ፈልግ

“ለሃያ አራት ሰዓት ከእግዚአሔር ጋር" ዝግጅት የንስሐ ሥነ ሥርዓት “ለሃያ አራት ሰዓት ከእግዚአሔር ጋር" ዝግጅት የንስሐ ሥነ ሥርዓት  (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ምዕመናን በር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የገቡት ንስሐ፣ በኃጢአታቸው ተጸጸተው የገቡት ንስሐ መሆኑን ገለጹ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ዓርብ መጋቢት 8/2015 ዓ. ም. በሮም ከተማ በሚገኝ ቅድስት ድንግል ማርያም የጸጋ እናት ቁምስና በመሄድ ሐዋርያዊ ጎብኝት አድርገዋል። የዓብይ ጾም ወቅትን ምክንያት በማድረግ፣ “ለሃያ አራት ሰዓት ከእግዚአሔር ጋር ቆይታ እናድርግ” በሚል ርዕሥ ቁምስናው ባስተባበረው ዝግጅት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተገኝተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ዘንድሮ ለአሥረኛ ጊዜ በተዘጋጀው ዝግጅት ላይ የቁምስናውን ምዕመናን ጨምሮ ሮም ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ልዩ ልዩ ቁምስናዎች የመጡት መንፈሳዊ ነጋዲያን በዕለቱ በቀረበው የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ንስሐን ገብተው የተመለሱ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስም ቁምስናው ባዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ላይ በመገኘት የተወሰኑ ምዕመናንን ንስሐ በማስገባት የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ለምነዋል።

ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀርበው ንስሐ ከገቡት አምስት ምዕመናን መካከል አንዷ ወጣት እናት፣ ወደ ቅዱስነታቸው ዘንድ ለመቅረብ ከቁምስናው መሪ ካህን የተሰጣት ዕድል ከፍተኛ ስጦታ እንደሆነ ገልጻ፣ ያለፈው ዓመት የአእምሮ ዝግመት ያለበት ሕጻን መገላገሏን በማስታወስ፣ ይህም ከእግዚአብሔር የተሰጣት ስጦታ መሆኑንም ገልጻለች። ባሏ እና እርስዋ ሕጻኑ ከመወለዱ አስቀድሞ ችግር እንዳለበት ሐኪሞች ሲነገሯቸው ተረብሸው እንደ ነበር ወጣቷ እናት ገልጻ፣ ሆኖም ግን፣ ሁለቱም በእግዚአብሔር የሚያምኑ እንደመሆናቸው ስጦታቸውን ተንከባክበው በጥሩ ሁኔታ ማሳደግ የሚችሉበት መንገድ እንዳለ ማሰባቸውን ገልጻለች። ይህ ዓይነት ችግር ያለባቸውን ወላጆች ለሚደግፉት ቤተሰቦች በሙሉ ምስጋናዋን አቅርባ፣ ከመልካም ቤተሰብ በሚደረግላቸው ዕርዳታ በመታገዝ በጥሩ ሁኔታ እየኖሩ የሚገኙ በርካታ ወላጆች መኖራቸውን አስረድታለች። "የክርስትና ሕይወት ብዙ አግዞናል” ያለችው ወጣት እናት፣ ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድ የቀረበችውም ማኅበረሰቦቿን በመወከል እንደሆነ የተሰማት መሆኑን ገልጻለች።

“ራስን ይቅር ማለት ከባድ ነገር ነው”

ወደ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ዘንድ ቀርበው ንስሐ ከገቡት አምስት ምዕመናን መካከል አንዱ ወጣት፣ በእርግጥ ያልተለመደ ክስተት እንደነበር ገልጾ፣ ምናልባት በመደበኛነት መኖር ያለበት ተሞክሮ ሊሆን እንደሚገባ ተናግሯል። እርሱን ንስሐ ያስገቡት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከእግዚአብሔር በተቀበሉት የክህነት ጸጋ አማካይነት እንደሆነ የገለጸው ወጣቱ፣ በዚያች ቅጽበት ይቅርታን የተቀበለው ከኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን እንደሚያምን ተናግሯል። ወጣቱ በማከልም በዕለቱ የፈጸመውን የንስሐ ሥነ ሥርዓት ልዩ የሚያደርገው “የራስን ልብ እና ደካማነት ለሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ለሆኑት፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ አሳልፎ መስጠት መቻል ነው” በማለት አስረድቶ፣ ከዚህም በተጨማሪ በዚህ የዓቢይ ጾም ወቅት ወደ ቤተ ክርስቲያን መመለሱ ከፍተኛ ጥቅምን እንደገና ያገኘበት ልዩ አጋጣሚ መሆኑን ተናግሯል።

ወጣቱ አክሎም ግልጽ በሆነ መንገድ ህሊናውን ለመመርመር ጊዜን በማግኘት እራሱን በጥንቃቄ በመመልከት እና ግንዛቤን በማግኘት ለንስሐ መዘጋጀቱን ገልጿል። በጠቅላላው እርሱ የሚጋራው እውነት እንዳለ የገለጸው ወጣቱ፤ “ለኑዛዜ መቅረብ የሚያስፈራ ቢሆንም ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ እና ከጊዜ ወደ ጊዜ ሊለማመዱት የሚገባ ቅዱስ ምስጢር እንደሆነ ተናግሮ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሕረት እንዳደረገ ሁሉ፣ ካህናትም ምሕረት እንዲያደርጉ በማለት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጠየቃቸውን አስታውሷል።

“እራስን ይቅር ማለት የበለጠ ከባድ ነው” ያለው ወጣቱ፣ “ቢሆንም አንድ መማር ያለበት ነገር ነው" ብሎ፣እራስን ይቅር ማለት ምስጢራዊ ከመሆኑ በላይ፣ የወደፊት ተስፋውም ከዚህ ልምድ አንዳንድ ፍሬዎችን ማየት እንደሆነ አክሎ ተናግሯል። ቤተ ክርስቲያንን ሳያቋርጥ በማዘውትር ደስተኛ ሕይወትን እንዴት መኖር እንደቻለ አስታውሶ፣ የሮም ሀገረ ስብከት መሪ ጳጳስ ከሆኑት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳስት ፍራንችስኮስ ጋር በንስሐ ሰዓት ያደረገው ቆይታ ሙሉ እምነት ያለበት አድርጎ እንደሚቆጥረው አስረድቷል።

18 March 2023, 16:17