ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወዳጅ ከሆኑት መምህር አብርሐም ስኮርካ ጋር ሲገናኙ  (የማህደር ፎቶ) ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወዳጅ ከሆኑት መምህር አብርሐም ስኮርካ ጋር ሲገናኙ (የማህደር ፎቶ) 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ እምነት እና ሰብዓዊ መብቶች የሚገናኙ መሆናቸውን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በስሎቫኪያ ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ የሥነ መለኮት ፋኩልቲ መምህር ለሆኑት አብርሃም ስኮርካ ግንቦት 2/2015 ዓ. ም. የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት ልከዋል። በስሎቫኪያ ውስጥ በምትገኝ ትርናቫ ዩኒቨርሲቲ የሥነ መለኮት ፋኩልቲ የአይሁድ እምነት መምህር፣ ደራሲ እና የባዮፊዚክስ ሊቅ ለሆኑት አርጀንቲናዊው መምህር አብርሐም ስኮርካ ዩኒቨርስቲው የክብር ዶክትሬት አበርክቶላቸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለመምህር አብርሃም ስኮርካ በተበረከተላቸው የክብር ዶክትሬት ማዕረግ የተሰማቸውን ደስታ በገለጹበት መልዕክታቸው፣ መምህሩ በሃይማኖቶች መካከል በሚደረግ የጋራ ውይይት ላይ ያላቸውን ቁርጠኝነት በማስታወስ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የስሎቫኪያ ከተማ በሆነች ትርናቫ የሚገኝ የኢየሱሳውያን ማኅበር ዩኒቨርሲቲ የሥነ መለኮት ፋኩልቲ ለአይሁድ መምህር አብርሐም ስኮርካ ያበረከተውን የክብር ዶክትሬት ማዕረግ በማስታወስ በላኩት የደስታ መግለጫ መልዕክታቸው መምህሩ በአይሁድ እና በክርስትና እምነቶች መካከል በሚደረጉ የጋራ ውይይቶች ዕድገት፣ በሳይንስ እና በትምህርት መስኮች መቻቻልን ለማስተዋወቅ ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተነበበው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የደስታ መግለጫ መልዕክቱ፣ የቀድሞ ጓደኛቸው መምህር አብርሐም ስኮርካ በ 42 ዓመታት የትምህርት እና አካዳሚያዊ እንቅስቃሴ ውስጥ መልካም ተጽዕኖን በማሳደር፣ እንዲሁም የካቶሊክ እና የፕሮቴስታንት የሃይማኖት ሊቃውንትን በሙሉ አክብረው በመገኘታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በክርስቲያኖች እና በአይሁዶች መካከል ያለው ግንኙነት ፍሬያማ ግንኙነቶችን ፈጥሯል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአይሁድ እምነት መምህር ለሆኑት ለአብርሐም ስኮርካ በላኩት የደስታ መግለጫ መልዕክት፣ ረጅም ጊዜን ባስቆጠረው መልካም ግንኙነት የወዳጅነት እና የጥበብ ስጦታን ማጣጣማቸውን ገልጸው፣ ለዚህም እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ" ብለዋል። ፍሬያማ በሆኑ ውይይቶች እና ጓደኝነቶች፣ እንዲሁም በሃይማኖታዊ ውይይት ውስጥ በማሰላሰል አብረው ያሳለፏቸውን ጊዜያት ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2021 ዓ. ም. በስሎቫኪያ ያደረጉትን የማይረሳ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በማስታወስ በርካታ ካቶሊካዊ ምዕመናን በተገኙበት ብራቲስላቫ ውስጥ ከአይሁድ ማህበረሰብ ጋር በሬቢኔ አደባባይ ያደረጉትን ስብሰባንም አስታውሰዋል። እነዚህ ክስተቶች ፍሬያማ የሆኑ የእርስ በርስ ግንኙነቶች እንዲዳብሩ በር የሚከፍቱ መሆኑን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ የተበረከተላቸው አካዳሚያዊ እውቅና በትርናቫ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከፍተኛ አክብሮት እንደሚሰጠው እና የትርናቫ ከተማ የአይሁድ ሕዝብ የስቃይ ታሪክ ያላት ከተማ መሆኑን አስታውሰዋል። የረጅም ጊዜ ወዳጃቸው የሆኑት መምህር አብርሐም ስኮርካ በስሎቫኪያ ዩኒቨርሲቲ መገኘታቸው ዓለማችን እጅግ የሚፈልገው የአዲሱ ታሪክ ምዕራፍ አድርገው እንደሚመለከቱት ቅዱስነታቸው ገልጸዋል።

እምነትን በእውነት መኖር እና ሰብዓዊ መብቶችን ማክበር

"ለብዙ ዘመናት እምነት ብዙውን ጊዜ ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶችን ለማሳካት ጥቅም ላይ እንደሚውል እና ይህም ሃይማኖታዊ እሴቶች ያላቸውን አድናቆት ለመቀነስ ብቻ ነው" ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በሌላ በኩል የአይሁድ እምነት መምህር አብርሐም ስኮርካ “የሃይማኖትን ባሕል በትክክለኛ መንገድ በመኖር እና ሰብዓዊ መብቶችን በማክበር ግጭት ውስጥ መግባት እንደሌለበት ዘወትር ለማስረዳት መሞከራቸውን ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አክለውም “የእምነት ሰዎች በሁሉም የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን ማስጠበቅ እንደሚችሉ እና እንዳለባቸው ለማሳየት ሞክረዋል” ሲሉ ተናግረዋል። “ሃይማኖታቸው ምንም ይሁን ምን፣ ውይይት ፣ ፍትህ እና በሰላም አብሮ የመኖር ቁርጠኝነት በሁሉም ሰዎች መካከል ያለው ግንኙነት እየጨመረ በመሄድ አስደሳች አጋጣሚዎችን እንደሚፈጥርላቸው ገልጸው፣ ለመምህር አብርሃም ስኮርካ የተበረከተላቸው የክብር ዶክትሬት፣ በአይሁድ እና በክርስትና እምነቶች መካከል በመደረግ ላይ የሚገኘውን መልካም ውይይት በተለየ መንገድ ያጠናክራል” ብለዋል።

11 May 2023, 16:52