ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ 77ኛ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ 77ኛ ጠቅላላ ስብሰባ ላይ  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የጣሊያን ጳጳሳት የቤተ ክርስቲያንና የዓለም ተግዳሮቶችን ይፋ እንዲያደርጉ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያን ጳጳሳት ጉባኤ 77ኛ ጠቅላላ ስብሰባን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት፣ በሰላም፣ በፋይናንስ፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በጳጳሳት እና ካኅናት አገልግሎት እንዲሁም በድሆች፣ በስደተኞች እና በበጎ አድራጎት ጉዳዮች ላይ ግልጽ ውይይት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። ሰኞ ግንቦት 14/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ እና በጣሊያ ብጹዓን ጳጳሳት መካከል ግልጽ ውይይት የተደረገ ሲሆን፣ 77ኛውን ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ለማካሄድ በቫቲካን ከተሰበሰቡት ከ200 በላይ ጳጳሳት ጋር ቅዱስነታው ተወያይተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ብጹዓን ጳጳሳቱ በጉባኤያቸው ላይ ስለ ወጣቶች እና ጥሪ፣ ስለ ገንዘብ እና ርዕዮተ ዓለማዊ አስተምህሮዎች፣ ስለ ካህናት እና የዘርዓ ክህነት ትምህርት ቤቶች አገልግሎት፣ ስለ ሰላም፣ ስለ አካባቢ ጥበቃ እና ስለ በጎ አድራጎት ተቆርቋሪነት ተናጋግረዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሰኞ ግንቦት 14 እስከ ሐሙስ ግንቦት 17/2015 ዓ. ም. ድረስ የሚቆየውን እና "መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚናገራቸውን የማስተዋ እርምጃዎችን ማዳመጥ” በሚል መሪ ሃሳብ የተዘጋጀውን የብጹዓን ጳጳሳት የጸደይ ወር ጉባኤን በይፋ አስጀምረዋል።

ጥያቄዎች እና መልሶች

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሁሉም የአገሪቱ ክልሎች ከመጡት ጳጳሳት ጋር ያደረጉት ውይይት ሦስት ሰዓት ያህል የፈጀ ሲሆን፣ የተጀመረውም በሰሜን ጣሊያን ኤሚሊያ ሮማኛ ክፍል ሀገር በአውሎ ነፋስ አደጋ የተጎዱትን አካባቢዎች በጋራ ጸሎት አስታውሰዋል። በዝግ የተካሄደው ጠቅላላ ጉባኤው በጥያቄ እና መልስ የተካሄደ ሲሆን፣ ከዋና ዋና ርዕሠ ጉዳዮች መካከል፣ ስለ ሐዋርያዊ አገልግሎት ጥሪ ማሽቆልቆል እና ስለ ዘርዓ ክኅነት ትምህርት ቤቶች ውህደት የሚሉ ይገኙበታል። ከእነዚህ ርዕሠ ጉዳዮች በተጨማሪ በካህናት አገልግሎት ላይ በማትኮር፣ ቅዱስነታቸው ዘወትር እንደሚያሳስቡት፣ በጳጳሳት እና በካኅናት መካከል መቀራረብ ሊኖር እንደሚገባም ተወያይተዋል።

የበጎ አድራጎት ሥራን ማበረታታት

ብጹዓን ጳጳሳቱ በዩክሬን እና በዓለም ውስጥ የሚታየውን የሰላም ሁኔታ ሁሉንም ሰው የሚመለከት አጣዳፊ ጉዳይ መሆኑን፣ በጊዜያችን የሚነሱ አስተሳሰቦችን ማጤን፣ የተለያዩ ባህላዊ ችግሮችን እና ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን በሚመለከት እና ብዙውን ጊዜ ለቤተ ክርስቲያን  አስቸጋሪ ሁኔታን በሚፈጥሩ ችግሮች ላይ ተወያይተዋል።

እንዲሁም የአምስቱ አህጉራት ቤተ ክርስቲያንን የሚያሳትፍ ሲኖዶሳዊ ጉዞ፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ ለአዲስ እና አሮጌ የድህነት ሕይወት ትኩረት እንድንሰጥ እና ከሁሉም በላይ የበጎ አድራጎት ሥራ እንዳይጓደል ጥሪ ቀርቧል። በተለይም የበጎ አድራጎት ተግባራትን በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የጣሊያ ጳጳሳት ጉባኤ ለዓመታት ያህል ስደተኞችን እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን ለመቀበል ላሳዩት ቁርጠኛ አቋም ያላቸውን አክብሮት ገልጸዋል። ስደተኞችን በተመለከተ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለእያንዳንዱ የጣሊያን ጳጳስ በገጣሚ አሜትስ አርዛለስ አንቲያ የተገጠመ የስደተኛ ኢብራሂማ ባልዴ ሕይወት የሚተርክ 'Fratellino' የተሰኘ መጽሐፍ አበርክተዋል። ደራሲው በጽሑፉ ታናሽ ወንድሙን ፍለጋ አገሩን ጥሎ የተሰደደ የጊኒ ወጣት፣ በተራው ወደ አውሮፓ ተሰድዶ ወደ ቦታው ሳይደርስ የቀረበት ታሪክ ይናገራል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ መጽሐፉን በተለያዩ አጋጣሚዎች የጠቀሱ ሲሆን፣ ከሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሲመለሱ በአውሮፕላኑ ውስጥ በሰጧቸው አንዳንድ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እና ስብሰባዎች ላይ ለታዳሚዎች መናገራቸው ይታወሳል።

በጎርፍ ለተጎዱ የኤሚሊያ-ሮማኛ ሀገረ ስብከት ጳጳሳት ሰላምታን አቅርበዋል

በጉባዔው ጣልቃ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርብ ቀናት ውስጥ በማያቋርጥ እና አውዳሚ ጎርፍ ለተመቱት፣ በጣሊያን የኤሚሊያ ሮማኛ ክልል ሀገረ ስብከት ጳጳሳት ሰላምታቸውን አቅርበዋል፣ በነዋሪው ላይ የደረሰውን እና በመድረስ ላይ የሚገኘውን መከራ እና የተደረጉ በርካታ የአብሮነት ምልክቶችን ካዳመጡ በኋላ፣ በጸሎታቸው ከጎናቸው መሆናቸውን በማረጋገጥ ከማኅበረሰቡ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል። በጉባኤው መጀመሪያ ላይ የጣሊያ ጳጳሳት ጉባኤ ፕሬዝዳንት እና የቦሎኛ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ ዙፒ በአውሎ ነፋሱ ምክንያት ሕዝቡን ያጋጠሙት የተለያዩ ችግሮችን እና በርካታ የአብሮነት እና የዕርዳታ እጆች መዘርጋታቸውን አስረድተዋል። ብፁዕ ካርዲናል ማቴዮ በመጨረሻም ከሰሜን ጣሊያን ከመጡት ጳጳሳት ጋር ሆነው ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሰላምታቸውን ካቀረቡላቸው በኋላ ቅዱስነታቸው በአደጋው ለተጎዱት ያደረጉትን ድጋፍ በማስታወስ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ብጹዓን ጳጳሳቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ "በፍጥረት እና በጋራ መኖሪያ ምድራችን ጥበቃ ላይ የበለጠ ማሰላሰል ያስፈልጋል" በማለት ያቀረቡትን የማበረታቻ ሃሳብ በሙሉ ተነሳሽነት ተቀብለውታል። ጳጳሳቱ በማከልም "የኤሚሊያ ሮማኛ ሕዝብ ቆራጥ ቢሆንም ነገር ግን ፈተናዎች ብዙ ጊዜ እየተደጋገሙ እንደሆነ እና የቅዱስነታቸው ጸሎት እና ድጋፍ ያስፈልገዋል” በማለት አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለአዲስ የወንጌል ስርጭት ጥሪ አቅርበዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከጣሊያን ብጹዓን ጳጳሳቱ ጋር ያደረጉትን ዝግ ውይይት በማስመልከት የጳጳሳት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጁሴፔ ባቱሪ፣ TV200 ለተሰኘ ካቶሊክ ቴሌቪዥን በሰጡት መረጃ፣ "ዝግ ስብሰባው ከአገር ውስጥ እና ከቤተ ክርስቲያን ችግሮች ጋር ግንኙነት ያለው በመሆኑ አስፈላጊ ነበር" ብለዋል።

“አዲስ የወንጌል አገልግሎት ታማኝነት ባለው ምስክርነት የሚገለጽ አጣዳፊ ተግባር ነው” በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጥብቅ መናገራቸውን የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጁሴፔ፣ ብጹዓን ጳጳሳቱ ለሰው ልጅ ርኅራሄን በማሳየት፣ በተለይም ችግር ውስጥ ሆነው ዕርዳታን የሚለምኑትን እንዲንከባከቡ እና በዚህ መንገድ እንድንቀጥሉ ብርታትን ያገኙበት ስብሰባ እንደ፣ እንዲሁም በሂደት ላይ የሚገኝ ሲኖዶሳዊ ጉዞ ለውይይት እና ለሥራ ምቹ ቦታን ያገኘበት አጋጣሚ ነበር” በማለት አስረድተዋል።

 

24 May 2023, 18:02