ፈልግ

2023.05.25 polonia chiesa kempis varsavia lublin majdanek gdansk cracovia majdanek

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በካንሰር ሕመም የሚሰቃዩ የፖላንድ ሕጻናትን አጽናንተዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በካንሰር ሕመም ተይዘው የሚሰቃዩ የፖላንድ ሕጻናትን ሰኞ ግንቦት 21/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው የማጽናኛ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ መልዕክታቸው፣ በሕመም በሚሰቃዩባቸው ጊዜያትም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር ከጎናቸው እንደሆኑ አስታውሷቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ኢየሱስ ክርስቶስ በሕመማች፣ በስቃያችን እና በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ጊዜያትም ተስፋ ሊሰጠን ሁል ጊዜ ከጎናችን ይገኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በፖላንድ ውስጥ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል የሕክምና ዕርዳታን በማግኘት ላይ የሚገኙ 53 የካንሰር ታማሚ ሕጻናትን ሰኞ ግንቦት 21/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ተቀብለው የማበረታቻ እና የማጽናኛ መልዕክታቸውን ሰጥተዋል።

ኢየሱስ ምስክርነትን ይፈልጋል

ታማሚ ሕጻናትን ቫቲካን በሚገኘው ጳውሎስ ስድስተኛ አዳራሽ ውስጥ የተቀበሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ካንሰርን የመሰለ ከባድ ስቃይን ከሚያስከትል ሕመም ጋር መኖር እና ማሸነፍ አስቸጋሪ እንደሆነ በመግለጽ፣ "በሕይወታችን ውስጥ መቀበል በማንችላቸው መከራዎች ውስጥ የምንሆንባቸው ጊዜያት በርካቶች ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ ጊዜ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘወትር ከአጠገባችን ሆኖ “እኔ ከእናንተ ጋር ነኝ” በማለት እንደሚያጽናን ለሕጻናቱ በማስረዳት፣ ሕጻናቱ በቤተ ክርስቲያን እና በዓለም ውስጥ የእግዚአብሔር ፍቅር ሐዋርያ እንዲሆኑ እና ለዚህ ምስክርነት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሚፈልጋቸው በመግለጽ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሕጻናት ያደረጉትን ንግግር ሲደመድሙ እንደተናገሩት፣ ብቻችንን በምንሆንበት ጊዜ እና የተዘነጋን መስሎ በሚታየን ጊዜ ሁሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ እኛ በመቅረብ፣ በተለይም ሕመማችንን መሸከም ሲያቅተን ዘወትር ከጎናችን ሆና እናታዊ ርኅራኄዋን የምትገልጽልን መሆኗን ተናግረዋል።

31 May 2023, 14:31