ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ጥሪን በማበረታታት ላይ ከሚገኝ ማኅበር አባላት ጋር በቫቲካን ሲገናኙ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ጥሪን በማበረታታት ላይ ከሚገኝ ማኅበር አባላት ጋር በቫቲካን ሲገናኙ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ለወጣቶች ግራ መጋባት ወንጌል መልስ እንደሚሆናቸው ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የወንጌል አገልግሎት ጥሪን በማበረታታት ላይ የሚገኝ ማኅበር አባላትን ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው መልዕክት አስተላልፈዋል። ሕይወታቸውን ለወንጌል አገልግሎት ለማቅረብ የሚፈልጉ ወጣቶች እንዳሉ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ጥሪያቸውን በሚገባ ለመገንዘብ መንፈሳዊ ማስተዋልን በማድረግ ላይ ለሚገኙ ወጣቶች ትኩረት በማድረግ መርዳት እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ጸሎት፣ ወንጌልን መመስከር እና ተልዕኮ፣ ጥሪዎችን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉት ሦስት መንገዶች መሆናቸውን፣ ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው የአገልግሎት ጥሪን በማሳደግ ላይ ለሚገኝ ማኅበር አባላት ገልጸዋል። ጥሪዎችን ማዘጋጀት፣ ማሳደግ እና መንከባከብ እንደሚገባ የጠየቁት ቅዱስነታቸው፣ ይህን ማድረግ የሚቻለው የማኅበሩ መሥራች የቅዱስ ጁስቲኖ ሩሶሊሎ ምሳሌን በመከተል እንደሆነ አሳስበው፣ ሰው ለጥሪ መበራከት ምን ያህል በልቡ እንደሚጸልይ ራሱን ሊጠይቅ ይገባል ብለዋል።

ጸሎት በክርስትና ሕይወት መካከል የምናገኘው የእግዚአብሔር ፍቅር ነጸብራቅ በመሆኑ ምስጋናን ልናቀርብለት እንደሚገባ ገልጸው፣ ጸሎት በዚህ መንገድ ለጥሪ ማደግ የመጀመሪያውን ድጋፍ እንደሚሰጥ፣ በጸሎት አማካይነት በተለይ ወጣቶች ራሳቸውን ለእግዚአብሔር በማቅረብ ምርጫ እንደሚማረኩ አስረድተዋል። 

ጥሪዎች፣ በተለይም ራስን ለምንኩስና ሕይወት ማቅረብ ብዙውን ጊዜ በጸሎት ሕይወት አማካይነት እንደሚወለድ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ መልካም ምሳሌነታቸውን ፣ የልብ ሰላም፣ የማይሸነፍ ደስታ እና የመልካም አቀባበል ባህሪን ከሚያሳዩ ካኅናት ወይም መንኮሳት እንደሚገኙ አስረድተው፣ ለዚህም የሚያበቃን ጸሎት በመሆኑ ቸል ሳንል ለጥሪ ማደግ በብርቱ መጸለይ እንደሚገባ አደራ ብለዋል።

እምነትን ወደ ሌሎች ለማስተላለፍ የሚደረግ ምስክርነት

ከጸሎት ጋር ጎን ለጎን የሚሄድ የወንጌል ምስክርነት መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ኢየሱስ ክርስቶስን ለሌሎች መመስከር የትምህርተ ክርስቶስ አገልግሎት አንዱ እና ጠቃሚ ገጽታ መሆኑን ተናግረዋል። በሰዎች በተለይም በወጣቶች መካከል ብዙውን ጊዜ ግራ የመጋባት ምልክት በሚታይበት በዛሬው ዘመን እምነትን በቀላል መንገድ እና በጋለ ስሜት ለማሳወቅ ወደ ወንጌል ምስክርነት መመለስ እንደሚያስፈልግ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አብራርተዋል።

በቤተ ክርስቲያን ወንጌልን የመመስከር አስፈላጊነት እንዳለ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ “ሐዋርያዊ ጥሪያችንም ከምንም በላይ ከሰዎች ጋር መገናኘት፣ መደማመጥ እና ጥሪን በሚገባ የሚገነዘቡበት መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲኖር መርዳት ስለሆነ ራስን ለወንጌል አገልግሎት አሳልፎ መስጠት ያስፈልጋል” በማለት አሳስበዋል።

አንዱ ሌላውን መቀበል ፣ መደማመጥ እና መቀራረብ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም የወንጌል አገልግሎት ጥሪን በማበረታታት ላይ ለሚገኝ ማኅበር አባላት ያስተላለፉትን መልዕክት ሲደመድሙ፣ የሚሲዮናዊነት መንፈስ በየጊዜው መታደስ እንደሚገባ ተናግረው፣ ይህ መንፈስ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በኅብረተሰቡ መካከል ሊኖር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ይህም የወንጌል ደስታን ወደ ሌሎች ለማስተላለፍ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል። በተጨማሪም በዚህ መንገድ ተልዕኮውን ወደፊት በማራመድ፣ አንዱ ሌላውን መቀበል ፣ መደማመጥ እና መቀራረብ እንደሚቻል አስረድተዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም የማኅበሩ አባላት በሙሉ ሌሎችን ተቀብለው ለመንፈሳዊ ጥሪያቸው እንክብካቤን ለማድረግ ዘወትር ክፍት እና ዝግጁ እንዲሆኑ፣ ጥሪያቸውን በሚገባ ማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች የጸሎት እና የማስተዋል ቦታ እንዲሆኑ፣ ያዘኑትም መጽናናትን የሚያገኙበት ቦታ እንዲሆኑ፣ ወደ እነርሱ የመጣ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ አምላካዊ ጥበብ መታነጽን የሚለማመድበት የመንፈስ ቅዱስ አውደ እንዲሆኑ በመመኘት መልዕክታቸውን ደምድመዋል። 

23 May 2023, 16:22