ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አብረዋቸው ወደ አፍሪካ የተጓዙ ጋዜጠኞችን በማመስገን ሰላምታ አቅርበውላቸዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ አብረዋቸው ወደ አፍሪካ የተጓዙ ጋዜጠኞችን በማመስገን ሰላምታ አቅርበውላቸዋል 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የሰሃራ በረሃን ሲያቋርጡ የሞቱ ስደተኞችን በጸሎት አስታወሱ

ርዕሠ ሊቃነ ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን የአውሮፕላን ጉዞ በጀመሩበት ወቅት አብረዋቸው ለሚጓዙት ጋዜጠኞች ሰላምታቸውን አቅርበዋል። በመቀጠልም የሰሃራ በረሃን ሲያቋርጡ ሕይወታቸውን ያጡ በርካታ ስደተኞችን እና ከዚያ በኋላም በየወህኒ ቤቶቹ የሚሰቃዩትንም አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው አብረዋቸው ወደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ከሚጓዙት ጋር ሆነው በጸሎት ያስታወሷቸው ሰዎች፣ የተሻለ እና አዲስ ሕይወት ፍለጋ ወጥተው በበረሃ ወድቀው የቀሩትን ስደተኞችን ለማስተወስ እንደሆነ ተገልጿል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከሮም ተነስተው ወደ ኮንጎ ዴሞክራሲውት ሪፐብሊክ ዋና ከተማ ኪንሻሳ በሚያደርጉት 40ኛው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉዟቸው ደቡብ ሱዳንንም እንደሚጎበኙት ታውቋል። በአውሮፕላን የሰሃራ በርሃን ሲያቋርጡት የተመለከቱት በረሃማው አፈር በውሃ ጥም እና በሚደርስባቸው ግፍ ተሰቃይተው በአሸዋ ተቀብረው የቀሩ የበርካታ ሰዎች ሕይወትን ያስታወሳቸው እንደሆነ ታውቋል።

ለመንገደኞቹ “በዚህ ሰዓት የሰሃራ በረሃን እየተሻገርን እንገኛለን” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ስደተኞች በረሃውን ካቋረጡ በኋላ ወደ ሜዲትራኒያን ባሕር ሲደርሱ ብዙዎች እንደሚታመሙ እና ለእስር ተዳርገው እንደሚሰቃዩ በማስታወስ፣ ለእነዚያ ሰዎች በሙሉ እንጸልይላቸው ብለዋል።

ለአብሮነታቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ የሕሊና ጸሎት ከመደረጉ በፊት ከ12 አገራት ለተወጣጡ እና ከሁለት አፍሪካውያን ጋር ወደ 75 ለሚጠጉ ጋዜጠኞች ባደረጉት ንግግር፣ ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረውን ሐዋርያዊ ጉዞ አብረው በመጓዛቸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። መልካም ጉዞን በማድረግ ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ኮንጎ ውስጥ ወደ ጎማ ክፍለ ሀገር ጭምር ለመሄድ ቢፈልጉም በአካባቢው ያለው የጸጥታ ሁኔታ እንዳልፈቀዳቸው ገልጸዋል። በመሆኑም ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በሁለቱ አገራት መዲና በሆኑት በኪንሻሳ እና በጁባ ብቻ የተገደበ እንደሆነ ገልጸው፣ ጋዜጠኞቹ አብሮአቸው በመሆናቸው እና በሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ይፋ የሚያደርጓቸው ምስሎች፣ ሃሳቦች እና የተለያዩ አስተያየቶች ጉብኝቱን በቅርብ ለመከታተል ፍላጎት ላደረባቸው በሙሉ የሚጥቅም እንደሆነ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። 

ቅዱስነታቸው ከዚህ በፊት ባደረጓቸው ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ወቅት በአውሮፕላኑ ውስጥ የሚገኙትን እየተዘዋወሩ ሰላምታቸውን የሚያቀርቡ ቢሆንም በዚህ ጉዞ ወቅት ግን በእግር ሕመም ምክንያት ይህን ማድረግ አለመቻላቸውን ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በጉዞው ላይ አብረዋቸው ከነበሩት ሰዎች የተለያዩ ስጦታዎችን የተቀበሉ ሲሆን፣ ስጦታዎችን ካቀረቡላቸው ጋዜጤኞች መካከል፣ የስፔን ካቶሊካዊ ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ቃል አቃባይ እና የሬዲዮ ኮፕ ጋዜጠኛ ኢቫ ፈርናንዴዝ ስትሆን፣ ለቅዱስነታቸው ያቀረበችው ስጦታ ከጎማ ከተማ በስተሰሜን 12 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ከናይራጎንጎ እሳተ ገሞራ የተገኘ ኮልታን የተሰኘ ማዕድን ቁራጭ ሲሆን፣ እያንዳንዱን ሁለት ኪሎ ግራም ለማውጣት ሲሉ ሁለት ሰዎች እንደሚሞቱ ገልጻለች።

31 January 2023, 16:07