ፈልግ

የዩኤስ ወታደር በጎ ፈቃደኛ ክሪስቶፈር ካምቤል የቀብር ሥነ ሥርዓት በኪየቭ-ዩክሬን የዩኤስ ወታደር በጎ ፈቃደኛ ክሪስቶፈር ካምቤል የቀብር ሥነ ሥርዓት በኪየቭ-ዩክሬን 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ በዩክሬን ሰላም እንዲወርድ መጸለይ እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 9/2015 ዓ. ም. ባቀረቡትን ሳምንታዊ ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምሮ ማጠቃለያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በጦርነቱ ምክንያት በየቀኑ መከራ ለሚደርስበት የዩክሬን ሕዝብ የሰላም ጸጋን በጸሎት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተገኙት ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተሰጠው የግንቦት ወር የሚቀርብ የመቁጠሪያ ጸሎት ከፍተኛ ዋጋ ያለው መሆኑን አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ የዕለቱን ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮአቸውን ለመከታተል በአደባባዩ ለተገኙት ታዳሚዎች እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ባቀረቡት ሰላምታ፣ ምዕመናኑ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እንዲያበቃ መጸለይ እንዳለባቸው ተናግረው፥ “በጦርነቱ ምክንያት ሕጻናትን ጨምሮ በየቀኑ ከፍተኛ የሞት እና የመቁሰል አደጋ ለሚደርስቸው ሰዎች በሙሉ ሰላም እንዲወርድ እንጸልይ” ብለዋል።

“የዓለምን ችግር ለሰማዕት ቦቦላ አደራ እንስጥ”

ቅዱስነታቸው ከፖላንድ ለመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን ሰላምታ ባቀረቡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ በተለይም የወንድማማችነትን ሕይወት በማሳደግ ጥረት ላይ ለተሰማራው ቡድን ባደረጉት ንግግር፣ በፖላንድ በምትገኝ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ትናንት የተከበረውን የኢየሱሳዊ ካህን የሰማዕት ቅዱስ እንድሪያስ ቦቦላ ዓመታዊ በዓልን በማስታወስ፣ “የትውልድ አገሩን ጨምሮ በሌሎች አገራትም የሚታዩ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን፣ በተለይም በዩክሬን ውስጥ ያለውን የሰላም ጥያቄ በአደራ ለእርሱ እንሰጣለን” ብለዋል።

“ሰላምን ለማግኘት የመቁጠሪያ ጸሎት እናድርስ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ለአረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ምዕመናን ባስተላለፉት መልዕክት፣ የጸሎትን ዋጋ እና የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነትን፣ ለእርሷ በተሰጠው በዚህ የግንቦት ወር የሚቀርብ የመቁጠሪያ ጸሎት ከፍተኛ ዋጋ ያለው እና የድነታችን ጠቅላላ ታሪክ ማጠቃለያ እንደሆነ አስታውሰዋል። በማከልም፣ የመቁጠሪያ ጸሎት ክፉን የምንዋጋበት ኃይለኛ መሣሪያ እንደሆነ እና በልባችን ውስጥ እውነተኛ ሰላምን የምናገኝበት ውጤታማ መንገድ መሆኑን በመግለጽ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

17 May 2023, 16:26