብሮነት ላይ በተመሠረተ የወደፊት ተግባራት አፈፃፀም ላይ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

በአካሄድ ላይ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል

“ይህ ትልቅ ጥረትን የሚጠይቅ ተግዳሮት መሆኑን ተገንዝበነዋል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ አሁን ባለው የፍጆታ እና የምርት ሞዴል ላይ ወሳኝ ለውጥ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፥ ዓለማችን በብኩንነት እና በግዴለሽነት ባሕል መሞላቱን ገልጸው፥ በማከልም፥ “በሳይንሱ ዓለም ውስጥ የሚገኙ ብዙ ተመራማሪዎች እንደሚናገሩት ሁሉ፥ ይህን ሞዴል ቀጠሮ ሳይሰጡ በአስቸኳይ መለወጥ ያስፈልጋል” ማለታቸውንም አስታውሰዋል።

ምድራችንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን እና ይህ ደግሞ ኅብረተሰቡን እንዴት እንደሚለውጥ ማስተማር እንደሚገባ ቅዱስነታቸው ጠይቀዋል። ከጥቃቅን የዕለት ተዕለት ምርጫዎች ጀምሮ እስከ አካባቢያዊ ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎች ድረስ በሁሉም ደረጃዎች የጋራ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ በመግለጽ፥ ፈተናዎችን በቆራጥነት ለመቅረፍ ያለሙ የተለያዩ ዕድሎችን እና ውጥኖችን በመጥቀስ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አካባቢን በአግባቡ ለመጠበቅ ተጨማሪ ወጪ እና መስዋዕትነት መክፈል እንደሚገባ አምነው፥ ለሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ ግምትን የሚሰጡ ሰዎችን አመስግነዋል። "የመተሳሰብ ባሕልን በመደገፍ የትምህርት ሥርዓት ለውጥን ማፋጠን ያስፈልጋል" ብለው፥ ለሰው ልጅ ክብር እና ለጋራ ጥቅም መቆርቆር ቅድሚያ የሚሰጥበት ጉዳይ እንደሆነም አስረድተዋል።

የወደፊት ትውልዶች ተስፋ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቫቲካን ለተቀበሏቸው የ “አረንጓዴ እና ሰማያዊ” ፌስቲቫል አዘጋጆች እና ተሳታፊዎች ያደረጉትን ንግግር ሲያጠቃልሉ፥ አካባቢን ከጉዳት ለመጠበቅ ለሚያደርጉት ጥረት ምስጋናቸውን አቅርበው፥ “የአዲሱን ትውልድ የተሻለ ጊዜ ተስፋን መሰወር የለብንም” በማለት ተናግረዋል። አገር አቀፉ የአካባቢ ጥበቃ ዝግጅት በተለያዩ ቦታዎች ከአራት ቀናት በላይ የሚካሄድ ሲሆን፥ ዓላማውም የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል አስቸኳነት ለማጉላት ብቻ ሳይሆን፥ አስፈላጊውን ለውጥ ለማምጣት ለቀረቡት ግዙፍ ዕድሎች አፅንዖት ለመስጠት ያለመ መሆኑን እንግዶቹ ገልጸው፣ ፌስቲቫሉ ላይ የሚቀርቡ ንግግሮች እና የሙዚቃ ትርኢቶች የትብብር መንፈስን እንደሚፈጥሩ እና እንደሚያነሳሱ አስረድተዋል።

06 June 2023, 15:20