ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፋጢማ የተገለጸችበት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፋጢማ የተገለጸችበት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ላይ  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ እንደሚገኙ ተነገረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበር ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል ላይ እንደሚገኙ የቅድስት መንበር ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል አስታወቀ። የመግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ፣ ቅዱስነታቸው በፌስቲቫሉ ላይ የሚገኙባቸው ቀናትም ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሆነ ገልጸው፣ ፌስቲቫሉን ከመላው ዓለም የሚመጡ ወጣቶች እንደሚካፈሉት አስረድተዋል። አቶ ማቴዮ አክለውም ቅዱስነታቸው በፖርቱጋል ውስጥ የሚገኝ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ለመጎብኘት ዕቅድ እንዳላቸው ገልጸው፣ ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2017 ዓ. ም. እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በሥፍራው የተገለጸችበት መቶኛ ዓመት መታሰቢያ ክብረ በዓል ላይ መገኘታቸውንም አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፊታችን የሚመጣውን ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ምክንያት በማድረግ ወደ ፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝበን በሚያደርጉት ጉዞ በፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ቆይታ ለማድረግ ማቀዳቸውን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ጽ/ቤት ዳይሬክተር አቶ ማቴዮ ብሩኒ ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ. ም. በሰጡት መግለጫ አረጋግጠዋል። በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀን ላይ እንዲገኙ ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በቀረበላቸው ግብዣ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሐምሌ 26-30/2015 ዓ. ም. ድረስ በሊዝበን በሚያደርጉት ቆይታ የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ማርያም ቤተመቅደስን እንደሚጎበኙ የቫቲካን ቃል አቀባይ አቶ ማቴዮ ብሩን አስታውቀዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የተገኙበት አራተኛ የወጣቶች ፌስቲቫል ነው

በየዓመቱ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ንግደት የሚያደርጉበትን በፖርቱጋል ውስጥ ፋጢማ በሚባል መንደር የሚገኘውን የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተመቅደስ ቅዱስነታቸው ሲጎበኙት የዛሬው ሁለተኛ ጊዜ መሆኑን አቶ ማቴዮ ብሩኒ ገልጸው፣ በወጣቶች ዓለም አቀፍ ፌስቲቫል ላይ ተገኝተው በዓሉን በበላይነት ሲመሩት ለአራተኛ ጊዜ መሆኑን አስረድተዋል። 

በብራዚል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2013 ዓ. ም. ፣ በፖላንድ ክራኮቪያ እንድ እጎርጎሮሳውያኑ በ 2016 ዓ. ም. እና በላቲን አሜሪካዊቷ  አገር ፓናማ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2019 ዓ. ም. ተገኝተው እንደነበር አቶ ማቴዮ ብሩኒ አስታውሰው፣ እንዳለፉት ዓመታት በዚህ ዓመትም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ከሁሉም አህጉራት የተውጣጡ ወጣቶችን የሚያሰባስብ ዝግጅት በፖርቱጋል ዋና ከተማ ሊዝበን እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎሮሮሳውያኑ ጥር 27/2019 በፓናማ እንዳስታወቁት ቀጣዩ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል በ 2022 ዓ. ም. ሊከበር ዕቅድ የተያዘለት ቢሆንም፣ በዓለማችን በተሰራጨው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ለቀጣይ ዓመት መዘዋወሩን ይታወሳል። ለበዓሉ የተመረጠው ጭብጥም፣ በሉቃ. 1፡39 ላይ እንደተጠቀሰው “ማርያም ፈጥና ተነሥታ ሄደች” የሚል እና ማርያም ኤልሳቤጥን እንደጎበኘቻት የሚናገር እንደ ነበር ይታወሳል።  

ከቅዱስነታቸው የቀረበ ግብዣ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ባስተላለፉት አንድ የቪዲዮ መልዕክት፣ በፖርቱጋል መዲና ሊዝበን በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ፌስቲባል ላይ ወጣቶች እንዲገኙ በማለት ጥሪያቸውን ደጋግመው ማቅረባቸው ይታወሳል። ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫልን መሳተፍ አስደሳች ልምድ እንደሚሆን ገልጸው፣ ወጣቶች በበዓሉ ላይ ለመገኘት ተስፋ እንዲያደርጉ እና ይህን በመሰለ በዓል ላይ ሲገኙ ዕድገትን ማሳየት እንደሚችሉ አስረድተዋል። ቅዱነታቸው በማከልም፣ “አናስተውለውም እንጂ በውስጣችን ብዙ ስጦታዎች ይቀራሉ፣ ያገኘናቸው እሴቶችም በውስጣችን ይቀራሉ፣ ከሌሎች አገራት ከመጡ ወጣቶች ጋር የነበረን ግንኙነት፣ የበዓሉ ድባብ እና ሁሉም ነገር በውስጣችን ይሆናል፣ ከሁሉም በላይ የወጣቶችን ጥንካሬ ማየት እንችላለን” ብለው፣ “ቤተ ክርስቲያን የወጣቶች ጥንካሬ ያላት በመሆኗ ወጣቶች ወደ ፊት መጓዝ ያስፈልጋል” በማለት መልዕክት ማስተላለፋቸው ይታወሳል።

23 May 2023, 16:29