ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ብርታትን በመጨመር ለወንጌል ተልዕኮ እንደሚያነሳሳ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ረቡዕ ግንቦት 9/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሳምንታዊውን የጠቅላላ ትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ አቅርበዋል። ከተለያዩ አገራት የመጡ ምዕመናን፣ መንፈሳዊ ነጋዲያን እና የሀገር ጎብኚዎች የቅዱስነታቸውን አስተምህሮ በዛሬው ዕለት ተከታትለውታል። ቅዱስነታቸው በዛሬው ሳምንታዊ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፥ “የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ብርታትን በመጨመር ለወንጌል ተልዕኮ ይገፋፋል” ብለዋል። ክቡራት ክቡራን ተከታታዮቻችን ቅዱስነታቸው በዛሬው ዕለት ያቀረቡት የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ ትርጉም ከማቅረባችን በፊት ያስተነተኑበትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከዚህ ቀጥሎ እናቀርብላችኋለን፥

“አንዱ ስለ ሁሉ እንደ ሞተ እርግጠኞች በመሆናችን፥ የክርስቶስ ፍቅር ግድ ይለናል፤ ይህ በመሆኑም ሁሉ ሞተዋል። በሕይወት ያሉት፥ ስለ እነርሱ ለሞተው እና ለተነሳው እንጂ፣ ወደ ፊት ለራሳቸው እንዳይኖሩ እርሱ ስለ ሁሉ ሞተ። ስለዚህ እግዚአብሔር ጥሪውን የሚያቀርበው በእኛ በኩል በመሆኑ፥ እኛ ለክርስቶስ መልዕክተኞች ነን፤ ስለ ክርስቶስ ሆነን “ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ” ብለን እንለምናለን። (2ኛ ቆሮ. 5:14-15 እና 20)

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እንደምን አረፈዳችሁ!

በአንዳንድ የሐዋርያዊ ቅንዓት ምሳሌዎች ላይ የጀመርነውን አስተምህሮ በመቀጠል፥ በዛሬው አስተምህሮ የዘመናችን ታላቅ የወንጌል መልዕክተኛ ተብሎ የሚገመተውን እና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮዎች ጠባቂ የሆነውን የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየር ታሪክ እናያለን።

ቅዱስ ፍራንችስኮስ ዛቪየር፥ በሰሜን ስፔን ናቫራ በተባለች አካባቢ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1506 ዓ. ም. ከተከበረ ነገር ግን ድሃ ከነበረ ቤተሰብ ተወለደ። ጥሩ ደሞዝ የሚከፈልበትን የቤተ ክርስቲያን ሥራ ለማግኘት የሚያስችል የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ለመቅሰም ወደ ፓሪስ ሄደ። በስፖርት እና በትምህርት የተካነ፣ ተወዳጅ እና ጎበዝ ወጣት ነበር። በኮሌጅ ቆይታው አንድ በዕድሜ የሚበልጠውን እና በተወሰነ ደረጃ ልዩ የሆነ ጓደኛን አገኘ። እርሱም የሎዮላው ኢግናጤዎስ የሚባል ነበር። ሁለቱ ታላቅ ጓደኛሞች ሆኑ። ኢግናጤዎስ ፍራንችስኮስ ኢየሱስ ክርስቶስን በመውደድ እና በመከተል፥ ራሱን ከማንኛውም ምኞት ለማላቀቅ እና ለእግዚአብሔር አገልግሎት እራሱን እንዲሰጥ፣ አዲስ እና ጥልቅ የሆነ መንፈሳዊነት እንዲኖረው ረዳው። ፍራንችስኮስ ዛቪየር የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንደጨረሰ፣ እሱ እና ሌሎች ጓደኞቹ በዓለም ላይ ላሉ የቤተ ክርስቲያን አስቸኳይ ጥሪዎች ራሳቸውን ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ለማቅረብ ወደ ሮም አቀኑ። መጀመሪያ ላይ አሥር ያህል ነበሩ። እነዚህ ወጣቶች እራሳቸውን "የኢየሱሳውያን ማህበረሰብ" ብለው ለመጥራት ወሰኑ።

ወቅቱ ክርስትና ከአውሮፓ አህጉር ወደ ሌሎች ሩቅ የዓለም ዳርቻዎች የሚሰፋበት ጊዜ ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስን ወንጌል ገና ያልሰሙ ሰዎች የሚገኙባቸው አዳዲስ አህጉራት ነበሩ። የፖርቱጋል ንጉሥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳቱ አንዳንድ የኢየሱሳውያን ማኅበት አባላትን ወደ ምሥራቅ ኢንዲስ እንዲልኩ በጠየቋቸው ጊዜ ከመካከላቸው ፍራንችስኮስ ዛቪየር ይገኝበታል። ስለዚህ ልኡካኑ ኢየሱስ ክርስቶስን እና ወንጌሉን ለመስበክ ባላቸው እጅግ ጽኑ ፍላጎት ተገፋፍተው፣ ከባድ መከራዎችን እና አደጋዎችን በማለፍ፣ ወደ ምድር ዳርቻ ሁሉ ለመድረስ እና በፍጹም የማይታወቁ ባሕሎች እና ቋንቋዎች ካላቸው ሰዎች ጋር ለመገናኘት ዝግጁ እና ከፍተኛ ስሜት ያላቸው በርካታ የሚስዮናውያን ቡድን ጉዞን ጀመረ። የዚህ ቡድን ከፍተኛ ፍላጎት እና ዓላማ ብዙ ሰዎችን ወደ እግዚአብሔር እና ወደ እውነተኛ ጥቅማቸው በመምራት እንዲድኑ ማድረግ ነበር።

ፍራንችስኮስ ዛቪየር የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ሦስተኛ ሐዋርያዊ እንደራሴ በመሆን፥ ኢንዲስ እየተባሉ ለሚጠሩት ገዥዎች ተወካይ ሆኖ ተሾመ። ፍራንችስኮስ ዛቪየር ከአሥራ አንድ ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ አስደናቂ ተግባራትን አከናወነ። በዚያን ጊዜ ከቦታ ቦታ መጓዝ ከባድ እና አደገኛ ነበር። ብዙ ሰዎች  በመርከብ ብልሽት ወይም በበሽታ ምክንያት መንገድ ላይ ይሞቱ ነበር። ፍራንችስኮስ ዛቪየር መርከቦች ላይ ከሦስት ዓመት ተኩል በላይ አሳልፏል። ይህም ከተልዕኮው ጠቅላላ ቆይታ መካከል አንድ ሦስተኛው ነው። ፍራንችስኮስ ዛቪየር የፖርቱጋሎች ምሥራቃዊ ሕንድ ግዛት ወደ ሆነች ጎዋ ከተማ እንደደረሰ ኑሮውን እዚያ አደረገ እንጂ በዚያ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። በሕንድ ደቡባዊ የባሕር ዳርቻ ለሚገኙ ድሃ ዓሣ አጥማጆች ወንጌልን ለመስበክ፣ ሕጻናትን ትምህርተ ክርስቶስ እና ጸሎት ለማስተማር፣ ሕሙማንን በማጥመቅ እና በመንከባከብ ወንጌልን ለመስበክ ሄደ።

ከዚያም የሐዋርያው ቅዱስ በርተሎሜዎስ መቃብር በሚገኝበት ሥፍራ የማታ ጸሎት እያቀረበ ሳለ፥ ከሕንድ አልፎ ወደ ሌሎች አካባቢዎችን መሄድ እንዳለበት ተሰማው። ያከናወናቸው የነበሩ ሥራዎችን መልካም እና ጎበዝ በሆኑ ሰዎች እጅ በመተው በድፍረት በመርከብ እጅግ በጣም ርቀው ወደሚገኙ የኢንዶኔዥያ ደሴቶች ሄደ። ትምህርተ ክርስቶስን በአገሩ ቋንቋ ተርጉሞ በግጥም በማስቀመጥ እንዴት መዘመር እንዳለበት አስተማረ። ስሜቱንም ከደብዳቤዎቹ እንረዳለን፥ “ሊደርሱን የሚችሉ አደጋዎችን እና መከራዎችን በፈቃደኝነት የምንቀበላቸው ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ፍቅር እና አገልግሎት ስንል እንዲሁም በታላቅ መንፈሳዊ ጽናቶች የተሞሉ ውድ ሃብቶች በመናቸው ነው። እዚህ አንድ ሰው ከብዙ የደስታ እንባ የተነሳ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዓይኖቹን ሊያጣ ይችላል” ሲል እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ጥር 20/1548 ዓ. ም. ጽፏል።

ከዕለታት አንድ ቀን ሕንድ ውስጥ ያገኘው አንድ ጃፓናዊ፥ ሩቅ በሆነ አገሩ ወንጌልን የሚሰብክ አንድም አውሮፓዊ ልኡክ አለመኖሩን ነገረው። ፍራንችስኮስ ዛቪየርም በተቻለ ፍጥነት ወደ ሥፍራው ለመሄድ ስለወሰነ፥ ድፍረት የተሞላበት ጉዞን ካደረገ በኋላ ወደ አካባቢው ደረሰ። ጃፓን ውስጥ ያሳለፋቸው ሦስት ዓመታት በአየር ጸባይ፣ በተቃውሞ እና ቋንቋን ካለማወቅ ምክንያት በጣም ከባድ ነበሩ። ነገር ግን እዚህም የተዘሩት ዘሮች ትልቅ ፍሬ ማፍራታቸው አልቀረም።

ፍራንችስኮስ ዛቪየር በጃፓን ቆይታው፥ በእስያ ለሚደረግ የወንጌል ተልዕኮ ወሳኝ አገር ሌላዋ እንደሆነች ተረዳ። ይህችም አገር ቻይና እንደሆነች ተገነዘበ። ቻይና በባሕሉ፣ በታሪኩ እና በስፋቱ በዚያ የዓለም ክፍል ላይ የበላይነቷን አሳይቷል። ስለዚህ ፍራንችስኮስ ዛቪየር ከዚህ በፊት ወደነበረባት ወደ ጎዋ ከተማ ተመለሰ። ምንም እንኳን ለውጭ ዜጎች የተዘጋ ቢሆንም፥ ብዙም ሳይቆይ ቻይና ለመግባት ተስፋ በማድረግ እንደገና በመርከብ ተሣፈረ። ነገር ግን እቅዱ ከሸፈ። ካንቶን በተባለች ዋና መሬት ላይ ለማረፍ እየጠበቀ እያለ ሳንሲያን በተባለች ትንሿ ደሴት ውስጥ ሕይወቱ አለፈ። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ታኅሣሥ 3/1552 ዓ. ም. ሙሉ በሙሉ ብቻውን በሆነበት፥ እሱን ለመጠበቅ አንድ ቻይናዊ ብቻ ከጎኑ ቆሞ ነበር። በዚህ ሁኔታ የፍራንችስኮስ ዛቪየር ምድራዊ ጉዞ አከተመ። ሕይወቱ ስታልፍ ዕድሜው አርባ ስድስት ነበር። ፀጉሩ ከዕድሜው ቀድሞ ሸበተ፤ ጉልበቱ ተሟጠጠ፣ ሳይሰስት ዕድሜውን እና ጉልበቱን ለወንጌል አገልግሎት ሰጠ።

የእርሱ ጠንካራ አገልግሎት ዘወትር በጸሎት የተደገፈ፣ በመንፈሳዊ ተመስጦ እና ጥልቅ ማሰላሰል ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ያለው ነበር። በሄደባቸው አካባቢዎች ሁሉ የታመሙትን፣ ድሆችን እና ሕጻናትን ይንከባከብ ነበር። የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅር ወደ ሩቅ አካባቢዎች እንዲሄድ በመገፋፋት ብርታትን ይሰጠው ነበር። የማያቋርጥ ድካምን፣ አደጋን እና እንቅፋቶችን በማሸነፍ፣ ቅሬታ እና ተስፋ መቁረጥ ሲሰማው እንኳ ኢየሱስ ክርስቶስን እስከ መጨረሻው መከተል እና ማገልገል መጽናናትን እና ደስታን ይሰጠው ነበር።"

17 May 2023, 16:20