ፈልግ

የ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” ዓለም አቀፍ ጉባኤ የ “ስኮላስ ኦኩራንቴስ” ዓለም አቀፍ ጉባኤ  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ “በሩሲያ እና ዩክሬይን መካከል ሰላም የሚወርደው እርስ በርስ መነጋገር ሲችሉ ነው”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ስደትን፣ ውርጃን እና የምኩስና ሕይወትን የተመለከቱ ርዕሠ ጉዳዮችን በማንሳት ቴሌሙንዶ ከተሰኘ የቴሌቪዢን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በዚህ ቃለ ምልልሳቸው፣ ምዕመናን ዘወትር በጸሎታቸው እንዲያስታውሷቸው ማሳሰባቸውን ተናግረውው፣ የምዕመናን ጸሎት ለካኅናት እና ሐዋርያዊ አባቶች “ጋሻ” እንደሆነ አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል ሰላም ሊረጋገጥ የሚችለው ሁለቱ አገራት ተቀራርበው መነጋገር ከቻል፣ ካልሆነም በሌሎች አገራት በኩል በሚደረግ ጥረት አማካይነት ነው” በማለት አስረድተዋል። ከአንድ ዓመት በላይ በዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርንርት እና ያስከተለውን የሰው ሕይወት እና የንብረት ጥፋትን በማስታወስ፣ ቴሌሙንዶ ከተሰኘ የስፓንኛ ቋንቋ የአሜሪካ ቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ግንቦት 17/2015 ዓ. ም. ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ ሁለቱ አገራት ተቀራርበው የሚያደርጉት ውይይት ለግጭቱ መፍትሄ ሊሆኑ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቴሌሙንዶ ከተሰኘ የአሜሪካ ቴሌቪዢን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት፣ ሮም በሚገኝ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ተቋም ውስጥ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የተገኙ ሃምሳ የላቲን አሜሪካ እና የአውሮፓ ከተሞች ከንቲባዎችን ባገኙበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል። የቴሌቪዥን ጣቢያው ጋዜጠኛ ቫኬይሮ ስብሰባውን ሲመራ ከቆየ በኋላ ስለ ጦርነት፣ ፅንስን ስለ ማስወረድ እና የምንኩስና ሕይወትን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ለቅዱስነታቸው ያቀረበላቸው ሲሆን፣ ቀጥሎም ስለ ጤንነታቸው፣ ትውልድ አገራቸውን ጥለው ስለሚሰደዱት ሰዎች እና እንደ ‘ጋሻ’ የሚያገለግል የምእመናን የጸሎት ድጋፍን በማስመልከት ቃለ ምልልስ አድርጓል።

በቅርቡ ከዩክሬይኑ ፕሬዝዳንት አቶ ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ፥ ከዩክሬይኑ ፕሬዚደንት ዘሌንስኪ በኩል ከፍተኛ ተማጽኖ እንደቀረበላቸው ገልጸው፣ ይህም “ወደ ሩሲያ ለተወሰዱት የዩክሬይን ሕጻናት እንክብካቤን እንዲያደርጉ” የሚል እንደነበር አብራርተዋል። “የዩክሬይን ወቅታዊ ሕመም የሽምግልና ጉዳይ ሳይሆን ወደ ሩሲያ ለተወሰዱት የዩክሬይን ሕጻናት ዕርዳታን ማድረግ እና ሕጻናቱን ወደ ዩክሬን ለመመለስ ጥረት ማድረግ እንደነበር ርዕሠ ሊቅነ ጳጳሳት ገልጸዋል። “በሁለቱ አገራት መካከል ሰላምን ለማምጣት ሩሲያ የያዘቻቸውን ግዛቶች መመለስ አለባት ብለው ያስባሉ?” ተብለው ለተጠየቁት ስመልሱ፥ ይህ ፖለቲካዊ ጉዳይ ነው" በማለት መልሰዋል።

ስደትን በተመለከተ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቃለ ምልልሳቸው የተመለከቱት ሌላው ችግር የስደት ጉዳይ ሲሆን፣ ለዚህም ሕዝብ የሚሰደድባቸው አገሮች ዘላቂ ልማትን የሚያመጡ ውጤታማ ስትራቴጂዎችን ማጎልበት እንደሚያስፈልግ ደጋግመው አሳስበዋል። የአፍሪካ አህጉርን በቅድሚያ በመጥቀስ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፤ አፍሪካን በመርዳት እና የአፍሪካ የስደት ችግር በአፍሪካውያን መፈታት አለበት ብለዋል። በሚያሳዝን መልኩ የአፍሪካ ንቃተ ህሊና የሚነዳው በውጭ አገራት እንደሆነ በመግለጽ፣ “ከውጭ የሚደረግ ድጋፍ የአፍሪካ ችግርን በመቅረፍ እራሷን እንድትችል የሚያደርግ እንጂ ሁልጊዜ ተመጽዋች የሚያደርጋት ሊሆን አይገባም” ብለዋል።ቅዱስነታቸው ከዚህ ጋር በማያያዝ ባለፈው የካቲት ወር የጎበኟትን ደቡብ ሱዳን በማስታወስ፣ የሱዳን ሕዝብ እራሱ በማሳደግ ላይ የሚገኝ አስደናቂ ሕዝብ እደሆነ በመግለጽ ያላቸውንም ወዳጅነት ገልጸዋል።

"የውጭ ኃይላት ኢንዱስትሪዎቻቸውን ቶሎ ብለው በአፍሪካ የሚተክሉት አገራቱን ለማሳደግ ሳይሆን ለመንጠቅ ነው" ያሉት ቅዱስነታቸው፣ “ሁሉንም ባልል፣ ወይም የአገራትን ስም መጥራት ባልፈልግም፣ የአፍሪካ ችግር ሐቀኝነት የጎደለው የፖለቲካ ንቃተ-ህሊና እና አፍሪካ መጠቀሚያ መሆን አለባት” የሚል ያልተለወጥ አስተሳስብ መኖሩን ተናግረዋል። ቀጥለውም ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ለተሰበሰቡት የጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳት ያበረከቱትን “ትንሹ ወንድም” የሚለውን መጽሐፍ የጠቀሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ከትውልድ አገሩ ጊኒ በመሰደድ ወንድሙን ፍለጋ ወደ ስፔን ለመድረስ ባደረገው የሦስት ዓመታት ጎዞ ላይ ባርነት፣ እስር እና ድብደባ እንደደረሰበት እና “ስደት ትንሹ ሞት ነው” በማለት ጋዜጠኛው መገልጹን ጠቅሰዋል።  

ፅንስ ማስወረድ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ፅንስን ማስወረድ እና ያለ ጋብቻ በምንኩስና ሕይወት መኖርን ባካተተው ቃለ ምልልሳቸው በመቀጠል፣ በጽንስ ጥናቶች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን በመጥቀስ “ከተፀነሰ ከአንድ ወር በኋላ በማህፀን ውስጥ የሚገኝ ሕያው ፍጡር" እንደሆነ አስረድተው፣ በሕይወት የሚገኝ ፍጡር ማጥፋት የችግሩ መፍትሄ ሊሆን ይችላል ወይ?” በማለት ጠይቀዋል። 

የካህናት ያለጋብቻ መኖር እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚፈጸመው የሕፃናት ጥቃት ጋር ስላለው ግንኙነት በተመለከተ፣ ስታቲስቲክስን በመጥቀስ በሰጡት ምላሽ፡- “32 በመቶ እና በሌሎች አገራትም 36 በመቶው በሕጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቤተሰብ፣ በአጎት ወይም በአያት፣ በባለትዳሮች ወይም በጎረቤቶች በኩል የሚፈጸም እንደሆነ ገልጸው፣ ከዚያም ባሻገር በስፖርት ሥፍራዎች እና በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንደሆነ በማስረዳት፣ ያለማግባትን ከዚህ ጋር የሚያገናኝ ምንም ነገር የለም” ብለዋል።

የግል ጤና ጉዳይ

የግል ጤናን እና በጉልበታቸው ላይ ያለውን ችግር በተመለከተ በስጡት ምላሽ፣ ከዚህ ቀደም መራመድ እንደሚቸግራቸው እና አሁን መራመድ እንደሚችሉ ገልጸው፣ ባለፈው ጥር ወር ላይ ባጋጠማቸው የሳንባ ሕመም ምክንያት ሆስፒታል ገብተው መውጣታቸውን አስታውሰው፣ ቶሎ ብለው የሕክምና ዕርዳታ ባያገኙ ኖሮ ጉዳዩ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ገልጸዋል። በእያንዳንዱ የአደባባይ ንግግሮች ማጠቃለያ ላይ ምዕመናን እንዲጸልዩላቸው በመጠየቅ እንደሚጨርሱ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ አንዳንድ ሰዎች ለሐዋርያዊ አገልጋዮቻቸው ወይም ለካህናቶቻቸው የሚያቀርቡት ጸሎት ኃይል እንዳለው አይገነዘቡም” ብለው፣ የምእመናን ጸሎት ድጋፍ በመሆን ተአምራትን እንደሚሠራ አስረድተዋል።

በከፍተኛ ጳጳስዊ ጽ/ቤቶች ውስጥ ያመጧቸው ማሻሻያዎች

ባለፉት አሥር ዓመታት የርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ዓመታት ስለተደረጉት ለውጦች ማብራሪያን የሰጡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ እንደ እውነቱ ከሆነ፣ በምርጫው ወቅት ከብጹዓን ካርዲናሎች በኩል ከቀረቡት ጥያቄዎች ሌላ ምንም ያደረጉት ነገር እንደሌለ አስረድተው፣ የቅድስት መንበር የኢኮኖሚ ሥርዓት ማሻሻል፣ አዳዲስ የቫቲካን ሕጎችን ማጽደቅ፣ የቫቲካን ሐዋርያዊ አገልግሎት እና እንክብካቤ ማሳደግ እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሴቶችን ሚና ማሳደግ የሚሉት ርዕሠ ጉዳዮች ከካርዲናሎች በኩል የቀረቡ ሃሳቦች እንደነበሩ አስረድተዋል።

“ወደፊትም ገና ብዙ የሚቀሩ ጉዳዮች እንዳሉ ይሰማኛል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ወደ ፊት በተጓዘን ቁጥር ብዙ መሥራት እንዳለብህ እንገነዘባለን ብለው፣ በእርግጠኝነት ሌላኛው ግብ የቤተ ክኅነትን አምባ ገነንነት ማስቀረት እንደሆነ ገልጸው፣ ሐዋርያዊ እረኛ ከሆኑ ቤተ ክርስቲያንን ዝቅ ብሎ ማገልገል እንደሚገባ ሁልጊዜ ለጳጳሳት፣ ለካህናቶች እና ለራሴም ጭምር እናገራለሁ በማለት ቃለ ምልልሳቸውን ደምድመዋል።

27 May 2023, 17:11