ፈልግ

በአሜሪካ ናሽቪል ከተማ በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት የተፈጸመ የተኩስ ጥቃት በአሜሪካ ናሽቪል ከተማ በሚገኝ የግል ትምህርት ቤት የተፈጸመ የተኩስ ጥቃት  (AFP or licensors)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በናሽቪል ትምህርት ቤት በተገደሉት ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በአሜሪካ ለናሽቪል ሀገረ ስብከት ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ዮሴፍ ማርክ የቴሌግራም መልዕክት ረቡዕ መጋቢት 20/2015 ዓ. ም. ልከዋል። ቅዱስነታቸው ለጳጳሱ በላኩት መልዕክት፣ ቴኔሲ በተባለ የአሜሪካ ግዛት፣ ናሽቪል ከተማ ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት በተከፈተ ተኩስ ለተገደሉት ሰዎች የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል። ጥቃቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተከታታይ ሲከሰቱ ከቆዩ የተኩስ ጥቃቶች መካከል አንዱ እና በአገሪቱ ከፍተኛ ድንጋጤን ያስከተለ ነው ተብሏል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅርብ ጊዜያት ውስጥ በአሜሪካ ትምህርት ቤቶች ከተፈጸሙት የትምህርት ቤት ጥቃቶች መካከል አንዱ በሆነው በዚህ ጥቃት ሦስት የዘጠኝ ዓመት አዳጊ ልጆችን ጨምሮ የስድስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱ የተነገረ ሲሆን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአደጋው የተሰማቸውን ሐዘን ለናሽቪል ሀገረ ስብከት ጳጳስ አቡነ ዮሴፍ ማርክ ስፓልዲንግ መልዕክት በመላክ ገልጸዋል።     

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በናሽቪል ከተማ በሚገኝ፣ ባለቤትነቱ የግል በሆነው የክርስቲያን ትምህርት ቤት በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ የሰው ሕይወት በመጥፋቱ የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን የገለጹበትን መልዕክት፣ የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፔዬትሮ ፓሮሊን በቅዱስነታቸው ስም ፈርመዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለናሽቪል ሀገረ ስብከት ጳጳስ ለአቡነት ዮሴፍ ማርክ በላኩት መልዕክት፣ "የተሰማቸውን ልባዊ ሐዘን እና በጥቃቱ ሕይወታቸውን ያጡትን እና የተጎዱትን በሙሉ በጸሎት የሚያስታውሷቸው መሆኑን" ለወላጅ ቤተሰቦቻቸው እንዲያስተላልፉ ጠይቀዋል። ቅዱስነታቸው በማከልም፣ በጥቃቱ የሞቱትን ሕጻናት እና ጎልማሶች ከማኅበረሰቡ ጎን በመሆን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የፍቅር እቅፍ እንዲቀርቡ በማለት በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመጨረሻም፣ ሐዘን ውስጥ ለሚገኙት ቤተሰቦች ላይ የመንፈስ ቅዱስን ጽናትን እና ጥንካሬ በጸሎት ጠይቀው፣ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ እና በእምነታቸው ኃይል ከደረሰባቸው ጉዳት እንዲፈወሱ እና ከክፋት እንዲያመልጡ ጸልየውላቸዋል።

የተከሰተው ምን ነበር?

ማክሰኞ መጋቢት 19/2015 ዓ. ም. የ28 ዓመት ዕድሜ ሴት፣ ቴኔሲ በተባለ የአሜሪካ ግዛት፣ ናሽቪል ከተማ በሚገኝ አንድ የግል ትምህርት ቤት ተኩስ በመክፈት የስድስት ሰዎች ሕይወት አጥፍታለች። የአካባቢው ፖሊስ በጥቃቱ ሦስት የዘጠኝ ዓመት አዳጊ ልጆችን ጨምሮ የስድስት ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን በመረጃው አረጋግጧል።

ጥቃቱ ሲፈጸም በሥፍራው ከነበሩት የትምህርት ቤቱ ሠራተኞች መካከል አንዷ የሆነች የ61 ዓመቷ መምህርት ሲይሺያ ፒክ፣ የ60 ዓመቷ የትምህርት ቤቱ ሃላፊ ካትሪን ኮንስ እና ሌላኛው የ61 ዓመቱ የጽዳት ሠራተኛ ማይክ ሂል እንደነበር በትምህርት ቤቱ ድረ ገጽ ላይ ተገልጿል።

ጥቃቱን የፈጸመች የ 28 ዓመቷ ወጣት በአዕምሮ መታወክ ሕመም እንክብካቤ እየተደረገላት የምትገኝ ስትሆን፣ ከወላጆቿ ጋር በምትኖርበት ቤት ውስጥ የደበቀቻቸው እና በሕጋዊ መንገድ የገዛቻቸው ሰባት የጦር መሪያዎች እንደነበሯት ታውቋል። ወላጆቿም ልጃቸው የጦር መሣሪያ መያዝ እንደሌለባት ይሰማቸው እንደነበር ተገልጿል።

የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪ እንደነበረች የሚነገርላት አጥቂዋ ፖሊስ እራሱን ለመከላከል በከፈተው ተኩስ መገደሏ ታውቋል። ጥቃቱ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2023 ዓ. ም. አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ወይም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ቢያንስ አንድ ሰው የቆሰለበት 19ኛው የተኩስ ጥቃት እንደሆነ ተገልጿል።

30 March 2023, 16:06