ፈልግ

በዩክሬን ውስጥ ጦርነት ያስከተለው ቀውስ በዩክሬን ውስጥ ጦርነት ያስከተለው ቀውስ 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ "ሰላም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በሙሉ የሰጠው ስጦታ ነው!" አሉ

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ያዘጋጀውን ጉባኤ የተካፈሉት ሊቀ ጳጳሳት አቡነ ፖል ጋላገር ለስብሰባው ተካፋዮች የር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስን መልዕክት በንባብ አሰምተዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለጉባኤው ተካፋዮች በላኩት መልዕክት፥ በእውነት ከተፈለገ ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል ፤ ሰላም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በሙሉ የሰጠው ስጦታ እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ ሕዝቦች ከቂም እና ከጠበኛ ብሔርተኝነት እንዲቆጠቡ አሳስበው፣ የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በግልጽነት እና በቅንነት እንዲተገበር አበራትተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው በኒውዮርክ ለተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ በላኩት መልዕክት፥ ዓመፅ፣ ግጭቶች እና የጦር መሣሪያዎች ግንባታ ቆሞ በዛሬው ዓለም እየተስተዋለ ባለው የወንድማማችነት ጥማት ላይ እንዲያስተነትኑ ጥሪያቸውን በድጋሚ አቅርበዋል። “ጦርነትን አሻፈረን የምንልበት ጊዜ ደርሷል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ፍትሃዊው ጦርነት ሳይሆን ሰላም ብቻ መሆኑን የምንገልጽበት ጊዜ ደርሷል” ብለው፥ “በእውነት ከተፈለገ ሰላምን ማንገሥ ይቻላል" ብለዋል። ይህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ግልጽ መልዕክት፣ ቅዱስነታቸው ሮም በሚገኝ ጄሜሊ ሆስፒታል ውስጥ ከሕመማቸው በማገገም ላይ በሚገኙበት ወቅት በኒውዮርክ ለተሰበሰበው የፀጥታው ምክር ቤት ጉባኤ ተካፋዮች በንባብ ያቀረቡት፥ በቅድስት መንበር የመንግሥታት ግንኙነት ጽሕፈት ቤት ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ናቸው።

የሦስተኛው ዓለም ጦርነት ውጊያ

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክት የሚጀምረው፥ “የሰው ልጅ የሚገኝበት ይህ ወሳኝ ጊዜ ሰላም ለጦርነት ቦታ የለቀቀ በሚመስልበት፣ በታሪክ ውስጥ ወደ ኋላ እየተመለስን ያለን በሚመስለን ጊዜ፣ ጽንፈኝነት፣ ቂምና ጨካኝ ብሔርተኝነት በየቦታው ግጭቶችን እየቀሰቀሱ የበለጠ ጠብ አጫሪ እየሆኑ መጠጥተዋል” በማለት እንደሆነ ተመልክቷል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ግጭቶች እየጨመሩ እና መረጋጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን አስገንዝበው፥ “እየኖርን ያለነው ሦስተኛው የዓለም ጦርነት በጥቂቱ እየተካሄደ በሚገኝበት ወቅት እና ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ ነው” ብለዋል።

የተሳሳተ አመለካከትና የወገን ጥቅምን መቃወም

“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ የደህንነት እና የሰላም ቁጥጥር ተልዕኮው በሰዎች ዓይን አቅመ ቢስ እና ሽባ የሆነ ይመስላል" ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ቅድስት መንበር ምክር ቤቱ ሰላምን ለማስፈን ለሚጫወተው ወሳኝ ሚና ምስጋናዋን እንደምታቀርብ በመግለጽ፥ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት፣ ርዕዮተ ዓለማዊ አመለካከቶችን እና የወገን ፍላጎቶችን እንዲጋፈጡ በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በግልፅ ይተግበር

ለሁሉ የሰው ልጆች ጥቅም ለቆመ ለአንድ ሐሳብ ብቻ ጥረት እንዲደረግ አጽንዖት የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር በግልፅ እና በቅንነት፣ ያለ ስውር ዓላማ የግዴታ እና የፍትህ ማስፈጸሚያ እንጂ የተሳሳቱ ዓላማዎች መደበቂያ ባለመሆኑ ቻርተሩን ማክበር እና ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም በግሎባላይዜሽን ዓለም ዛሬ ሁላችን ብንቀራረብም ነገር ግን ወንድማማችነት በተጨባጭ እንደማይታይ ጠቁመው፥ ከብዙ የፍትሕ መጓደል፣ ከድህነት፣ ከኑሮ አለመጣጣም እና ከመተሳሰብ ባሕል እጦት የተነሳ በወንድማማችነት ጥማት እንሰቃያለን” ብለዋል።

ወደ ኋላ መጓዝ

የጎርጎሮሳውያኑን 2023 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የሰላም ቀን መልዕክታቸውን የጠቀሱት ቅዱስነታቸው፥ በአዳዲስ አስተሳሰቦች የተዋጠ ግለኝነት፣ ራስ ወዳድነት እና ፍቅረ ንዋይ ማኅበራዊ ትስስርን እያዳከመው እንደሚገኝ፣ ይህም ወደ ንቀት እና ግድ የለሽነት እየሚያመራ አቅመ ደካሞችን ወደ መዘንጋት እንደሚያደርስ ተናግረው፣ በዚህ መንገድ የሰው ልጅ አብሮ የመኖር ባሕል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠፋ ወደ ራስ ወዳድነት እንደሚዳርግ አስረድተዋል። የወንድማማችነት ጥማት አስከፊ ውጤቱ "የትጥቅ ትግል እና ጦርነት" እንደሆነ ገልጸው፥ ይህም ግለ ሰቦችን ብቻ ሳይሆን መላውን ሕዝብ እርስ በራሱ ጠላት በማድረግ፣ አሉታዊ ውጤታቸውም ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ያደርጋል" ብለዋል። ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት አለ መማር እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተመሠረተበትን ምክንያት ባለመረዳት የሰው ልጅ ወደ ኋላ መጓዙን አስረድተዋል።

ከጦር መሣሪያ ሽያጭ በቀላሉ የሚገኝ ትርፍ

እንደ እምነት ሰው፥ ሰላም እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በሙሉ የሰጠው ስጦታ እንደሆነ በመልዕክታቸው ያረጋገጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ነገር ግን ይህ አስደናቂ የእግዚአብሔር ስጦታ በጦርነት ምክንያት ወደ ስቃይ እንደሚለወጥ አስረድተዋል። “የችግሩ ምንጭ ኢኮኖሚያዊ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ጦርነት የሚያታልል እና ትርፍን የሚያስገኝ፣ በብዙዎች ስቃይ ጥቂት ሰዎች የሚበለጽጉበት ነው” በማለት አስረድተዋል። ሰላምን ለማስጠበቅ ሲባል በቀላሉ የሚገኘው የገንዘብ ትርፍ ይቁም ለማለት ድፍረት እንደሚጠይቅ፣ ጦርነት ከማድረግ ይልቅ ሰላምን መፈለግ፣ እርስ በርስ ተገናኝቶ መወያየት፣ ከግጭት ይልቅ ለድርድር ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መቅረብ የበለጠ ድፍረትን እንደሚጠይቅ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኒውዮርክ ለተሰበሰበው የመንግሥታቱ ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት ጉባኤ በላኩት መልዕክት ተናግረዋል።  

15 June 2023, 17:13