ፈልግ

ቅዱስነታቸው በሮም ኮንቺሊሲዮኔ መንገድ ላይ በሚገኝ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ እርግዝናን ሲባርኩ ቅዱስነታቸው በሮም ኮንቺሊሲዮኔ መንገድ ላይ በሚገኝ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ እርግዝናን ሲባርኩ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ቤተሰብ ድህነትን እና የሕዝብ ቁጥር መቀነስን መከላከል እንደሚችል ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ታውጆ ዘንድሮ “የሥነ-ሕዝብ አዝማሚያዎች እና ቤተሰቦች” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው “@Pontifex” በሚለው የትዊተር ማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት፣ በሁሉም አገራት ዘንድ ለሕይወት አስፈላጊውን ክብር የሚሰጡ እና ሕይወትን የሚቀበሉ፣ ለቤተሰብ ተስማሚ የሆኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ፖሊሲዎች እንዲኖሩ ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቤተሰብ ቁሳዊ እና መንፈሳዊ ድህነትን ለመዋጋት እንዲሁም የሥነ ሕዝብ አወቃቀር መናጋትን ለመከላከል የሚያስችል ዋነኛ መድኃኒት መሆኑን፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስተባባሪነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1989 ዓ. ም. ተቋቁሞ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1993 ዓ. ም. መከበር ለተጀመረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን ባስተላለፉት መልዕክት ገልጸዋል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ “@Pontifex” በሚለው የትዊተር ማኅበራዊ ሚዲያ ገፃቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት፣ ሁሉም አገራት ቤተሰብን የሚወዱ እና ለሕይወት ክብርን የሚሰጡ ማኅበራዊ፣ ኤኮኖሚያዊ እና ባሕላዊ ፖሊሲዎችን እንዲያራምዱ በማለት አሳስበዋል። 

እ.አ.አ. በ 2022 ዓ. ም. በጣሊያን አዲስ የተወለዱት ሕጻናት ቁጥር 393 ሺህ ብቻ ናቸው 

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘንድሮ ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የቤተሰብ ቀን የተመረጠው መሪ ጭብጥ "የሥነ-ሕዝብ አዝማሚያዎች እና ቤተሰቦች" የሚል እንደሆነ ተመልክቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ወይዘሮ ጂርጂያ ሜሎኒም በተሳተፉበት እና በአገሪቱ ለሦስተኛ ጊዜ ለተዘጋጀው ጠቅላላ የሕዝብ ሥነ ተዋልዶ የቤተሰብ ማኅበራት ጉባኤ ዓርብ ግንቦት 4/2015 ዓ. ም. ባስተላለፉት መልዕክት፣ የወሊድ መጠን ለኅብረተሰባችን የወደፊት ሕይወት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ አስገንዝበዋል። ከዓመታት ወዲህ በጣሊያን የሕዝብ መጠን እየቀነሰ መሆኑ ሲነገር፣ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2022 ዓ. ም. አዲስ የተወለዱት ሕጻናት ቁጥር 393,000 ብቻ እንደነበር፣ በተለይም በማኅበራዊ ደኅንነት ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ኤኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መዘዞችን ማስከተሉ ተመልክቷ። ይህ አዲስ የሚወለዱ ሕጻናት ቁጥር ጣሊያን ከተዋሃደች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ400,000 በታች ሆኖ የተመዘገበ ዝቅተኛው አሃዝ ነው ተብሏል።

ሥነ ተዋልዶ የአንድ አገር ሕዝብ ተስፋ ማሳያ ነው

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው አሃዙ መላው አውሮፓን የሚመለከት የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ውድቀትን የሚያሳስብ እንደሆነ ገልጸዋል። "በእርግጥም የሕጻናት መወለድ የአንድ አገር ሕዝብ ተስፋ የሚለካበት ዋና ማሳያ ነው" ብለው፣ “ጥቂት ሕጻናት የሚወለዱ ከሆነው የወደ ፊት ተስፋም ጥቂት ይሆናል" በማለት አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በዛሬው ዓለም የሚታየው ባሕል ለቤተሰብ ዕድገት "ጠላት" በመሆን ስጋት መፍጠሩን ገልጸው፣ አዲስ ሕይወት ወደ ዓለም መምጣቱን የሚቃወም መሆኑን አስረድተዋል። ሴቶችን የማይመጥኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ማሸነፍ እንደሚገባ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ ሴቶች ቤተሰብን ለመመሥረት ከባድ ፈተና በሆነበት ማኅበራዊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ፣ የተረጋጋ እና አስተማማኝ ሥራ የማግኘት ችግር፣ የቤት ኪራይ ዋጋ መናር እና በቂ ያልሆነ የደመወዝ ክፍያ ከፈተናዎቹ መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ ገልጸው፣ በዚህ ዐውድ ውስጥ በተለይ ወጣት ሴቶች ከሙያቸው እና እናት ከመሆን መካከል አንዱን ለመምረጥ እንደሚገደዱ ቅዱስነታቸው ገልጸዋል። ስለዚህም ለሕዝብ ቁጥር ማደግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ እና አርቆ አሳቢ ፖሊሲዎች እንዲዘረጉ፣ የሕዝብ ቁጥር እንዲያድግ የሚያበረታቱ እና የሥነ ሕዝብ አወቃቀር ችግሮችን ወደ ጎን በማድረግ የልደት መጠን መጨመርን በምስጋና መቀበል እንደሚገባ መክረዋል።

16 May 2023, 16:02