ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ ጂርጂያ ሜሎኒ እና ከተወሰኑ ሕጻናት ጋር  ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ከጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ ጂርጂያ ሜሎኒ እና ከተወሰኑ ሕጻናት ጋር   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ቤተሰብ የሕብረተሰብ መጭው ጊዜ ዕጣ ፈንታ መሆኑን አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን አዲስ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር መቀነስን በማስመልከት ግንቦት 4/2015 ዓ. ም. በሮም ለተካሄደው ጉባኤ መልዕክት አስተላልፈዋል። የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ችግርን ለመፍታት እና ቤተሰቦችን ለመደገፍ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ የነፃ ገበያ ሥርዓት ወጣቶች ትዳር እንዳይመሠርቱ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ እንደ ጣሊያን ያሉ አገራት የሕዝብ ቁጥር መቀነስን ለመቀልበስ፣ በተለይም ሴቶች የበለጠ ድጋፍ እና ደኅንነት ይፈልጋሉ በማለት ዓርብ ግንቦት 4/2015 ዓ. ም. በሮም ለተካሄደው ጉባኤ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ወይዘሮ ጂርጂያ ሜሎኒም በተሳተፉበት እና በአገሪቱ ለሦስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው ጠቅላላ የሕዝብ ሥነ ተዋልዶን አስመልክቶ ለተዘጋጀው ጉባኤ ቅዱስነታቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የወሊድ መጠን ጉዳይ ለኅብረተሰባችን የወደፊት ሕይወት ወሳኝ እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስገንዝበዋል። "በእርግጥም የልጆች መወለድ የአንድን ሕዝብ ተስፋ ለመለካት ዋና ማሳያ ነው" ብለው፣ ጥቂት ሕጻናት የሚወለዱ ከሆነው የወደ ፊት ተስፋም ትንሽ ይሆናል" በማለት አስረድተዋል።

ጣሊያንን ያጋጠማት የሥነ-ሕዝብ ቀውስ

በጣሊያን የሕዝብ መጠን ከዓመታት ወዲህ እየቀነሰ መሆኑ ሲነገር፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. አዲስ የተወለዱት ሕጻናት ቁጥር 393,000 ብቻ ሲሆን፣ በተለይም በማኅበራዊ ደኅንነት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መዘዞችን ማስከተሉ ተመልክቷ። ይህ መረጃ የሚያመለክተው ጦርነቶችን፣ ወረርሽኞችን፣ የጅምላ መፈናቀልን እና የአየር ንብረትን ቀውስ ለማጉላት አስተዋፅዖ በማበርከት በወጣቶች ዘንድ ስጋት መፍጠሩን ገልጸዋል።

ቤተሰብን መገንባት ሁሉም ሰው የሚያውቀው እና የሚደግፈው የጋራ እሴት መሆኑ ቀርቶ

በተለይ ለሴቶች ከባድ ፈተና ሆኗል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ሴቶች ቤተሰብን መመሥረት ከባድ ፈተና በሆነበት ማኅበራዊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ፣ የተረጋጋ እና አስተማማኝ ሥራ የማግኘት ችግር፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር እና በቂ ያልሆነ ደመወዝ ከፈተናዎቹ መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ ገልጸዋል። በዚህ ዐውድ ውስጥ በተለይ ወጣት ሴቶች ከሙያቸው እና እናት ከመሆን መካከል አንዱን ለመምረጥ የተገደዱ መሆኑን ቅዱስነታቸው አምነዋል።

ቤተሰብ የችግሩ አካል ሳይሆን የመፍትሄው አካል ነው

እነዚህ ችግሮች በሙሉ የፖለቲካ ባለስልጣናትን እንደሚፈታተኑ፣ ነፃ ገበያው አስፈላጊው የማስተካከያ እርምጃዎች ከሌለው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ ሁኔታዎችን እንደሚፈጥር እና በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ አለመመጣጠንን እንደሚያስከትል አስረድተዋል። አንድ ሰው ብቻውን ችግሮችን ማሸነፍ እንደማይችል የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ከችግሩ ሁላችንም በአንድነት እንወጣለን ካልሆነ ሁላችን አብረን ችግር ውስጥ እንወድቃለን በማለት አስረድተዋል።

ስለሆነም "ቤተሰብ የችግሩ አካል ሳይሆን የመፍትሄው አካል" መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ችግርን ለመፍታት የጋራ ጥረት እና የወደ ፊት ዕጣ ፈንታን ታሳቢ ያደረጉ አስቸኳይ ፖሊሲዎችን ማውጣት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም “ቤተሰብ የመመሥረት ህልማቸውን እውን ለማድረግ የሚታገሉ በርካታ ወጣቶች የፍላጎት ደረጃቸውን ዝቅ በማድረግ ገንዘብ ለማግኘት፣ ሥራን ለመፈለግ ከቦታ ቦታ የሚጓዙ፣ የመዝናኛ ጊዜን በመጠበቅ ላይ የሚገኙ ወጣቶች መኖራቸውን በቅንነት መቀበል አንችልም” ብለው፣ ርዕዮተ ዓለማዊ መሰናክሎችን እና አቋሞችን ወደ ጎን በማለት ችግሩን በጋራ መጋፈጥ አለብን ብለዋል።

ሕጻናትን እና ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም ሕፃናትን እና ስደተኞችን በመቀበል መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት በማጉላት፣ “የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች” እንደሆኑ ገልጸው፣ “በኅብረተሰቡ ውስጥ ምን ያህል ደስታ እንዳለ ያሳየናል” ብለዋል። “ደስተኛ ማኅበረሰብ በተፈጥሮ የማደግ እና የመዋሃድ ፍላጎትን ሲያዳብር፣ ደስተኛ ያልሆነ ኅብረተሰብ ግን በማንኛውም ወጪ ራሱን ብቻ ለመከላከል የሚጥሩ ግለሰቦች ድምር ሆኖ ይቀራል" በማለት ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

ተስፋን የመሰነቅ ጉዳይ ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የወሊድ መጠን ፈተና የተስፋ ጉዳይ ነው” ብለው፣ የወሊድ መጠን መጨመር የማይሆን ሕልም ወይም ስሜት ሳይሆን፣ ነገር ግን ሁሉም ሰው ለበጎነት ባለው ቁርጠኝነት የሚታገዝ ተጨባጭ ተስፋ ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

“ስለዚህ ተስፋን መመገብ ማኅበራዊ፣ ምሁራዊ፣ ጥበባዊ እና ፖለቲካዊ ተግባር እንደሆነ ገልጸው፣ ክህሎትን እና ሃብትን ለጋራ ጥቅም አገልግሎት በማዋል መልካም የወደ ፊት ሕይወትን መጠበቅ እንደሚገባ አደራ ብለው፣ በተስፋ ለውጥ እና የተሻለ ጊዜ እንደሚያመጣ ተናግረዋል። የሕዝብ ቁጥር መጨመር ታላቅ ተስፋ እንዲኖር ዕድል የሚከፍት በመሆኑ ለችግሩ መፍትሄን ለመፈለግ ተስፋ እናድርግ ብለው፣ "የልደት መጠን ማደስ ማለት ወጣቶችን እና ሕይወታቸውን የሚጎዱ ማኅበራዊ መገለልን መጠገን ማለት ነው" በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መልዕክታቸውን አጠቃለዋል።

13 May 2023, 17:02