ፈልግ

የ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” ዓለም አቀፍ ጉባኤ የ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” ዓለም አቀፍ ጉባኤ   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እያንዳንዱ ሰው በስብዕናው መከበር እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከተመሠረተ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” የተሰኘ ጳጳሳዊ ፉውንዴሽን ባዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ መዝጊያ ላይ ተገኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ከተሞችን የሥነ-ምህዳር እና የትምህርት ማዕከላት በማድረግ ከግንቦት 15-17/2015 ዓ. ም. በተካሄደው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ በላቲን አሜሪካ እና በአውሮፓ የሚገኙ የ50 ከተሞች ከንቲባዎች ተሳትፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ለጉባኤው አባላት ባሰሙት ንግግር የተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በአርጄንቲና ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ የሚቻልበትን ዕድል ካለ፣ የብዙዎችን ሕይወትን እያጠፋ ስለሚገኝ የጉልበተኝነት ዝንባሌ፣ እያንዳንዱ ሰው በስብዕናው መከበር እንደሚገባ፣ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ በማይችሉ በርካታ ሕፃናት ላይ ሊደርስ በሚችል አደጋ፣ በተለይ በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶችን እያጠቃ ያለ የብልግና ሥዕሎች እና "የፍቅር ንግድ" መስፋፋት የሚሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከላቲን አሜሪካ እና አውሮፓ ከተሞች ከመጡት ከንቲባዎች እና ወጣቶች ጋር ውይይት ያደረጉባቸው ርዕሠ ጉዳዮች ነበሩ።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከላቲን አሜሪካ እና አውሮፓ አገራት ከመጡ የ“ስኮላስ ኦኩራንቴስ” ጳጳሳዊ ፉንስዴሽን አባላት በኩል ለቀረቡላቸው ጥያቄውች ምላሽ ሰጥተዋል። “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” የተባለ አውታረ መረብ አርጄንቲና ውስጥ ለታዩት ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ባሕላዊ ምላሾችን ለመስጠት በወቅቱ የቦይነስ አይሬስ ሊቀ ጳጳስ በነበሩት በአቡነ ጆርጅ ማርዮ በርጎሊዮ፣ ባሁኑ ስማቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዕርዳታ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2001 ዓ. ም. መጀመሩ ይታወሳል።  “ስኮላስ ኦከርንቴስ” እንደ ጳጳሳዊ ፋውንዴሽን የተመሠረተበት አሥረኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ “ከተሞች የሥነ-ምህዳር እና የትምህርት ማዕከላት” በሚል ርዕሥ ባዘጋጀው የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ከላቲን አሜሪካ እና አውሮፓ አገራት ከተሞች የመጡ 50 የከተማ ከንቲባዎች ተካፍለዋል። ሮም በሚገኝ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ተቋም ውስጥ በተዘጋጀው ጉባኤ መዝጊያ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተገኙ ሲሆን፣ በጉባኤው ሰፊ ውይይቶች ከመደረጋቸው በላይ ፣ ዜማዎች፣ የቪዲዮ ፊልሞች፣ የሰላምታ እና የስጦታ ልውውጦች ተደርገዋል።

የትምህርት አንገብጋቢነት

ቅዱስነታቸው በቅርብ ወደ ትውልድ አገራቸው አርጄንቲና ሄደው ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ዕቅድ እንዳለ ተጠይቀው ሲመልሱ፣ በሚቀጥለው ዓመት በአርጄንቲና ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ሃሳብ እዳላቸው ገልጸዋል። ስለ ወቅታዊው የትምህርት አንገብጋቢነት እና ትምህርትን በማዳረስ ሥራ ላይ የሚሠራ “ግሎባል ኮምፓክት” አስፈላጊነትን በማስመልከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ዛሬ እጅግ በርካታ ወጣቶች ጥራት ያለውን ትምህርት የማግኘት ዕድል እንደሌላቸው ገልጸው፣ በትምህርት ቤቶች የጾታ ትምህርት ካለመኖሩ የተናሳ ፍቅር ወደ ንግድ እየተለወጥ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ፍቅር ለገበያ መቅረብ እንደሌለበት እና “ወጣቶችንም ለዚህ ተግባር መዋል የለባቸውም” በማለት ተናግሯል። "ወጣቶችን ማስተማር የወላጆች እና የኅብረተሰቡ አጠቃላይ ግዴታ ነው" ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ያልቻሉ ሕጻናት ወደ ፊት የኅብረተሰቡ ሸክም እንደሚሆኑ ጠቁመው፣ በተለይ በጉርምስና የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን እያጠቃ የሚገኝ የብልግና ሥዕሎች እና "የፍቅር ንግድ" መስፋፋትን በማስታወስ፣ በዚህ ርዕሥ ላይ ትኩረት በማድረግ ሃላፊነትን መውሰድ ያለባቸው ትምህርት ቤቶች እና መምህራን እንደሆኑ ገልጸው፣ በጉባኤው ላይ የተገኙትም ይህንን ቃል ኪዳን እንዲፈጽሙ አሳስበዋል።

ለትክክለኛ ማንነት ክብር መስጠት

ጉባኤውን በሥፍራው ተገኝተው ወይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ከሩቅ ሆነው ከሚከታተሉት ሰዎች በኩል፣ ጭፍን ጥላቻን፣ ዘረኝነትን እና ጉልበተኝነትን በማስመልከት ተጠይቀው ቅዱስነታቸው ምላሽ ሰጥተዋል። ጉልበተኝነት ከሁሉም በላይ "እጅግ አሳሳቢ እና ሕይወትን የሚያጠፋ ተግባር ነው” በማለት ያስረዱት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ "እያንዳንዱ ወንድ ወይም እያንዳንዷ ሴት 'እውነተኛ ማንነትን' የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸው ገልጸው፣ እራሳቸውን የመሆን እና የመከበር መብት አላቸው" ብለዋል።

ዓለምን እያስጨነቁ ያሉ ቀውሶችን ሰፋ አድረገው በመመልከት የኮቪድ-19 ወረርሽ በጣም አስፈሪ በሆነባቸው ጊዜያት እንደተናገሩት ሁሉ፣ ከችግር ለመውጣት ከፈለጉ አስቀድሞ ችግሩን ለይቶ ማወቅ እንደሚገባ፣ በማኅበርዊ ሕይወት ውስጥ አንድ ሰው ብቻውን ከችግር መውጣት እንደይችል ገልጸው፣ ከችግር በኋላ ሕይወት ተመሳሳይ እንደማይሆን፣ የተሻለ ወይም ካልሆነ የከፋ እንደሚሆን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አስረድተዋል።

“የማራዶና ማለያ”

በጉባኤው መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከቀረቡት በርካታ ስጦታዎች መካከል ከሸክላ የተሠራ የሕፃኑ ኢየሱስ ክርስቶስ ምስል፣ ቲሸርቶች፣ ሥዕሎች፣ ቅርጫቶች፣ በእጅ የተሠሩ ሌሎች ምርቶች እና ጣሊያን ውስጥ የናፖሊ እግር ኳስ ቡድን ተጫዋች የነበረ የአርማንዶ ማራዶና 10 ቁጥር  ማለያ ሲሆን፣ የቡድኑ ፕሬዝደንት ለቅዱስነታቸው ባሰሙት ንግግር፣ የቡድናቸው ጠንካራ እና ዝነኛ ተጫዋች የነበረው የአርማንዶ ማራዶና 10 ቁጥርን በማስታወስ፣ በዓለም ላይ የሚታዩ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችን እንዲረቱ" በማለት ጠይቀዋል።

በቦይነስ አይረስ የነበሩ አያቶችን አስታውሰዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ብዙውን ጊዜ በሚያነሱት በአረጋውያን ጭብጥ ላይ ላይ በማሰላሰል እንደተናገሩት፣ በአርጄንቲና ቦይነስ አይረስ ከተማ የነበሩ አያቶቻቸውን በማስታወስ “እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አያቶቻቸውን በሕይወት የማግኘት ጸጋ እንደ ነበራቸው ገልጸው፣ የመጀመሪያ አያታቸው ሲያርፉ ዕድሜአቸው 16 ዓመት እንደነበር እና ሌላኛው አያታቸው ያረፉትም ጳጳስ ከሆኑ በኋላ እንደነበር አስታውሰዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም አያቶቻቸው ብዙ የቤተሰብ አባላትን በማፍራት እንደረዱ አስታውሰው፣ በተጨማሪም ቋንቋቸውን እና እሴቶቻቸውን እንዳስተማሯቸው ተናግሯል።

የዘር ሐረግ አስፈላጊነት

በ 86 ዓመት ዕድሜአቸውም እነዚያን ወርቃማ ጊዜያትን ሳይረሱ የሚያስታውሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ወደ ዘር ሐረግ የመመለስ ስሜት ሁልጊዜ ይኖራል” ብለው፣ አንድ ማኅበረሰብ የሚበላሸው በሥሩ እና በግንዱ መካከል መለያየት ሲፈጠር እንደሆነ፣ ጭማቂውን ከሥሩ ካልወሰድን እንደምንደርቅ ገልጸው፣ በትንቢተ ኢዩኤል ምዕ. 2:28 ላይ “ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፤ ሽማግሌዎቻችሁም ህልምን ያልማሉ፤ ወጣቶቻችሁም ራዕይን ያያሉ” የሚለውን በመጥቀስ፣ ይህን ማድረግ የሚችሉት በመካከላቸው ግንኙነት ካለ ብቻ ነው” በማለት አስረድተዋል።

አረጋውያንን አትርሷቸው!

አርጀንቲና ውስጥ በነበሩ ጊዜ አረጋውያንን ሲጎበኟቸው የሰሟቸውን ታሪኮች ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በማኅበረሰቡ መካከል አረጋውያን ተረስተው መቅረት እንደሌለባቸው፣ “በውስጡ ያለውን ዝምድና ተቀብሎ በአግባቡ የማያስተናግድ ማኅበረሰብ ርዕዮተ-ዓለማዊ ከመሆን በተጨማሪ ቡድናዊነትን ያስፋፋል” በማለት አስጠንቅቀዋል።

“አዴላንቴ” የክብር ዲፕሎማ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጉባኤው ላይ ለተገኙት ወጣቶች እና መላው የ “ስኮላስ” አውታረ መረብ አባላት ከፍተኛ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ትምህርት ቤት የክብር ዲፕሎማን ከመስጠታቸው በፊት ባስተላለፉት መልዕክት፣ "ይህ የእንቅስቃሴው መጨረሻ ሳይሆን አዲስ ጅምር ስለሆነ በርትታችሁ ወደ ፊት መጓዝ ያስፈልጋል" ብለዋል። 

27 May 2023, 17:17