ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ዕለት   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በቻይና መከራን የሚቀበሉ ምዕመናንን እና ካኅናትን በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ግንቦት 16/2015 ዓ. ም. ካቀረቡት ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸው በመቀጠል፣ ዕለቱ በቻይና የምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የምናስታውስበት ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን መሆኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም በሻንጋይ ሼሻን ከተማ በሚገኝ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቲያኖች ረዳት ቤተ መቅደስ ዓመታዊ በዓል የሚከበርበት ዕለት መሆኑንም ተናግረው፣ በዚያች አገር ቅዱስ ወንጌል በሙላት እና በነጻነት እንዲሰበክ፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን ጋር በመሆን እንድንጸልይ ጠይቀው፣ በዚህ ወቅት በጦርነት ምክንያት በመከራ ውስጥ የምትገኝ ዩክሬይንንም በጸሎታችን እንድናስታውሳት አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ሲል በመስቀል ተሰቅሎ መሞቱ እና ከሞት የመነሳቱ ታላቅ ዜና ቻይና ውስጥ በሙላት እና በነጻነት ይሰበክ ዘንድ፣ ይህም በቻይና ለሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናን እና ለመላው የአገሪቱ ሕዝቦችም መልካም ፍሬን እንዲያስገኝ እግዚአብሔርን በጸሎት እንድትለምኑ እጋብዛችኋለሁ” ብለዋል። 

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ግንቦት 16/2015 ዓ. ም. ያቀረቡትን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮን ለመከታተል ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተገኙት በርካታ ምዕመናን ጋር በጣሊያን የሚኖሩ የቻይና ካቶሊክ ምዕመናን ቆሞሳትም ተገኝተዋል። ቅዱነስታቸው በአደባባዩ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ ግንቦት 16 ቀን በቻይና ለምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ጸሎት የሚቀርብበት ዕለት በመሆኑ፣ ምዕመናን በሙሉ በአገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ምዕመናን ጋር በመሆን በጸሎት እንድንደግፋቸው አደራ ብለዋል። “ደስታቸውን” እና “ተስፋቸውን” አብረን እንደምንካፈል ያረጋገጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንዲሁም ባሁኑ ጊዜ በካኅናት እና በምዕመናን ላይ የሚደርስ መከራ እና ስቃይንም መጋራት እንደሚያስፈልግ፣ በቻይና ወንጌል በሙላት እና በነጻነት እንደሚሰበክ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።   

የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በሼሻን (ሻንጋይ)

በቻይና እና በመላው ዓለም በሚገኙ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቁምስናዎች እና ቤተመቅደሶች የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የጸሎት ቀን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ዕለቱ የክርስቲያኖች ረዳት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል ጋር በአንድነት የሚከበር መሆኑን አስታውሰው፣ ቻይና ውስጥ በሼሻን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በድምቀት እንደሚከበር ገልጸዋል።

የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2007 ዓ. ም. ለቻይና ካቶሊክ ምዕመናን በጻፉት ትንቢታዊ መልዕክት፣ በቻይና ሼሻን ውስጥ በሚገኝ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ በታላቅ አክብሮት በሚከበር ዓመታዊ በዓል በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካዊ ምዕመናንም በጸሎት እንዲተባበሩ ለማድረግ ፍላጎት እንደነበራቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ገልጸው፣ “በዚህ አጋጣሚ በቻይና ካሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለንን አንድነት በመግለጽ፣ ደስታቸውን እና ተስፋቸውን ለመካፈል እንደምፈልግ አረጋግጣለሁ” ብለዋል።

ከሚሰቃዩት ጎን መሆን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባሁኑ ወቅት ቻይና ውስጥ መከራና በደል የሚደርስባቸውን ካኅናት እና ምዕመናን ባስታወሱበት ልዩ ጸሎታቸው፣ በአገሪቱ ውስጥ መከራ እና ስቃይ የሚደርስባቸው ካቶሊካዊ ምዕመናን በሙሉ በመላው ዓለም ከምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ጋር ባላቸው ኅብረት እና አንድነት መጽናናትን እና ብርታትን እንደሚያገኙ ገልጸዋል።

ዩክሬይንን በጸሎት ማስታወስ

ተመሳሳይ መጽናናትን ለዩክሬይን በጸሎት የለመኑት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዩክሬይን ውስጥ ጥቃቱ በቀጠለበት ባሁኑ ጊዜ ሰዎች በሞት እና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ እንደሚገኙ አስታውሰዋል። “በዩክሬይን ብዙ ስቃይ አለ" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ጸሎታቸውን ወደ ክርስቲያኖች ረዳት ወደ ሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በማቅረብ፣ “በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ስቃይ የሚደርስባቸውን ሰዎች ሳንዘነጋ ሁላችንም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕርዳታ በጸሎት እንለምን” ብለዋል።

25 May 2023, 16:50