ፈልግ

2023.05.29 SS. Papa Francesco - Bambini da diverse Nazioni africane, in occasione della "Giornata per l'Africa"

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የአፍሪካ ሕጻናት የሰላም ልኡካን እንዲሆኑ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየዓመቱ የሚከበረውን የአፍሪካ ቀንን ምክንያት በማድረግ 1,500 የሚሆኑ አፍሪካውያን ሕፃናትን በቫቲካን ተቀብለው ንግግር አድርገውላቸዋል። በወላጆቻቸው እና በየአምባሳደሮቻቸው በመታጀብ ግንቦት 21/2015 ዓ. ም. ወደ ቫቲካን ለመጡት ሕጻናት ባሳተላለፉት መልዕክት፥ በአገራቸው ሰላም እንዲሰፍን እና የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንዲኖራቸው ያላቸን ሕልም እንዳያቋርጡ በማበራታታት፣ የሰው ልጅ ዛሬ በከባድ አደጋ ውስጥ እንደሚገኝ በመግለጽ ሕጻናቱ ለሰላም እንዲቆሙ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ሕጻናቱ በመጡባቸው አገራት ውስጥ ሙስና፣ ብልሹ አስተዳደር፣ ስደት፣ ሽብርተኝነት እና የአየር ንብረት ለውጥ ቀውሶች መኖራቸውን አስታውሰው፣ ልጆቹ አንዳንድ ጊዜ አቅመ ቢስነት እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ቢኖራቸውም፣ ወጣቶች በመሆናቸው እና ብዙ ችሎታዎችን በውስጣችሁ የተሸከሙ በመሆናቸው ትልቅ ሕልማቸውን እንዲከተሉ በማለት አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ የግጭት እና የጦርነት ሰለባ የሆኑ ሕፃናት ወታደሮች የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው ቅርበትን እና ጓደኝነትን ሊያሳዩዋቸው እንደሚገባም ምክራቸውን ሰጥተዋል።

ወጣቶች ብልሹ አስተዳደርን እና ሙስናን በመቃወም፣ ከሽብርተኝነት ይልቅ ተሰጥኦዋቸውን በማሳደግ፣ ከማግለል ይልቅ ወዳጅነትን፣ ከጦርነት እና ከግጭት ይልቅ ሰላምን በመመኘት ስብዕናችንን አደጋ ላይ የሚጥሉ ግጭቶችን መቃወም እንደሚገባ አሳስበዋል። “አቅመ ቢስነት ሲሰማችሁ እንኳን ተስፋን አትቁረጡ” ያሉት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ወጣቶቹ ትልቅ ሕልማቸውን እንዲከተሉ በመንገር፣ የአፍሪካ ቀንን ምክንያት በማድረግ ከሁሉም የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ከ1,500 በላይ ሕፃናትን ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው ጳውሎስ 6ኛ አዳራሽ  ውስጥ ግንቦት 21/2015 ዓ. ም. ተቀብለው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ የአፍሪካ ቀን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ግንቦት 25/1963 ዓ. ም. የአፍሪካ ኅብረት የተመሠረተበት ዓመታዊ መታሰቢያ ዕለት መሆኑ ይታወቃል።

"ከሌሎች የተለዩ" መሆን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለሕጻናቱ ባደረጉት ንግግር በወላጆቻቸው እና በአምባሳደሮቻቸው ታጅበው መምጣታቸው እንዳስደሰታቸው ከተናገሩ በኋላ፣ ሕጻናቱ የበለፀገ የባሕል ልዩነት የሚታይባቸው መሆናቸውንም በመግለጽ፣ ዕለቱ መላው የአፍሪካ አህጉር ለነጻነት፣ ለልማት፣ ለኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲሁም የአፍሪካን ባሕላዊ ቅርሶች ለማሳደግ እና ለማስፋፋት የተደረገውን ጥረት እንደሚወክሉ አስታውሰዋል። በዚህም የተነሳ ከሌሎች ተለይተው ለለጋስነት፣ ለአገልግሎት፣ ለልብ ንጽህና፣ ለድፍረት፣ ለይቅር ባይነት፣ ለፍትህና ለጋራ ጥቅም የሚደረገውን ጥረት በመቀላቀል፣ ድሆችን ለመውደድ እና ማኅበራዊ ወዳጅነትን ለመመስከር ድፍረት እንዲኖራቸው ሕጻናቱን ጋብዘዋል።

የአካባቢ እና የውስጥ ሰላምን መለማመድ

“ከሕይወት ትልቁ ፈተናዎች መካከል አንዱ ለሰላም የሚደረግ ትግል” እንደሆነ የተናገሩት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የሰው ልጅ በአደጋ ውስጥ እንዳለ እና በአስቸጋሪ ጊዜያት ውስጥ እንደሚገኝ ገልጸው፣ በዚህ ወቅት በጦርነት ውስጥ የምትገኝ ዩክሬይን ብቻ ሳትሆን በአፍሪካ፣ በእስያ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ዓመታትን ያስቆጠሩ ግጭቶች እና ክፍፍሎች መኖራቸው በከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንድንገኝ አድርገውናል" በማለት አስጠንቅቀው፣ ሕጻናቱ የሰላም አምባሳደሮች በመሆናቸው እና መላው ዓለም የፍቅርን፣ አብሮ የመኖርን፣ የወንድማማችነትን እና የመተሳሰብን ውበት መልሶ እንዲያገኝ የአካባቢ እና የውስጥ ሰላምን እንዲለማመዱ አሳስበዋል።

ፈተናዎች ሲያጋጥሙ ተስፋ መቁረጥ አይገባም

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያለፈው ጥር እና የካቲት ወር ወደ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና ደቡብ ሱዳን ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የተነገሯቸውን ቃላት በማስታወስ፣ ውድ የአፍሪካ ምድርን እያጋጠማት ያለውን ትልቅ ፈተና በመመልከት፣ የአፍሪካ ፈተናዎች “ሽብርተኝነት፣ ብልሹ አስተዳደር፣ ሙስና፣ ከፍተኛ የወጣቶች ሥራ አጥነት፣ ስደት፣ ማኅበረሰባዊ ግጭቶች፣ “የአየር ንብረት ለውጥ እና የምግብ እጥረት ናቸው” በማለት ጠቅሰው፣ እንደነዚህ ያሉ አስደንጋጭ አውዶች በሕጻናት ውስጥ አቅመ ቢስነትን እና ተስፋ የመቁረጥ ስሜትን በመፍጠር፣ መጪው ጊዜ የጨለማ እና ተስፋ የሌለበት አስመስለው ሊያቀርቡ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ፣ ሕጻናቱ ወይም ወጣቶቹ በውስጣቸው ብዙ ተሰጥኦዎችን የተሸከሙ፣ ትላልቅ ምኞቶችን ማዳበር የሚችሉ እና ትላልቅ ሕልሞች ያሏቸው በመሆኑ፣ እነዚያን ሕልሞችን እንዲከተሉ በማሳሰብ፣ በአዳራሹ የተገኙት ሕጻናት ተስፋ ሳይቆርጡ “ፍፁም የሆነው ህልማቸው እና ጥሪያቸው ተቀብረው እንዲቀሩ አታድርጉ” በማለት መክረዋል።

የጦርነት ሰለባ የሆኑ ሕፃናት ወታደሮች

“አፍሪካ ካሏት ሃብቶች መካከል አንዱ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ወጣቶች ናቸው” በማለት የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ የአፍሪካ ወጣቶች ለትምህርት ባላቸው ቁርጠኝነት ለኅብረተሰቡ ሰብዓዊ እና ሁለንተናዊ ዕድገት አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ፣ የሁሉም ዓይነት ግጭቶች ሰለባ የሚሆኑ ሕፃናት ወታደሮችን በማስታወስ፣ የሚደርሱባቸውን አሳዛኝ ክስተቶችን በማውገዝ፣ የመረሳት እና የመገለል ስሜት እንዳይሰማቸው ጓደኝነትን እና መቀራረብን መፍጠር እንደሚገባ መክረዋል።

አረጋውያንን መደገፍ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፣ ከዚህ በፊትም ከአዲሱ ትውልድ ጋር ውይይት እንደሚገባ የተናገሩትን ጠቃሚ ምክረ ሃሳባቸውን ዛሬም በመድገም፣ ወጣቶች በአረጋውያን  ምክር እና ምስክርነት ራሳቸውን እንዲያንጹ በማሳሰብ፣ ከአረጋውያን፣ ከአያቶቻችን እና ከእኛ አስቀድመው ከነበሩት ሰዎች ጋር የሚደረግ ውይይት ወደፊት ለመራመድ እንደሚያስችለን በመግለጽ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

31 May 2023, 14:25