ፈልግ

2023.05.29 Consegna del Premio Paolo VI di Brescia al Presidente della Repubblica Italiana Sergio Mattarella

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት ሴርጆ ማታሬላ የጳውሎስ 6ኛ ዓለም አቀፍ ሽልማት አበረከቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሴርጆ ማታሬላ በሥልጣን ዓመታት ውስጥ ላበረከቷቸው አገልግሎቶች እና ላሳዩት የሃላፊነት ሚና የጳውሎስ 6ኛ ዓለም አቀፍ ሽልማትን በማበርከት ምስጋናን አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ዓመታዊ በዓል ተከብሮ በዋለበት ሰኞ ግንቦት 21/2015 ዓ. ም. ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት ለአቶ ሴርጂዮ ማታሬላ ዓለም አቀፍ ሽልማትን አበርክተዋል። የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ መታሰቢያነት እንዲሆን ተብሎ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1979 ዓ. ም. የተቋቋመው እና ለጣሊያኑ ፕሬዝዳንት አቶ ሴርጂዮ ማታሬላ የተበረከተላቸው ዓለም አቀፍ ሽልማቱ በጥናት ዘርፎች እና በዓለም ዙሪያ ለሃይማኖታዊ ሥራዎች ዕድገት ጉልህ አስተዋጽኦን ላበረከቱት ግለሰቦች ወይም ተቋማት የሚሰጥ ሽልማት እንደሆነ ይታወቃል።

በቫቲካን በሚገኝ የቀሌሜንጦስ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው የሽልማት አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለገኙት እንግዶች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባደረጉት ንግግር፣ የቀድሞ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ በሁለተኛው የቫቲካን ጉባኤ ስኬታማነት ካደረጉት አስተውጽዖ በተጨማሪ ምእመናን በቤተ ክርስቲያን ለሚያበረክቱት ሚና አጽንዖት መስጠታቸውን በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

"ምዕመናን በሚያከናውኗቸው ሥራዎች መካከል አንዱ እና ታዋቂው ፖለቲካ ነው" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ፖለቲካ ከከፍተኛ የበጎ አድራጎት ሥራዎች መካከል አንዱ ነው" በማለት ከገለጹ በኋላ በመቀጠልም “የፖለቲካ እርምጃዎችን እንዴት የበጎ አድራጎት ክፍል ማድረግ እንደሚቻል እና በሌላ በኩልም በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በጎ አድራጎትን እንዴት በተጨባጭ መኖር እንደሚቻል እራሳችንን ልንጠይቅ ይገባል” ብለዋል።

አገልግሎት

“መልሱ ‘አገልግሎት’ በሚለው ቃል ላይ ነው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ቀጥለውም ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ ሕዝባዊ ሥልጣንን የሚለማመዱ ሰዎች ራሳቸውን እንደ አገልጋዮች በመመልከት ወገኖቻቸውን በታማኝነት ለሚያገለግሉበት ከፍተኛ ሥልጣን የበቁ አድርገው መቁጠር አለባቸው” ማለታቸውን አስታውሰዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ሌሎችን ማገልገልና ለሌሎች መሥራት አስቸጋሪ እንደሆነ መናገሩን ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “ለማገልገል የማይኖር በሕይወት አይኖርም” በማለት ሐሳቡን አበክረው ገልጸውታል። ዛሬ ለፕሬዝዳንት ሴርጆ ማታሬላ የተሰጠው ዓለም አቀፍ የጳውሎስ 6ኛ ሽልማት የአገልግሎት ዋጋን እና ክብር የሚገልጽ እንደሆነ አስረድተው፣ “ማገልግለል ከራስ ይልቅ ሌሎችን የሚያስቀድሙበት ታላቅ የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነ አምናለሁ” ብለዋል። ለጣሊያኑ ፕሬዚዳንት ሴርጆ ማታሬላ በቀጥታ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ “በጣሊያን ሕዝብ የተመሰከረላቸው አገልግሎታቸው እውነት እንደሆነ አጽንኦትን ሰጥተው፣ ፕሬዝዳንቱ በጉጉት ሲጠበቅ የነበሩትን የጡረታ መውጫ ይሁንታን ማግኘታቸውን አስታውሰው፣ መንግሥታቸው በሚሰጧቸው አዲስ ሹመት አሁንም አገራቸውን ለማገልገል ፍላጎት ያላቸው መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

ሃላፊነት

አንድ ሰው አገልግሎቱን የተሟላ ለማድረግ የተሰጠውን ኃላፊነት መተግበር እንዳለበት ያሳሰቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፣ “አገልግሎት ከኃላፊነት ጋር አብሮ የሚሄድ ነው” በማለት ተናግረዋል።“ሃላፊነት” የሚለው ቃልም እንደሚያመለክተው፣ በቁርጠኝነት ላይ መመሥረት፣ ሌሎች ሰዎች መልስ እንዲሰጡዋቸው ሳይጠብቁ መልስ የመስጠት ችሎታ ነው” ሲሉ በማብራራት ፕሬዘደንት ሴርጆ ማታሬላ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በቅድሚያ ምሳሌ በመሆን ከዚያም በቃላት መፈጸማቸውን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ “የኃላፊነት ስሜት እና የአገልጋይነት መንፈስ ለቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ የማኅበራዊ ሕይወት ግንባታ መሠረት ነበር" ብለው፣ የአብሮነት እና ማኅበረሰቦችን የመገንባት ትሩፋት ለትውልድ ጥሎ ማለፍ ሕልማቸው እንደ ነበር ገልጸው፣ “በወጣቶች እና አዛውንት ስም ራሴን የምስጋና መሣሪያ በማድረጌ ደስተኛ ነኝ” ብለው ከሁሉም በላይ ለተከታታይ የትኅትና አገልግሎት እና ኃላፊነት ምስክር በመሆኔ ደስታ ይሰማኛል" በማለት፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛም በዚህ ደስ እንደሚሰኙበት በመግለጽ ንግግራቸውንም ሲጠቅሱ፥ “የዘመኑ ሰው አስተማሪዎቹን ከማዳመጥ ይልቅ ምስክሮችን በሙሉ ፈቃድ እንደሚያዳምጥ፤ አስተማሪዎቹን የሚያዳምጥ ከሆነ ምስክሮች ስለሆኑ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። 

 

31 May 2023, 14:18