ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ጀምረዋል ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ጀምረዋል 

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ኮንጎ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን ሐዋርያዊ ጉዞ ጀምረዋል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ወደ ጎንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና ደቡብ ሱዳን የሚያደርጉትን 40ኛ ዓለም አቀፍ ሐዋርያዊ ጉዞ ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ. ም. ጀምረዋል። ቅዱስነታቸው በሁለቱም አገራት የሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እርቅን እና ሰላምን ያማዕከለ እና ለክርስቲያኖች አንድነት ሲባል የተካሄደ 5ኛው የአፍሪካ ሐዋርያዊ ጉብኝት እንደሆነ ተነግሯል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ሁለቱ የአፍሪካ አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ከሮም ፊውሚቺኖ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የተነሱት ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ. ም. በአገሩ የሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከሃያ ዘጠኝ ደቂቃ ላይ ሲሆን፣ አብረዋቸው ከሰባ የሚበልጡ ጋዜጠኞች መጓዛቸው ተነግሯል። ቅዱስነታቸው የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝት የመጀመሪያ መዳረሻ አገር ወደ ሆነች ኮንጎ ኪንሳሻ “ንድጂሊ” ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ የሚደርሱት፣ በአገሪቱ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በዘጠኝ ሰዓት እንደሆነ የጉዞአቸው መርሃ ግብር አመልክቷል። 

ለስደተኞች፣ ለጥገኝነት ጠያቂዎች እና በጦር ሚዳ ለወደቁት ያላቸውን ቅርበት ገልጸዋል

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ማክሰኞ ጥር 23/2015 ዓ. ም. በቫቲካን ውስጥ ከሚገኝ የቅድስት ማርታ ጳጳስዊ መኖሪያቸው ከመነሳታቸው አስቀድመው፣ ሮም ውስጥ በኢየሱሳውያን ማኅበር በሚመራ አስታሊ የስደተኞች ማዕከል ድጋፍ ከሚደረግላቸው አሥር የኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፓብሊክ እና የደቡብ ሱዳን ስደተኞች፣ ጥገኝነት ጠያቂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተዋል። ስደተኞችን ከቅዱስነታቸው ጋር ያገናኟቸው፣ የር. ሊ. ጳ. በጎ አድራጎት ሥራ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ፣ ብጹዕ ካርዲናል ኮንራድ ክራዬቪስኪ መሆናቸው ታውቋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ወደ አውሮፕላን ጣቢያው እንደደረሱ፣ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የሰማዕታት መታሰቢያ ሐውልት በመሄድ፣ ኅዳር 2/1954 ዓ. ም. ኮንጎ ውስጥ ኪንዱ በተባለ ሥፍራ የወደቁ 13 የጣሊያን አየር ኃይል አባላት እና በአገሪቱ በተቀሰቀሱት የእርስ በእርስ ጦርነቶች የተገደሉትን፣ ሰብዓዊ ዕርዳታን በማቅረብ እና የሰላም ተልዕኮን በመወጣት ላይ እያሉ ሕይወታቸውን ያጡትን በሙሉ በጸሎት አስታውሰዋል።

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ወደ ዋና ከተማዋ ኪንሻሳ ሲደርሱ የክብር አቀባበል የሚደረግላቸው ሲሆን፣ ቅዱስነታቸው በመቀጠልም የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ክቡር አቶ ፌሊክስ ቲሺሴኪዲን በቤተ መንግሥታቸው ከጎበኟቸው በኋላ ለአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለ ስልጣናት፣ ለሕዝብ ተወካዮች እና ዲፕሎማሲያዊ አካላት ንግግር እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በአፍሪካ አህጉር የሚያደርጉትን ይህን አምስተኛ ሐዋርያዊ ጉብኝት መጪው እሑድ ጥር 28/2015 ዓ. ም. ሲጠናቀቅ፣ መንበረ ጵጵስናቸውን ከያዙበት ጊዜ አንስቶ የጎበኟቸው አገራት ቁጥር 60 እንደሚደርስ ታውቋል። ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2015 ዓ. ም. በኬንያ ፣ በኡጋንዳ እና በመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ በ 2017 ዓ. ም. በግብፅ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ከዚያም በመጋቢት ወር 2019 ዓ. ም. በሞሮኮ፣ በኋላም በመስከረም ወር 2019 ዓ. ም. በሞዛምቢክ፣ በማዳጋስካር እና በሞሪሸስ ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።

ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየ ጉብኝት ነው!

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከዚህ በፊት በሐምሌ ወር 2014 ዓ. ም. በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በደቡብ ሱዳን ሊያደርጉት ያቀዱት ሐዋርያዊ ጉብኝት በከባድ የጉልበት ሕመም ምክንያት ለሌላ ጊዜ መዛወሩ ይታወሳል። በጊዜው ቅዱስነታቸው በስማቸው ሁለቱንም አገራት እንዲጋበኟቸው በማለት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊንን የላኳቸው ሲሆን፣ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ባለመቻላቸው የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸው፣ ሳይዘገይ በሁለቱም አገራት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ከፍተኛ የክርስቲያን ቁጥር በሚገኝባት ደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት ለዓመታት ሲገልጹ ቢቆዩም፣ ነገር ግን በአገሪቱ በሚታየው አለመረጋጋት እና በኮቪድ-19 ወረርሽኙ ምክንያት ዕቅዳቸው ሳይሳካ መቆየቱ ታውቋል። ቅዱስነታቸው እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ ወር 2019 ዓ. ም. ለደቡብ ሱዳን የፖለቲካ መሪዎች እና ለአገሪቱ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች በቫቲካን ውስጥ የሱባኤ እና የጸሎት ቀናትን አዘጋጅተው ማስተናገዳቸው ይታወሳል። በቅድስት ማርታ ቤተ ጸሎት በቀረበው የሱባኤ እና የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመንግሥት ባለስልጣናት እግር ላይ ወድቀው ለሰላም እንዲሠሩ መማጸናቸው ይታወሳል።

የክርስቲያኖችን አንድነት ማዕከል ያደረገ ንግደት ነው

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ የዚህ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ መዳረሻ አገር በሆነች ኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ ከማክሰኞ ጥር 23-26/2015 ዓ. ም. ድረስ እንደሚደርጉ ታውቋል። ከዚህ በፊት እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ በ1985 ዓ. ም. የቀድሞ ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በዚያች አገር ሐዋርያዊ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል። ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ ከዚያም ዓርብ ጥር 26/2015 ዓ. ም. ወደ ደቡብ ሱዳን ተጉዘው እስከ ጥር 28/2015 ዓ. ም. ድረስ የሦስት ቀናት ቆይታ የሚያደርጉ ሲሆን፣ የክርስቲያኖችን አንድነት ማዕከል ያደረገ ንግደት የተባለውን የደቡብ ሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው ወደ ሮም ከመመለሳቸው በፊት፣ ከካንተርበሪው የአንግሊካዊ ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ እና ከስኮትላንድ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ጉባኤ ተወካይ ከቄስ ያን ግሪንሺልድስ (ዶ/ር) ጋር በደቡብ ሱዳን በጋራ የወንድማማችነት የሰላም ንግደት እንደሚያደርጉ ታውቋል።

ከዓለም የካቶሊክ ምዕመናን መካከል 20 በመቶው የሚገኘው በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ሲሆን፣ ይህ ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ታውቋል።

31 January 2023, 12:47