ፈልግ

የሩስያ ጦር ኃይል በዩክሬን ያካሄደው የሚሳይል ጥቃት የሩስያ ጦር ኃይል በዩክሬን ያካሄደው የሚሳይል ጥቃት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በጦርነት ለምትሰቃይ ዩክሬን ሰላም እንዲወርድ ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ረቡዕ ሰኔ 21/2015 ዓ. ም. ካቀረቡትን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ በመቀጠል፥ በጦርነት አደጋ ውስጥ በምትገኝ ዩክሬን ሰላም እንዲወርድ በማለት ጥሪ አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በአተምህሮአቸው ማጠቃለያ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ላይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሰኔ 22/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ በዓል በማስታወስ፥ በጦርነት የተጎዳውን የዩክሬን ሕዝብ የአማላጅነት አደራ ለቅዱሳኑ ሰጥተዋል።ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም የትምህርት ውል አስፈላጊነት እና የወጣቶች የወደፊት ሰላም እና ወንድማማችነት በማስታወስ፥ እየተደረገ ባለው ጥረት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምዕመናን በዩክሬን በድህነት እና በጦርነት ውስጥ ለሚሰቃዩ ሰዎች ተጨባጭ የወንጌል ምስክሮች መሆናቸውን ገልጸው፥ሐሙስ ሰኔ 22/2015 ዓ. ም. የቅዱስ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ዕለት መሆኑን ከፖላንድ እና ከጣሊያን የተለያዩ ሀገረ ስብከቶች ለመጡት ምዕመናን አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በዩክሬን የሁለቱ ሐዋርያት የቅዱስ ጴጥሮስ እና የቅዱስ ጳውሎስ አማላጅነት በቅርቡ ሰላም እንዲያስገኝ ተማጽነው፥ ጦርነቱ ባስከተለው አደጋ ምክንያት በዩክሬን በርካታ ሰዎች እንደሚሰቃዩ መዘንጋት የለብንም” ብለዋል።

"የትምህርት ውል" አስፈላጊነት

በዛሬው ዕለት ያቀረቡትን ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የአውስትራሊያዊ መነኩሴ የቅድስት ሜሪ ማኪሎፕ ሐዋርያዊ ቅንዓት እና የበጎ አድራጎት ሥራዎቿ አስፈላጊነት በመግለጽ፥ በተለይም በገጠራማው አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶችን እና መኖሪያ ቤቶችን መሠረት በማድረግ ለተቸገሩት ሰዎች ድጋፍ ታደርግ እንደነበር ተናግረዋል።

ቤተሰቦችን፣ ትምህርት ቤቶችን እና መላውን የኅብረተሰብ ክፍል አንድ የሚያደርግ የትምህርት ሥርዓት ውል እንደሚያስፈልግ ያስረዱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “የቅድስት ሜሪ ማኪሎፕ ሐዋርያነት ዛሬም ወቅታዊ ነው” በማለት ተናግረዋል። በመሆኑም መምህራንን እና የትምህርት አገልግሎትን ለማሳደግ የሚተጉትን በሙሉ መደገፍ እንደሚገባ እና ለወጣቶች የወደፊት ሰላም እና ወንድማማችነት እየተደረገ ላለው ጥረት ተጨማሪ ድጋፍ እንዲደረግ አደራ ብለዋል። ቅድስት ሜሪ ማኪሎፕ ለሁሉ ሰው ዕድገት በተለይም ተጋላጭ ለሆኑት ፍትሃዊ እና የበለጠ ወንድማማች ማኅበረሰብን ለመገንባት ያደረገቻቸውን ጥረቶች አስታውሰዋል።

28 June 2023, 14:45