ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ለጥቃት ሰለባዎች ንግግር አድርገዋል ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በኮንጎ ለጥቃት ሰለባዎች ንግግር አድርገዋል   (VATICAN MEDIA Divisione Foto)

ከጥቃት የተረፉ የኮንጎ ሕዝቦች አሳዛኝ ታሪካቸውን ለር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አካፈሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በጦርነት ከተመሰቃቀለው የኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል በሕይወት የተረፉ ሰዎችን በኪንሻሳ ተገናኝተው፣ አሳዛኝ ምሥክራቸውን ካዳመጡ በኋላ የተፈጸመውን የኃይል ድርጊት አውግዘዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ምሥራቃዊ ክፍል እየተካሄደ ባለው ግጭት በሕይወት የተረፉ ሰዎች የጅምላ ግድያ እና የአካል መጉደል፣ ጠለፋ እና የዘመድ መሰወር፣ ተከታታይ መደፈር እና ወሲባዊ ባርነት እንዲሁም በተጨናነቀ እና ንጽህና በጎደለው የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮች ታሪካቸውን ለቅዱስነታቸው አካፍለዋል።

ረቡዕ ጥር 24/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ጋር በተካሄደው ስብሰባ ላይ የተሳተፉት ሰዎች፣ ጦርነቱ እና የተፈጥሮ አደጋዎች በአሰቃቂ ሁኔታዎች ውስጥ እንዲያልፉ ቢያደርጋቸውም፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ተስፋ አስፈላጊነት በመናገር ከአደጋው የተረፉት ሰዎች ሁሉ ተስፋቸውን ሲገልጹ፡- “ያለፈውን የጨለማ ጊዜን ወደ ኋላ ትተን መልካም የወደፊት ጊዜን መገንባት እንፈልጋለን” ብለዋል።

“ከጎናችሁ ነኝ!”

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለጥቃት ሰለባዎች ባደረጉት ንግግር፥ “በዓይኖቻችሁ ያያችሁትን እና በግል ያጋጠማችሁትን ኢ-ሰብአዊ ጥቃት ስንሰማ አሁንም እንደነግጣለን” ብለው፣ “ይህን ስንሰማ በዝምታ ከማልቀስ ሌላ የምንለው ቃል የለንም” ብለዋል። ቅዱስነታቸው በመጀመሪያ የሀገሪቱን ምሥራቃዊ ክፍል ለመጎብኘት ያሰቡ ቢሆንም ነገር ግን በአካባቢው የሚታየው የጸጥታ ሁኔታ እንዳስቻላቸው ታውቋል። ለክልሉ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከጎናቸው መሆናቸውን በመግለጽ፣ እንባችሁ እንባዬ፣ ሕመማችሁ ህመሜ ነው” በማለት ገልጸው በማከል፣ መንደሮቻቸው ወድመውባቸው ለተፈናቀሉት ቤተሰቦች፣ የጦር ወንጀል ለተፈጸመባቸው፣ ከፆታዊ ጥቃት የተረፉት እና ጉዳት ለደረሰባቸው ሕጻናት እና ጎልማሶች ባስተላለፉት መልዕክት፥ አለኝታነታቸውን በመግለጽ የእግዚአብሔርን እንክብካቤ በመካከላቸው ማምጣት እንደሚፈልጉ ገልጸውላቸዋል። በመቀጠልም  በጦር መሣሪያ የተደገፈ አመጽን፣ የሰዎች እልቂትን፣ በኃይል መደፈርን፣ የመንደሮች መውደምን እና መወረርን፣ የእርሻ እና የቀንድ ከብት ዘረፋን፣ ሕገወጥ የሃብት ብዝበዛን እና አገሪቱን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ሙከራ በእግዚአብሔር ስም አውግዘዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአደጋው ከተረፉት ሰዎች አንዱ ጋር
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከአደጋው ከተረፉት ሰዎች አንዱ ጋር

የንጹሃን ደም ጩኸት ይደመጥ!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለሁሉም ሰዎች በተለይም በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ጦርነት ለሚቀሰቅሱት ሰዎች ባቀረቡት ልባዊ ጥሪ፥ የንጹሐን ሰዎች ደም ጩኸት እንዲያዳምጡ፣ ጆሮአቸውን ለእግዚአብሔር እና ለኅሊናቸው ድምፅ ክፍት እንዲያደርጉ፣ የጦር መሣሪያቸውን በማስቀመጥ ጦርነትንም እንዲያቆሙ ተማጽነው፣ በድሆች ላብ መበልፀግ እንዲያበቃ፣ በደም የተለውሰ ገንዘብ መበልፀግ እንዲያቆም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ሰላምን ለማስፈን ምን ማድረግ እንደሚቻል እና ከየት መጀመር እንደሚገባ ባቀረቡት ጥያቄ፣ ምላሹ ‘አይሆንም’ እና ‘አዎ’ በሚሉ ሁለት መንገዶች እንደገና መጀመር እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለአመፅ እና ለሽንፈት እጅ አለመስጠት 

ከሁሉ አስቀድሞ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ፣ ሁልጊዜ እና በሁሉም ሥፍራ ሁከትን መቃወም አለብን ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ከዚሁም ጋር ሁከትን መቃወም ማለት ከጥቃት መራቅ ማለት እንደሆነ ገልጸው፣ ስግብግብነት፣ ምቀኝነት እና ከሁሉም በላይ ቂምን ጨምሮ የዓመፅን ምንጭ ማስወገድን እንደሚጨምር አስረድተዋል። ስብሰባው ላይ ለተገኙት እና ከጥቃት ለተረፉት ሰዎች ባሰሙት ንግግር፣ በስብሰባው የቀረቡ ደፋር ምስክሮቻችን በመጠቆም ሁሉም ሰው ልቡን ከአመጽ እና ከጥቃት ነጻ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል። በመቀጠልም በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በሙሉ ተስፋን እንዳይቆርጡ፣ የተሻለ የወደፊት ጊዜን ከመገንባት ወደ ኋላ እንዳይሉ አደራ ብለው፣ “አመጽ በተስፋፋበት የአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍልም እንኳ ቢሆን ሰላም ማንገሥ እንደሚቻል በማመን ለክፋት ሳንሸነፍ በርትትን እንሥራበት” ብለዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሕይወት የተረፉትን አነጋግረዋል
ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በሕይወት የተረፉትን አነጋግረዋል

እርቅ እና ተስፋ ማድረግ

በመቀጠል አዎንታ የሚገለጥባቸውን ሁለት መንገዶች የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ እርቅን አዎንታ በመግለጽ መጀመር እንደሚገባ ከጥቃቱ በሕይወት ለተረፉት በድጋሚ ሲናገሩ፣ እርስ በርስ ይቅር ለመባባል እና አለመግባባቶችን በሰላም ለመፍታት ላሳዩት ፍላጎት አወድሷቸዋል። መልካምነት፣ ፍቅር እና እርቅ እነዚህ በሙሉ ከክፋት የበለጠ ኃይለኞች መሆቸውን ገልጸው፣ እውነታውን ከውጭ ሳይሆን ከውስጥ እንደሚለውጡ በማስረዳት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ እንዳደረገው፣ ክፋትን በፍቅሩ እንደለወጠው ሁሉ እኛም ክፋትን  ማሸነፍ የምንችለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው” ብለዋል።

በመጨረሻም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ተስፋ ማድረግን እንደሚገባ፣ የተስፋ ምንጭም ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን አስረድተዋል። “ከኢየሱስ ጋር ከሆኑ ክፋት በሕይወት ላይ ስልጣን እንደሌለው በመግለጽ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞት ላይ ድል መቀዳጀቱን ተናግረዋል። በኮንጎ ምሥራቃዊ  ክፍል ለሚገኙት ወንድሞች እና እህቶች ይህ ተስፋ ለእነርሱ የታሰበ መሆኑን ገልጸው፣ ይህን የመምረጥ መብት እንዳላቸው በመግለጽ፣ ከቀን ወደ ቀን በትዕግሥት ከሚዘራ ሰላም የሚገኝ መብት መሆኑንም ተናግረዋል። ሰላምን መዝራት የሚጠቅም እና የግል ጥቅምን ከማሰብ ነፃ የሚያደርግ እንዲሁም ሕይወታችንን በልግስና እንደሚለውጥ እና የተስፋ ዘርን የሚዘራ እግዚአብሔርን እንድንመስል ያደርገናል ብለዋል።

የሰላም አብሳሪዎች መሆን

ቅዱስነታቸው በመቀጠልም ለሰላም የሠሩትን አመስግነው፣ ሰላምን ለመዝራት ሕይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት ተስፋን የዘሩት መስዋዕታቸው አይጠፋም ብለዋል። ንግግራቸውን ሲያጠናቅቁ ለኮንጎ ምሥራቃዊ ክፍል ሕዝቦች ያላቸውን ቅርበት ደግመው በመግለጽ፣ የእርቅ አምላክ እና በእርሱ ለሚያምኑት በሙሉ የተስፋ አምላክ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  አገራቸውን እንዲባርክ፣ ጽናቱንም እንዲሰጣቸው በመለመን ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የጥቃት ሰለባ ከሆኑት ጋር ተገናኝተዋል
02 February 2023, 16:30