ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ 2ኛ ከ10 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ 2ኛ ከ10 ዓመት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙበት  

ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እና ብጹዕ ወቅዱስ ሺኖዳ 3ኛ የተገናኙበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ሊከበር ነው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ግንቦት 2/2015 ዓ. ም. የሚያቀርቡትን ሳምንታዊ የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ የሚካፈሉት መሆኑን የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ 2ኛ ቀጥሎ ባሉት ቀናትም ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር በኅብረት ሆነው እንደሚጸልዩ እንዲሁም ፓትሪያርኩ በሮም ከተማ ውስጥ ከሚገኙ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ እሁድ ግንቦት 6/2015 ዓ. ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያሳርጉ የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በቲውተር ማኅበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ ባሠፈረው መልዕክቱ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የአሌሳንድሪያው ጳጳስ እና የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ ዳግማዊ የስድስት ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማካሄድ ግንቦት 1/2015 ዓ. ም. ወደ ሮም መጥተዋል። የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በመልዕክቱ ፓትሪያርኩ ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው ግንቦት 2 እና 3 የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የነበሩት ብጹዕ ወቅዱስ ሺኖዳ 3ኛ ግንቦት 2/1965 ዓ. ም. ከቀድሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ጋር የተገናኙበትን 50ኛ ዓመት በጸሎት እንደሚያስታውሱት አስታውቋል።

የብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ሐዋርያዊ ጉብኝት መርሃ ግብር እንዳመለከተው፣ ፓትሪያርኩ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በየሳምንቱ ረቡዕ የሚያቀርቡት የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ግንቦት 2/2015 ዓ. ም. ከመካፈላቸው በተጨማሪ ሐሙስ ግንቦት 3/2015 ዓ. ም. ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር በግል ተገናኝተው የጋራ ጸሎት ካቀርቡ በኋላ በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን እንደሚጎኙ ታውቋል። ፓትርያርኩ ቀጥለውም እሑድ ግንቦት 6/2015 ዓ. ም. በሮም ከሚኖሩ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን ጋር በቅዱስ ዮሐንስ ዘላቴራን ባዚሊካ ውስጥ የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት የሚያሳርጉ መሆኑን መርሃ ግብሩ አክሎ አስታውቋል።

በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ባልደረባ የሆኑት አባ ሃያሲንት ዴስቲቬል በሚያዝያ ወር ለቫቲካን ሚዲያ በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ ታዋድሮስ 2ኛ በቫቲካን ውስጥ የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለክርስቲያኖች አንድነት እና የኅብረት ጉዞ ወሳኝ ምዕራፍ እንደሚሆን ተናግረው እንደነበር ይታወሳል።

አባ ዴስቲቬል በተጨማሪም የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ከቀድሞ የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትሪያርክ የነበሩት ሺኖዳ ሦስተኛ ጋር ግንቦት 2/1965 ዓ. ም. የተፈረሙትን የጋራ መግለጫ አስታውሰው፣ የጋራ መግለጫው "ከሌሎች የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ጋር ለሚደረጉት ተመሳሳይ ስምምነቶች አርአያ በመሆን ለመጀመሪያዎቹ ሦስት የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች እውቅናን የሰጡበት እንደነበር ገልጸዋል። ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ 2ኛ በቫቲካን የሚያደርጉት የዛሬው ሐዋርያዊ ጉብኝት ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ለመጀመሪያ የተገናኙበትን 10ኛ ዓመት የሚያስታውስ መሆኑንም አባ ዴስቲቬል መናገራቸው ይታወሳል።

ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ከር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ጋር ሆነው በኅብረት የሚያቀርቡት ጸሎት  በልዩ ልዩ የክርስትና ቤተ እምነቶች ውስጥ ደማቸውን ያፈሰሱ የበርካታ ሰማዕታት መታሰቢያ እንደሆነ፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስም ይህን የሰማዕታቱን ደም የአንድነት ዘር እንደሆነ የሚቆጥሩት መሆኑን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘወትር እንደሚናገሩት፣ ሰማዕታት ቀድሞውኑ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ መሰብሰባቸውን፣ የተገደሉበት ምክንያትም ካቶሊክ፣ ኦርቶዶክስ ወይም ፕሮቴስታንት ስለሆኑ ሳይሆን ክርስቲያን በመሆናቸው እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሉ መከራን በመቀበል በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በክብር መሰብሰባቸውን ገልጸዋል እንደነበር ይታወሳል። 

የግብጽ ኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ጉልህ የሆኑ እውነታዎች ከሚገለጹባቸው አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ እንደሆነች የቅድስት መንበር ጽሕፈት ቤት በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ ላይ ባሠፈረው መልዕክቱ አስታውቆ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአገሪቱ ክርስቲያን ማኅበረሰብ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት እንደቆየ አስታውሷል። በቅድስት መንበር የክርስቲያኖች ሕብረት ማጠናከሪያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትም በበኩሉ ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ በቫቲካን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት፣ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የቆየውን ግንኙነት የሚያስታውስ እንዲሁም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ከብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ሺኖዳ 3ኛ ጋር ታሪካዊ ስብሰባ (1965-2015 ዓ. ም.) የተደረገበት 50ኛ ዓመት መታሰቢያን የሚገልጽ መጽሐፍ አሳትሞ ይፋ ማድረጉ ታውቋል።

ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቱ በድረ ገጹ እንዳስነበበው፣ በቫቲካን አሳታሚ ድርጅት ያሳተመው አዲሱ እና ሦስተኛው ጥራዝ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ጀምሮ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እና በግብጽ የኮፕት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል ያለውን መቀራረብ የሚገልጹ ዋና ዋና ሰነዶችን የያዘ፣ ከዚህ ቀደም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እና ብጹዕ ወቅዱስ ፓትሪያርክ ታዋድሮስ ዳግማዊ ያደረጉትን ግንኙነት ለመግለጽ የጻፉትን መልዕክት በመግቢያነት የያዘ መሆኑን ገልጿል።

09 May 2023, 16:59