ፈልግ

በእንግሊዝ የኖርዊች ከተማ ተወላጅ እማሆይ ጁሊያ በእንግሊዝ የኖርዊች ከተማ ተወላጅ እማሆይ ጁሊያ   (Matt Brown)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ለካቶሊካውያን እና ለአንግሊካውያን ምዕመናን የደስታ መግለጫ መልዕክት ላኩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእንግሊዝ የኖርዊች ከተማ ተወላጅ ለሆነች እማሆይ ጁሊያ የኢየሱስ ክርስቶስ ሕማማት የተገለጠላትን 650ኛ ዓመት መታሰቢያ ለሚያከብሩት የካቶሊክ እና የአንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ነጋዲያን መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእንግሊዝ የኖርዊች ከተማ ተወላጅ የሆነች የእማሆይ ጁሊያ 650ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓልን ምክንያት በማድረግ ዓመቱን በሙሉ በኖርዊች ከተማ ውስጥ በሚገኙት የካቶሊክ እና የአንግሊካን ካቴድራሎች በመሰብሰብ ላይ ለሚገኙት ምዕመናን ዓርብ ግንቦት 4/2015 ዓ. ም. መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው የመታሰቢያ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የአምልኮ ሥነ ሥርዓቶች ላይ ከሚሳተፉት ምዕመናን ጋር በመንፈስ እንደሚተባበሩ አረጋግጠዋል።

የኖርዊች ከተማ ተወላጅ የነበረች እማሆይ ጁሊያ የመካከለኛው ዘመን እንግሊዛዊ እማሆይ ስትሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1373 ዓ. ም. የኢየሱስ ክርስቶስን ሕማማት በተከታታይ በራዕይ የተቀበለች እማሆይ ናት። በተመሳሳይ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የተጽፉት ጽሑፎች በዘመናችን የመለኮታዊ ፍቅር መገለጦች በመባል ይታወቃሉ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምዕመናኑ በላኩት መልዕክታቸው “ይህ ምሥጢር ለክርስቲያናዊ ትውፊት ያለው ጥልቅ ጠቀሜታ ከብዙ መቶ ዘመናት ጀምሮ ሲነገር የቆየ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታወቀ እና እየተከበረ የቆየ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው በማከልም፣ “የእርሷ እናታዊ ተጽዕኖ፣ በትህትና የተሞላው ስሟ እና ጥልቅ ሥነ-መለኮታዊ ግንዛቤዎቿ በአምላክ ፍቅራዊ በረከት እና የሕይወት ቅድስና በችግር ለወደቁት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በልግስና እንደሚገለጽ የሚያስተምር ወቅታዊ ማሳሰቢያዎች ከመሆን በተጨማሪ ለክርስቲያናዊ ደቀመዝሙርነት ሕይወት ብቻ ሳይሆን ፍትሃዊ እና ወንድማማችነት ባለው ኅብረተሰብ መካከል ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት የሚደግፉ እና ጊዜ የማይሽራቸው እውነቶች ናቸው” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመቀጠልም፣ እማሆይ ጁሊያ መንፈሳዊ ምክር እና ማበረታቻ ለሚጠይቁት ያሳየችው ልግስና ልዩ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው፣ “በተለይ በቁሳዊ ዓለም ውስጥ በሚገኙ በርካታ ያደጉ አገራት ሕዝቦች መካከል የሚታየውን የመገለል እና የብቸኝነት ችግሮችን ለመፍታት እና ለሌሎች ጥቅም ሲባል የራስን ጥቅም የመተው ፈቃደኝነት አስፈላጊ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ዛሬ የእግዚአብሔር የምሕረት እና የርኅራሄ መልዕክት አስፈላጊነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው፣ የእማሆይ ጁሊያ የእግዚአብሔር ምሕረት እና የርኅራኄ መልዕክት ለዛሬው ዓለም አስፈላጊ ሆኖ እንደሚቀጥል ገልጸው፣ “በመለኮታዊ ፍቅር ራዕዮቿ ውስጥ፣ በመካከላችን ክፋት ቢኖርም ሁሉም ነገር መልካም እንደሚሆን ከእግዚአብሔር ጸጋ መማሯን እንገነዘባለን” ብለዋል። በዚህ ረገድ ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን ሲያጠቃልሉ፣ “በጦርነት፣ በፍትሕ መጓደል፣ በሥነ ምህዳራዊ አደጋ ወይም በመንፈሳዊ ድህነት የሚያጋጥሙትን ከባድ ፈተናዎች የሚጋፈጡት በሙሉ በእነዚህ ዘላቂ የጥበብ ቃላት መጽናናትን እንዲያገኙ እጸልያለሁ” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመጨረሻም በመታሰቢያ በዓል ላይ ለተሳተፉት በሙሉ ቡራኬአቸውን በመስጠት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

16 May 2023, 15:52