ፈልግ

2023.03.03 Assemblea continentale sinodale dell'Africa, Addis Ababa Ethiopia

ሲኖዶሳዊነት በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ

ቀዳሚ ማስታወሻ

አለም አቀፉ የስነ መለኮት ኮሚሽን በ9ኛው ጉባሄው የመጀመሪያዎቹ አምስት አመታት ውስጥ በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተልእኮ ላይ ስለ ሲኖዶሳዊነት ጥናት አካሂዶ ነበር። ሥራው የተከናወነው በአንድ የተወሰነ ንዑስ ኮሚቴ ሲሆን የዚህ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ብፁዕ አባ ማሪዮ አንጄል ፍሎሬስ ራሞስ እና የሎዮላ ማህበረሰብ አባል የሆኑ ሲስተር ፕሩደንስ አለን፣ ብፁዕ አባ አንቶኒዮ ሉዊዝ ካቴላን ፌሬራ፣ ብፁዕ አባ ፒዬሮ ኮዳ፣ ክቡር ካርሎስ ማሪያ ጋሊ፣ ክቡር አልፍሬድ ሃኪም፣ ፕሮፌሰር ሄክተር ጉስታቮ ሳንቼዝ ሮጃስ፣ ክቡር አባ ጄራርድ ፍራንሲስኮ ቲሞነር ይገኙበታል።

የዚህ ዝግጅት አዘጋጅ እና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

በዚህ ጭብጥ ላይ አጠቃላይ ውይይቶች የተካሄዱት በንዑስ ኮሚቴው ስብሰባዎች እና ኮሚሽኑ ራሱ እ.አ.አ  በ2014 እና 2017 ዓ.ም መካከል ባካሄደው የምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ነው። የአሁኑ ጽሁፍ ማለትም ከእዚህ በታች የሚገኘው ሲኖዶሳዊነትን የተመለከተ ጽሑፍ እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም በአብዛኛዎቹ የኮሚሽኑ አባላት ጸድቋል። ሰነዱ በኋላም በኮሚሽኑ በፕሬዚዳንት የኢየሱሳዊያን ማሕበር አባል በሆኑት እና በቅድስት መንበር ጥላ ሥር በሚተዳደረው የቤተክርስቲያን የእመንት አስተምህሮዎችን ጉዳይ በበላይነት በሚቆጣጠረው ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ዋና ፕሬዚዳንት በሆኑት ብፁዕ ካርዲናል ሉዊስ እ.አ.አ በመጋቢት 2 ቀን 2018 እንዲታተም ፈቃድ የተሰጠው ሲሆን ይህም ሰነድ ይፋ የሆነው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስክሶስ መልካም ፈቃድ ከተሰጠው በኋላ የጸደቀ ነው።

መግቢያ

ለሲኖዶሳዊነት የሚሆን መልካም ጊዜ (THE KAIRÓS OF SYNODALITY)

(ለውሳኔ ወይም ለድርጊት የሚሆን መልካም ወይም ምቹ ወቅት/ጊዜ)

1. “እግዚአብሔር በሦስተኛው ሚሌንዬም ውስጥ ከምትገኘው ቤተ ክርስቲያን የሚጠብቀው ይህንን የሲኖዶሳዊነት መንገድ ነው” (እ.አ.አ በጥቅምት 07/2015 ዓ.ም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ ተቋም 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ)፤ የዚህ ፕሮግራም ግቢራዊነት ቁርጠኝነት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ የብፁዓን ጳጳሳት ሲኖዶስ የተቋቋመበትን 50ኛ ዓመት የምስረታ በዓል በቫቲካን በሚገኘው በጳውሎስ 6ኛ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ሲከበር ለታዳሚዎች ባደረጉት ንግግር ይፋ አድረገዋል። በእርግጥም ሲኖዶሳዊነት “የቤተ ክርስቲያን አስፈላጊ ገጽታ ነው” በማለት አጽንኦት ሰጥተው በወቅቱ የገለጹት ቅዱስነታቸው “ጌታ ከእኛ የሚጠይቀው በተወሰነ መልኩ ‘ሲኖዶስ’ በሚለው ቃል ውስጥ ይገኛል” ማለታቸው ይታወሳል።

2. ይህ ሰነድ ወደዚህ የተስፋ ቃል ሥነ-መለኮታዊ ስሜት እና ለቤተክርስቲያኗ ተልእኮ ምን እንደሚያመለክት አንዳንድ የሐዋርያዊ ተግባራትን አቅጣጫዎችን በጥልቀት ለመረዳት የሚያስችል አንዳንድ ጠቃሚ መመሪያዎችን ለማቅረብ ያለመ ነው። መግቢያው ስለ ይዘቱ እና 'ሲኖዶሳዊነት'' ለሚለው ቃል የመጀመሪያ ደረጃ ማብራሪያ የሚያስፈልገውን ሥርወ-ቃል እና ፅንሰ-ሃሳባዊ መረጃዎችን ያሳያል። ከዚያም የሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ባመጣው መነቃቃት ላይ እና የቤተክርስቲያኗ አስተምህሮ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሰጠንን ጠቃሚ እና አዲስ ትምህርት በዐውደ-ጽሑፉ ያስቀምጣል።

ሲኖዶስ፣ ጉባኤ፣ ሲኖዶሳዊነት

3. “ሲኖዶስ” የሚለው ቃል በቤተ ክርስቲያን ትውፊት ውስጥ ጥንታዊ እና የተከበረ ቃል ነው፣ ትርጉሙም የራዕይ ጥልቅ ጭብጦችን ያመጣል። በሁለት የግሪክ ቃላት ውዕድ ሐሳብ የተዋቀረ ሲሆን ተውላተ ስም “συν” (‘ሲን’ ጋር) እና ስም όδός (‘ኦዶስ’ መንገድ) በሚሉት ቅላት የተዋቀረ ሲሆን ይህም የእግዚአብሔር ሰዎች አብረው የሚሄዱበትን መንገድ ያመለክታል። በተመሳሳይም ራሱን እንደ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” የሚያቀርበውን ጌታ ኢየሱስን ያንጸባርቃል (ሐዋ 9፣2፣ 19፣9.23፣ 22፣4፣ 24፣14.22)።

በግሪክ ቤተክርስቲያን የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዴት እንደ አንድ ጉባኤ እንደተጠሩ ይገልፃል እና በአንዳንድ ሁኔታዎችም ለቤተ ክርስቲያን ማህበረሰብ ተመሳሳይ ድምፅ ያሰማል። ለምሳሌ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል “በአንድነት ለመራመድ የቆመ ስም ነው” ሲል ጽፏል። ሁሉንም ነገር አንድ ላይ የሚይዝ የአንድነት እውነታ ነው፣ ምክንያቱም በተገላቢጦሽ ለአንድ አላማ የሚሰሩ የተለያዩ አቋም ያላቸው፣ የተጣመረ እዕምሮ ያላቸው በማለት ይገልጻቸዋል።

4. ከመጀመሪያዎቹ መቶ አመታት ዘመናት ጀምሮ “ሲኖዶስ” የሚለው ቃል በቃሉ ብርሃን ለመረዳት በተለያዩ ደረጃዎች (በሀገረ ስብከት፣ በአጉረ ስብከት፣ በቁምስናዎች እና በደብሮች፣ በፓትርያርክ ወይም በዓለማቀፋዊት ቤተክርስቲያን ማዕከላት) ለተጠሩት ቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች የተወሰነ ትርጉም በመስጠት ሲሠራበት ቆይቷል። እግዚአብሔር እና መንፈስ ቅዱስን ማዳመጥ፣ በጊዜ ሂደት ውስጥ እና ጊዜ እያለፈ ሲሄድ የሚነሱትን የቤተክርስቲያን አስተምህሮዎችን፣ ሥርዓተ አምልኮ፣ ቀኖናዊ እና የመሳሰሉ ተዛማች ጥያቄዎችን ለመመለስ ይችላ ዘንድ በተከታታይ እና አስፈላጊ በሆኑ ጊዜያት የሚካሄደውን ሲኖዶስ ያመለክታል።

በግሪክ ቋንቋ “σύνοδος” (‘ሲንኦዶስ’... በግርድፉ አንድ እውቅና ያለው በባለስልጣናት የሚካሄድ የስብሰባ ክፍለ ጊዜ የሚለውን የአማርኛ ትርጉም ይወክላል) ይህ ቃል በላቲን ቋንቋ synodus ወይም concilium ‘ሲንኦዶስ’ ወይም ‘ኮንችሊዬም’ በሚለው ተተርጉሟል። በላቲን ቋንቋ ‘ኮንችሊዩም’ (ጉባሄ) እንዲያው አለማዊ በሆነ የቃል መፍቻ በግርድፉ ስንመለከት አጠቃቀሙ፣ በአንዳንድ ህጋዊ ባለስልጣኖች የተጠራውን ስብሰባን ያመለክታል። “የሲኖዶስ” እና “ምክር ቤት” የተሰኙት ሐረጎች ሥር መሰረቶቻቸው የተለያዩ ቢሆኑም ትርጉማቸው አንድ ነው። እንዲያውም “ጉባኤ” የዕብራይስጥ ቋንቋ קָהָל (‘ካሀል’ ሕዝብ) በጌታ የተጠራውን ጉባኤ እና ወደ ግሪክ ሲተረጎም έκκλησία (‘ኤክሌዚያ’ ቤተክርስቲያን) በማለት በአዲስ ኪዳን በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ሕዝብ የፍጻሜ ጉባኤ የ“ሲኖዶስ”ን የትርጓሜ ይዘት ያበለጽጋል።

5. በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ "ጉባኤ" እና "ሲኖዶስ" በሚሉት ቃላት መካከል ያለው ልዩነት የቅርብ ጊዜ ትውስታዎችንን የሚያመልክት ነው። በሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ ላይ ሁለቱ ቃላት ተመሳሳይ ገጽታ ነበራቸው፣  ሁለቱም የጉባሄውን ወቅት በመጥቀስ ማለት ነው። አንድ ትክክለኛ ልዩነት በላቲን ቤተ ክርስቲያን ሕገ ቀኖና (1983) እንደ ተገለጸው ከሆነ፣ እሱም በልዩ (ምልአተ ጉባኤ ወይም አውራጃዊ) ጉባሄ እና በአንድ በኩል በማኅበረ ቅዱሳን፣ በጳጳሳት ሲኖዶስ እና በአገረ ስብከት ደረጃ ስለሚካሄደው ሲንዶስ መካከል ያለውን ልዩነት ይለያል።

በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ በሥነ-መለኮት ፣ በቀኖናዊ እና በሐዋርያዊ ሥነ-ጽሑፍ በኩል አዲስ የተፈጠረ ቃል ወይም አገላለጽ ታይቷል “ሲኖዳዊነት” የሚለው ቃል ወይም ስም ፣ የ“ሲኖዶሳዊነት” ቅጽል ተዛማጅ ሲሆን እነዚህ ሁለቱም “ሲኖዶስ” ከሚለው ቃል የተገኙ ናቸው። ስለዚህ ሰዎች ስለ ሲኖዶሳዊነት እንደ “የቤተክርስቲያኑ ሕገ ቀኖና ገጽታ” ወይም “የሲኖዶስ ቤተ ክርስቲያን” ጠቅላይ ፍርድ ቤት አድርገው ይናገራሉ። ይህ የቋንቋ አዲስነት፣ ጥንቃቄ የተሞላበት የነገረ መለኮት ማብራሪያ የሚያስፈልገው፣ ከሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ የቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጀምሮ በቤተ ክህነት ንቃተ ህሊና ውስጥ እየዳበረ የመጣ የአዲስ ነገር ምልክት ሲሆን ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና ከዓለም አቀፉ ቤተክርስቲያን የአኗኗር ልምድ ካለፈው ጉባኤ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ እየዳበረ የመጣ ነው።

ሕብረት፣ ሲኖዶሳዊነት፣ ጉባሄአዊነት (‘collegiality’ ኃላፊነት በተጣለባቸው ሰዎች መካከል ያለው ትብብር)

6. በሁለተኛው የቫቲካን ጉባሄ አስተምህሮ ውስጥ ሲኖዶሳዊነት እንደ ቃል ወይም እንደ ጽንሰ-ሐሳብ ቀርቦ በግልፅ ቦታ ባይገኝም የመታደስ ሥራው ዋና ማዕከል የሆነው ሲኖዶሳዊ ጉባኤው አበረታች ነበር ማለቱ ተገቢ ነው።

በቤተክርስቲያን ሥርዓት መሰረት ምስጢረ ጥምቀት የተቀበሉ የእግዚአብሔር ሕዝብ ሁሉ ልዩነታቸውን እና የሥርዓተ ምግባራቸውን ብልጽግናን፣ ጥሪያቸውን እና አገልግሎታቸውን በመለማመድ ያላቸውን የጋራ ክብር እና ተልዕኮ ያጎላል። በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ የኅብረት ጽንሰ-ሐሳብ የቤተክርስቲያንን ምስጢር እና ተልእኮ ጥልቅ ይዘት ይገልፃል ፣ ምንጭ እና ቁንጮው የቅዱስ ቁርባን ጥምረት እንደ ሆነ ያብራራል። ይህ የቤተክርስቲያን ምስጢራት ሕብረትን የሚያሳይ ሲሆን ከእግዚአብሔር ጋር አንድነት ያለው ቅድስት ሥላሴ እና በሰዎች መካከል ያለው አንድነት፣ በመንፈስ ቅዱስ በክርስቶስ ኢየሱስ እውን ሆኗል።

7. በዚህ የሥርዓተ ቤተክርስቲያን ዐውደ-ጽሑፍ፣ ሲኖዶሳዊነት የቤተክርስቲያን ልዩ በላቲን ቋንቋ “modus vivendi et operandi” ሞዱስ ቪቨንዲ ኤት ኦፔራንዲ (የአኗኗር ዘይቤ እና ሥራ ) ነው፣ ይህም የእግዚአብሔር ሕዝብ፣ ሁሉም አባሎቿ በአንድነት ሲጓዙ፣ በጉባኤ ተሰብስበው በስብከተ ወንጌል ተልእኮዋ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርጉ፣ ኅብረት መሆኖን የሚገልጥ እና ይዘትን የሚሰጥ ነው።

የሲኖዶሳዊነት ጽንሰ-ሐሳብ የእግዚአብሔር ሕዝብ በሙሉ በቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ተልእኮ ውስጥ ያለውን ተሳትፎና ተልዕኮ የሚያመለክት ሆኖ ሳለ፣ ጉባሄአዊነት (ኃላፊነት በተጣለባቸው ሰዎች መካከል ያለው ትብብር) ጽንሰ-ሐሳብ የሚከተሉትን ሥነ-መለኮታዊ ፋይዳውን እና መልክን ይገልፃል...

·      የጳጳሳት አገልግሎት በየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለእያንዳንዳቸው አደራ የተሰጣቸው ነው፣

·      በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በአንዲት ዓለም አቀፋዊ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን እምብርት ላይ የሚገኘውን የጳጳሳት ሕብረት ያለው ተዋረዳዊ ሕብረት በመጠቀም ነው፣ ይህም የሮም ኤጲስ ቆጶስ በቀዳሚነት በማስለፍ ማለት ነው።

‘ጉባሄአዊነት’ ኃላፊነት በተጣለባቸው ሰዎች መካከል ያለው ትብብር (ኮሌጃሊት) በአንድ ክልል ውስጥ ባሉ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የኅብረት ደረጃ በኤጲስ ቆጶሳት አገልግሎት እና በዓለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የኅብረት ደረጃ የቤተ ክህነት ሲኖዶሳዊነት የሚገለጥበት እና እውን የሚሆንበት ልዩ መልክ ነው። ትክክለኛው የሲኖዶሳዊነት መገለጫ የጳጳሳትን ወይም ኃላፊነት በተጣለባቸው ሰዎች መካከል ያለው ትብብር አገልግሎት መለማመድን ይጨምራል።

ምንጭ፡ የካቶሊክ ዓለም አቀፍ የነገረ መለኮት ኮሚሽን፣ ሲኖዶሳዊነት በቤተክርስቲያን ሕይወት እና ተልዕኮ ውስጥ በሚል አርእስ ይፋ ካደርገው ሰነድ ከአንቀጽ 1-7 ላይ የተወሰደ።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ አባ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ ቫቲካን

03 March 2023, 14:11