ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፥ የደቡብ ሱዳን የረጅም ዓመታት ቁስል ለዕድገት መንገድ ሊከፍት ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችኮስ በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚያካሂዱትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ዓርብ ጥር 26/2015 ዓ. ም. ወደ ደቡብ ሱዳን በመጓዝ በዚያች አገርም የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ጀምረዋል። በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከቀኑ ስምንት ሰዓት ከአርባ አምስት ደቂቃ ላይ ወደ ዋና ከተማ ጁባ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ደርሰዋል። ከቅዱስነታቸው ጋር ደቡብ ሱዳንን የሚጎበኙት በእንግሊዝ የካንተርበሪው የአንግሊካን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጀስቲን ዌልቢ እና የስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ መሪ ቄስ ያን ግሪንሺልድስ መሆናቸው ታውቋል። ሦስቱ የሐይማኖት መሪዎች በደቡብ ሱዳን የሚያደርጉት ጉብኝት የክርስቲያኖችን አንድነት የሚያሳድግ የጋራ ንግደት እንደሆነ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በጁባ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ባደረጉት ንግግር፣ ያለ ማወላወል አገሪቱን ወደ አንድነት ጎዳና ቶሎ መመለስ እንደሚገባ ተናግረው፣ እርስ በርስ ተግባብተን የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ይህ እንዳይሆን የሚከለክሉ እንቅፋቶችን በሙሉ ማሸነፍ እንደሚገባ፣ የጦር መሣሪያዎችን ወደ አገሪቱ ማስገባት እንዲቆም፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በሕዝቦች ልማት ሂደት ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆን አሳስበዋል። በጁባ ለባለስልጣናቱ ባደረጉት ግልጽ እና ቀጥተኛ ንግግር፣ በደቡብ ሱዳን ሰላም እና መረጋጋት ወርዶ ዕርቅ እንዲደረግ፣ አገሪቱ ሰላምን ለማምጣት የምታደርገው ጉዞ በአመጽ፣ በሙስና እና በድኅነት መደናቀፍ የለበትም ብለዋል።

የሰላም ጉዞ ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍ አይገባም

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በደቡብ ሱዳን ዋና ከተማ ጁባ በተደረገላቸው የክብር አቀባበል ሥነ ሥርዓት ላይ ፊርማቸውን ባኖሩበት ወቅት በጽሑፍ እንደገለጹት፥ የናይል ወንዝ ባለቤት በሆነች በዚያች ምድር ሕዝብ መካከል ሰላም እና እርቅ ወርዶ ብልጽግና እንዲመጣ እጸልያለሁ ብለው፣ ሰላምን ለማምጣት የተጀመረው ጉዞ ለሌላ ጊዜ ሊተላለፍ አይገባም ብለዋል።ለዓመታት የዘለቀው ጦርነት እና ግጭት ማብቂያ የሌለው ይመስላል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በቅርቡ እንዲሁም ትናንትም በአገሪቱ የተከሰተው ከባድ ግጭት የእርቅ ሂደቱን ፍሬ አልባ ከማድረጉ በተጨማሪ የሰላም ተስፋን ሊያጨልም እንደሚችል ገልጸው፣ የደቡብ ሱዳን ሕዝብ ትዕግስት እና መስዋዕትነት የሰላም ዘር እንዲያብብ እና ፍሬን እንዲሰጥ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል። በደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን ማካሄድ በጀመሩበት በትላንትናው ዕለት መሣሪያ የታጠቁ ሰዎች ባደረሱት ጥቃት ከብቶች የተሰረቁበትን እና ቢያንስ ለ21 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የሆነውን ወረራ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጠቅሰዋል።

ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ
ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ

ደቡብ ሱዳን የሚያስፈልጋት አባቶች እንጂ ጌቶች አይደሉም

ቅዱስነታቸው ለኮንጎ ዴሞክራሲዊት ሪፐብሊክ ሕዝብ እንዳስታወሱት ሁሉ፣ “ደቡብ ሱዳን በዕጽዋት ብቻ ሳይሆን በከርሰ ምድር ሀብቷ እና የእግዚአብሔር ስጦታ የሆነው የዓባይ ወንዝ የሚፈስባት አገር ነች” ብለው፣ የአገሪቱ ባለ ሥልጣናት ከሕዝባቸው ጋር ማኅበራዊ ሕይወትን የሚጋሩ፣ ለዚያች ለጋ አገር ሕዝቦች አባቶች እንጂ ጌቶች አለመሆናቸውን፣ የብልጽግና እና የሰላም ምንጮች እንደመሆናቸውም ማኅበራዊ ሕያወትን ለማደስ የተጠሩ፣ ለዘላቂ ውድቀት ሳይሆን ለተረጋጋ የዕድገት ደረጃዎች መጠራታቸውን አስረድተዋል።

የደቡብ ሱዳን የረጅም ዓመታት ቁስል ለዕድገት መንገድ ሊከፍት እንደሚገባ አጥብቀው የጠየቁት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ አገሪቱን ለትውልድ ማስተላልፍ እንደሚገባ አደራ ብለው፣ አመፅ የታሪክን ሂደት ወደ ኋላ እንደሚመልስ ተናግረዋል። ደቡብ ሱዳን ወደ መቃብር ሥፍራነት ሳይሆን እንደገና የምታብብ የአትክልት ስፍራነት እንድትለወጥ በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

አሁን ጊዜው የጥፋት ሳይሆን የግንባታ ነው!

ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ተማጽኖአቸውን ያቀረቡት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በአገሪቱ ውስጥ ደም መፍሰስ፣ ግጭት እና እርስ በርስ መወነጃጀል እንዲያበቃ፣ በቂ ግፍ የተቀበለው የደቡብ ሱዳን ሕዝብ የሰላም ፍላጎት መልስ ሊያገኝ ይገባል ብለዋል። ጊዜው አሁን የጥፋት ሳይሆን የግንባታ እና የዕድገት እንደሆነ የገለጹት ቅዱስነታቸው ሳያወላወሉ አገሪቱን ወደ አንድነት ጎዳና መመለስ እንደሚገባ ተናግረው፣ የአገሪቱ ፕሬዚደንት በኡጋንዳ ያደረጉትን የሰላም ውይይት በማስታወስ፣ ይህን የሰላም ጥረታቸውን ሊቀጥሉ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ሪፐብሊክ ተብሎ መጠራት ብቻ ሳይሆን መሆን ይገባል!

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ሐምሌ 9/2011 ዓ. ም. ነጻነቷን ላወጀች በዓለም ትንሿ አገር ደቡብ ሱዳን የሪፐብሊክነት የግዛት ትርጉም ምን እንደሆነ ያስረዱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የፖለቲካ ስልጣንን እንደ አገልግሎት በማብራራት ለራስ ጥቅም ብቻ መሥራት የተደበቅ ሁልጊዜ ፈተና መሆኑን አስረድተው፣ አገሪቱ ሪፐብሊክ ተብላ መጠራቷ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን ከመሠረታዊ ፍጆታዎች ጀምሮ እግዚአብሔር ይህችን ምድር የባረካት የተትረፈረፉ ሃብቶች ለጥቂቶች ጥቅም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን የሁሉም ሰው መብት እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ተመልሶ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል። “የአንድ አገር ሪፐብሊክነት እና መረጋጋት ዋስትናው ዲሞክራሲያዊ ዕድገት ነው” ሲሉ የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ 2ኛ እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ 23ኛን በመጥቀስ፣ የሁሉንም ሰው ሰብዓዊ መብቶች ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ
ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ

አዲስ ምዕራፍ የምንጀምርበት ጊዜው አሁን ነው።

የሰላሙ ሂደት ወደ ፊት ሊቀጥል የሚችልበት ተስፋ መኖሩን በድጋሚ የገለጹት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የሰላም ዕድሎችን በመጠቀም በፍጥነት ወደ ለውጥ መጓዝ እንደሚገባ የሰላም ውይይቶችን እንደገና በመጀመር የጥላቻ፣ የጎሳ፣ የክልል እና የብሔር ልዩነቶችን ማሸነፍ ይገባል ብለዋል። “ከቃላት ወደ ተግባር የምንሸጋገርበት ጊዜው አሁን ነው!” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ አስቸኳይ እና አስፈላጊ ለውጥ ለማምጣት ቃል የምንገባበት ጊዜው አሁን እንደሆነ፣ የሰላም እና የእርቅ ሂደቱ አዲስ ጥረትን እንደሚፈልግ በማስረዳት፣ እርስ በርስ በመገባባት የሰላም ስምምነትቱን ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ጎሳዊ ግጭት ሳይሆን ወጣቶችን በሰላም ጥረት ማሳተፍ

“እርስ በርስ መከባበር፣ መተዋወቅ እና የጋር ውይይት ሦስቱ ወቅታዊ ርዕሦች ናቸው” ያሉት ቅዱስነታቸው፣  ከእያንዳንዱ ግፍ ጀርባ ቁጣ እና ቂም ካለ፣ ከእያንዳንዱ ቁጣ እና ንዴት ጀርባ የመቁሰል አደጋ ካለ፣ የውርደት እና የበደል ትዝታ ካለበት፣ ከዚህ ለመውጣት ብቸኛው መንገድ እርስ በእርስ በሰላማዊ መንገድ መገናኘት ብቻ ነው ብለው፣ ቦታን በመስጠት ሌሎችን እንደ ወንድም እና እንደ እህት መቀበል፣ ለሰላም ሂደት አስፈላጊ የሆነው ይህ አስተሳሰብ ለኅብረተሰቡ የተቀናጀ ልማትም አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። “የአንድ አገር ሥልጣኔ የሚለካውም ለወጣቶች በአደራ በሚሰጥ ወሳኝ ሚና ነው” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ ወጣቶች ያለ ምንም ፍርሃት እርስ በእርስ ተገናኝተው የሚወያዩበት ነፃ መድረክ እንደሚያስፈልጋቸው እና ሴቶች በፖለቲካ እና በውሳኔ አሰጣጥ ሂደቶች ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል ብለው፣ ብዙውን ደህንነታቸው ባልተጠበቀበት ሁኔታ ውስጥ ለሚሠሩ ሚስዮናውያን እና ግብረሰናይ ድርጅት ሠራተኞች ድጋፍ እንዲደረግላቸው አደራ ብለዋል።

ሙስናን እና ድህነትን መዋጋት፣ የተፈናቀሉትን መንከባከብ

በአካባቢ ላይ የሚደርስን ውድመት፣ ስግብግብነትን የደን መጨፍጨፍን ያስታወሱት ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ በኮንጐ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ የተንሰራፋውን ሙስና በማስታወስ፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚደረግ ድብቅ ሙከራ እና ግልጽነት ማጣት፣ እነዚህ በሙሉ ሰብዓዊ ማኅበረሰብን የሚበክሉ መሆናቸውን ገልጸው፣ ከምንም በላይ ጥላቻን፣ መለያየትን፣ ብጥብጥን እና ሥር የሰደደውን ድህነትን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስተዋፅኦ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉ፣ የሰው ልጅ አብሮ በሰላም መኖር የሚችለው የጦር መሣሪያ ትጥቅን መፍታት ከተቻለ እና ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኩል ግልጽ ውግዘት ያለ እንደሆነ ብለው፣ በዚህ መንገድ የድጋፍ እና የልማት አውታሮችን ማንቃት እና ማጠናከር ይቻላል ብለዋል። በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ሊታገድ ይገባል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እገዳ ቢደረግም, በደቡብ ሱዳን እና በአካባቢው አገራት ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር መኖሩን ገልጸዋል። ለደቡብ ሱዳን የሚያስፈልጋት የጦር መሣሪያ ሳይሆን የማኅበራዊ ኑሮ ዕድገትን የሚያረጋግጡ ልማቶች፣ በቂ የጤና ፖሊሲዎች፣ ወሳኝ መሠረተ ልማቶች መሆናቸውን ገልጸው፣ ሕጻናት የዚህችን አገር የወደፊት ዕጣን በእጃቸው ለማስጨበጥ ትምህርት ብቸኛው መንገድ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ
ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ
ከደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ጋር የተደረገ ስብሰባ
04 February 2023, 16:33