ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሰሜን ጣሊያን አስቲ ሀገረ ስብከት የመጡ ነጋዲያንን በቫቲካን ተቀብለዋል  ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከሰሜን ጣሊያን አስቲ ሀገረ ስብከት የመጡ ነጋዲያንን በቫቲካን ተቀብለዋል   (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ቤተሰብ የኅብረተሰባችን ቁልፍ እሴት ሆኖ እንደሚቀጥል ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኅዳር 10 እና 11/2015 ዓ. ም. በሰሜን ጣሊያን አስቲ ሀገረ ስብከት ላደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ምስጋናቸውን ለማቅረብ የመጡ የሀገረ ስብከቱን ጳጳስ እና የምእመናን ተወካዮችን በቫቲካን ተቀብለዋቸዋል። ቅዱስነታቸው ዓርብ ሚያዝያ 27/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሏቸው እንግዶች ባደረጉት ንግግር፣ ቤተሰብ በኢየሱስ ክርስቶስ በመታገዝ ላመጡት ለውጥ ዋና ድጋፍ የሆናቸው የእርሱ ፍቅር፣ በምስጋና የተሞላ አገልግሎት እና እምነት መሆኑን አስረድተዋል። በሰሜን ጣሊያን የሚገኝ የአስቲ ሀገረ ስብከት የቅዱስነታቸው ወላጅ ቤተሰብ የትውልድ ሥፍራ ሲሆን፣ ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ሀገረ ስብከቱን በጎበኙበት ወቅት በአካባቢው ከሚገኙ ዘመዶቻቸው የተደረገላቸውን ደማቅ አቀባበል አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኢየሱስ ክርስቶስ ድጋፍ የተገኘው ክርስቲያናዊ ለውጥ በስጋ ዝብድና ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር የተገኘ በመሆኑ እጅግ አሰፈላጊ፣ በዝምድና እና በጥቅም ላይ ያልተመሠርተ፣ በምስጋና እና አንዱ ለሌላው በሚሰጠው አገልግሎት የተደገፈ መሆኑን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ኅዳር 10 እና 11/2015 ዓ. ም. በሰሜን ጣሊያን አስቲ ሀገረ ስብከት ላደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት፣ ወደ ወላጆቻቸው የትውልድ ሥፍራ በመምጣት የመጽናናት ልምድ የተገኘበት፣ ታላቅ ሰብዓዊ ፍቅር እና ቤተሰባዊ መንፈስ የታየበት መሆኑን፣ አራት መቶ የሚደርሱ የአስቲ ሀገረ ስብከት ነጋዲያንን በቫቲካን ተቀብለው ባደረጉት ንግግር ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።   

የወንድማማችነት መሠረት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው

ወንድማማችነት የሚለው ቃል በአገራችን፣ በአካባቢያችን እና በየከተሞቻችን በልማድ የሚነገር ቀላል ቃል ሳይሆን ሁሉን ሰው ወንድም እና እህት በሚያደርገው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ የተመሠረተ፣ በወንጌሉ በመመራት በኅብረት የሚጓዙት የፍቅር፣ የይቅርታ እና የሌላውንም ሸክም ጭምር የሚሸከሙበት የመረዳዳት መንገድ መሆኑን ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አስገንዝበዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም “በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በተመሠረቱት ቤተሰቦች፣ በአዲስ ባለ ትዳሮች፣ በወላጆች እና ልጆቻቸው መካከል የሚታይ ፍቅር በቤተ ክርስቲያን እና በሲቪሉ ማኅበረሰብ ዘንድም በመንጸባረቅ፣ ሰብዓዊ እሴቶች የሆኑ ምስጋናን የማቅረብ፣ እርስ በእርስ የመከባበር እና አንዱ ሌላውን በእንግድነት የመቀበል ልማዶች እንዲያድጉ ያደርጋል" ብለዋል።  

የቤተሰብነት መንፈስ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሰሜን ጣሊያን አስቲ ሀገረ ስብከት የተከበረው የኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ በዓል፣ በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል የተመለከቱት ከፍተኛ የቤተሰብነት መንፈስ ቶሎ የማይበርድ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠነከረ የሚመጣ መሆኑን ገልጸዋል። ቅዱስነታቸው ጨምረውም ከወላጆቻቸው የትውልድ ሐረግ እና ከዘመዶቻቸው ጋር መገናኘታቸው በሰፊ ትርጉሙ የእግዚአብሔር ሕዝቦች በጋራ በመሳተፍ በአንድ ካቴድራል ውስጥ የሚከበሩት በዓል፣ እንደዚሁም ሲቪሉ ማኅበረሰብ እና ባለ ስልጣናቱ በኅብረት መገኘታቸው የቤተሰብነትን መንፈስ የሚገልጽ መሆኑን ተናግረዋል። የሰው ልጆች የሚያሳዩት አንድነት ስሜታዊ ብቻ እንዳልሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በደስታ የተሞሉ ፊቶችን የተመለከቱበት፣ ፍቅራቸውን የተገነዘቡበት፣ በቅዱስ ወንጌል በመታገዝ ወደፊት የሚራመድ የክርስቲያን ቤተሰብ እንዳለ ያዩበት፣ ከሁሉም ውስንነቶች እና ችግሮች ጋር ዘወትር ወደ ፊት የሚጓዝ ቤተሰብ እንዳለ ያዩበት መሆኑን አስረድተዋል።

ከኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣ የቤተሰብ ለውጥ

“ቤተሰብ” በሚለው ቃል ላይ ያስተነተኑት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ “ብዙ ለውጦች የታዩበት እና አሁንም በለውጥ ጎዳና ላይ የሚገኝ እውነታ ነው" ብለው፣ ሆኖም ግን ቁልፍ እሴት ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል። “አዲሱን እና እውነተኛውን የቤተሰብ ለውጥ ወደዚህ ዓለም ያመጣው ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው” በማለት አስረድተዋል። በቅዱስ ማቴዎስ፣ በቅዱስ ማርቆስ እና በቅዱስ ሉቃስ ወንጌሎች የተጠቀሰውን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በደቀ መዛሙርቱ እና በሌሎች ሰዎች መካከል ሲሰብክ ሳለ፣ “እናትህ እና ዘመዶችህ ይፈልጉሃል” ባሉት ጊዜ ኢየሱስም በዙሪያው ወደ ነበሩት ሰዎች ዞሮ፥ “የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ ሁሉ ወንድሜም፣ እህቴ እና እናቴም ነው” ሲል መናገሩን አስታውሰው፣ የኢየሱስ ክርስቶስ መልስ ካሰብንበት ቤተሰብ የሚለውን ቃል ለመረዳት አዲስ መንገድ የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።

የኢየሱስ ቤተሰብ በምስጋና እና በጋራ አገልግሎት ላይ የተመሠረተ ነው

በክርስቲያኖች መካከል "ወንድሞች እና እህቶች" ተብለን መጥራታችን ልማዳዊ ብቻ ሳይሆን "ከኢየሱስ ክርስቶስ የመነጨ አዲስ እውነታ" እንደሆነ ቅዱስነታቸው አስረድተዋል። ቤተሰብ የሚለውን ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳደሰው የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በመሆኑም “ቤተሰብ የሚለው ቃል ለእኛ ለክርስቲያኖች የደም ትስስርን ሳይሆን ጠንካራ እና አስፈላጊ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ነው" ብለዋል። የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ቤተሰብን እንደሚለውጥ እና ከራስ ወዳድነት ነፃ እንደሚያወጣ የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ከኃጢአት ነፃ በማውጣት እና አዲስ ትስስርን በመፍጠር የበለጠ ጠንካራ የሚያደርግ፣ በዝምድና እና በጥቅም ላይ ያልተመሠርተ፣ በምስጋና በመሞላት አንዱ ለሌላው በሚሰጠው አገልግሎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል።

ደስታን እና በእንግድነት የመቀባበል ባሕልን የሚያሳድግ አዲስ ቤተሰብ

ከሰሜን ጣሊያን አስቲ ሀገረ ስብከት ከመጡት ወንድሞች እና እህቶች ሃሳባቸውን ለመካፈል እንድሚፈልጉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ እንግዶቹ በመጡበት አካባቢ የቤተሰባቸው ሐረግ መኖሩን ተናግረዋል። ሕይወት ለሰጠን እግዚአብሔር እና የቤተሰብ አካል እንድንሆን የጠራንን ኢየሱስ ክርስቶስ ማመስገን አለብን ብለው፣ በዚህ ውስጥ ትልቁ ነገር በሰማይ ያለውን የእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸም ነው" ብለዋል። አዲሱ የኢየሱስ ክርስቶስ ቤተሰብ ለቤተሰብ ግንኙነት አዲስ ትርጉም እንደሚሰጥ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣“በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በተመሠረቱት ቤተሰቦች፣ በአዲስ ባለ ትዳሮች፣ በወላጆች እና ልጆቻቸው መካከል የሚታይ ፍቅር በቤተ ክርስቲያን እና በሲቪሉ ማኅበረሰብ ዘንድም በመንጸባረቅ፣ ሰብዓዊ እሴቶች የሆኑ ምስጋናን የማቅረብ፣ እርስ በእርስ የመከባበር፣ አንዱ ሌላውን በእንግድነት የመቀበል እና ሌሎች ሰብዓዊ እሴቶች እንዲያድጉ ያደርጋል" ብለዋል። “ሁላችንም ወንድማማቾች ነን” በሚል መጠሪያ ስም የተቋቋመውን የሕክምና ማዕከል ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በሀገረ ስብከቱ ውስጥ ለአቅመ ደካሞች የሕክምና አገልግሎትን ለመስጠት የተቋቋመው ማዕከል የአካባቢው ነዋሪዎች ከሕክምና ባለሞያዎች እና ከበጎ ፈቃደኞች ጋር በመተባበር በሕመም ላይ ለሚገኙት ቤተሰቦች እንክብካቤን የሚያደርጉበት ማዕከል መሆኑን ገልጸዋል።  

በየከተማው፣ በየመንደሩ እና በልዩ ልዩ ቁምስናዎች ውስጥ "ወንድማማችነት" የሚለው ቃል በልማድ የሚገለጽ መልካም የንግግር ዘይቤ ብቻ ሳይሆን፣ ለወደ ፊት ሕይወት ዓላማ ላላቸው በሙሉ ተስማሚ ቃል፣ ሁላችንን ወንድሞች እና እህቶች ያደረገን የኢየሱስ ክርስቶስ መሠረት፣ በፍቅር፣ እርስ በእርስ በመደጋገፍ እና ይቅርታን በማድረግ ወደ ፊት ለመጓዝ የሚያስችለን የቅዱስ ወንጌል መንገድ መሆኑን፣ ምስጋናቸውን ለማቅረብ ከሀገረ ስብከታቸው ጳጳስ ጋር ሆነው ዓርብ ሚያዝያ 27/2015 ዓ. ም. ወደ ቫቲካን ለመጡት ነጋድያን ባሰሙት ንግግር ቅዱስነታቸው አስረድተዋል።

06 May 2023, 16:45