ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኪንሳሻ “ንድጂሊ” አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የክብር አቀባበል ተደጎላቸዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ በኪንሳሻ “ንድጂሊ” አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የክብር አቀባበል ተደጎላቸዋል  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በሰላም ደርሰዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካ የሚያደርጉትን 40ኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር ወደ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በሰላም ደርሰዋል። ይህ ቅዱስነታቸው በአፍሪካ አህጉር የሚያደርጉት አምስተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንቸስኮስ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለመጀመር ወደ ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ በሰላም ደርሰዋል። በኪንሳሻ በሚገኝ “ንድጂሊ” ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የደረሱት በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት ከሰላሳ ሦስት ደቂቃ ላይ መሆኑ ታውቋል። ከሮም ፊውሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ. ም. የተነሱት በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከሃያ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ አብረዋቸው የተጓዙት ጋዜጠኞች ቁጥር ከሰባ እንደሚበልጥ ተነግሯል። የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ መዳረሻ በሆነች ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ከማክሰኞ ጥር 23-26/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሚቆዩ ታውቋል። ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ በ1985 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ያችን አገር ጉብኝተው እንደነበር ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካ አህጉር ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርጉ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ ሲሆን፣ በኪንሳሻ በሚገኝ “ንድጂሊ” አውሮፕላን ጣቢያው ሲደርሱ የክብር አቀባበል ተደጎላቸዋል። በመቀጠልም የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፌሊክስ ቲሺሴኪዲን በቤተ መንግሥታቸው ከጎበኟቸው በኋላ ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች እና ዲፕሎማሲያዊ አካላት ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በአፍሪካ አህጉር የሚያደርጉትን ይህን አምስተኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው መጪው እሑድ ጥር 28/2015 ዓ. ም. ወደ ሮም ሲመለሱ፣ መንበረ ጵጵስናቸውን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ የጎበኟቸው አገራት ቁጥር 60 እንደሚደርስ ታውቋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. በኬንያ ፣ በኡጋንዳ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በ 2017 ዓ. ም. በግብፅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ከዚያም በመጋቢት ወር 2019 ዓ. ም. በሞሮኮ፣ በኋላም በመስከረም ወር 2019 ዓ. ም. በሞዛምቢክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሸስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ኮንጎን ለመጎብኘት የነበራቸውን ምኞት ማሳካት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት በሐምሌ ወር 2014 ዓ. ም. በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ሊያደርጉት ያቀዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት በከባድ የጉልበት ሕመም ምክንያት ለሌላ ጊዜ መዛወሩ ይታወሳል። ይሁንና በጊዜው በስማቸው ሁለቱንም አገራት እንዲጋበኟቸው በማለት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊንን የላኳቸው ሲሆን፣ በወቅቱ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረግ ባለመቻላቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸው፣ ሳይዘገይ በሁለቱም አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

ከዓለም የካቶሊክ ምዕመናን መካከል 20 በመቶው የሚገኘው በአፍሪካ አህጉር ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ታውቋል።

31 January 2023, 17:13