ፈልግ

የስደተኞች የባሕር ላይ ጉዞ የስደተኞች የባሕር ላይ ጉዞ  (ANSA)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሜዲቴራኒያ ባሕር፣ ሕዝቦች እና ባሕሎች የሚገናኙበት ሥፍራ ሊሆን ይገባል አሉ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የሜዲቴራኒያ ባሕር አካባቢ አገሮች የጋራ ውይይት ስምንተኛ ጉባኤያቸውን ላካሄዱት አባላት ኅዳር 23/2015 ዓ. ም. መልዕክት አስተላልፈዋል። ጉባኤያቸውን ቅዳሜ ኅዳር 24/2015 ዓ. ም. ላጠቃለሉት የጉባኤው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዓለም አቀፍ ችግሮች ያሏቸውን የዩክሬን ጦርነት እና በዓለማችን ውስጥ የሚከሰት የሕዝቦች ስደት የጋራ መፍትሄዎችን እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሮም የተካሄደው ይህ የሜዲተራኒያን አካባቢ አገሮች የጋራ ውይይት ጉባኤ በሜዲቴራኒያ አካባቢ በሚታዩ አንዳንድ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማካሄድ የፖለቲካ ተቋማት ተወካዮችን፣ ተንታኞችን፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የሚዲያ ባለሙያዎችን አንድ ላይ ያሰባሰበ እንደነበር ተመልክቷል። ቅዱስነታቸው ለጉባኤው ተካፋዮች ባስተላለፉት መልዕክት ለሰው ልጅ መሰደድ የጋራ መፍትሄዎችን ማግኘት አለመቻሉ በተለይም በሜዲትራኒያን ባሕር ላይ የሚከሰት ተቀባይነት የሌለውን የሕይወት መጥፋት እንደሚያስከትል አስረድተው፣የሁሉንም ጥቅም የሚያስጠብቅ ትብብር ጎልቶ መታየት እንዳለበት፣ በተቻለ መጠን የተባበረ እና የተቀናጀ ራዕይ ሊኖር እንደሚገባ በመናገር፣ ከችግር ብቻውን ማምለጥ የሚችል እንደሌለ አስገንዝበዋል።

የዩክሬን ጦርነት ያስከተለው ዓለም አቀፍ ተጽእኖ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ንግግራቸውን በመቀጠል፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ችግሮች ዓለም አቀፍ ይዘት እንዲኖራቸው ማድረጉን ገልጸው፣ ጦርነቱ በወታደራዊውም ሆነ በሲቪል ማኅበረሰብ ላይ፣ በኃይል አቅርቦት፣ በፋይናንስ፣ በሰው ሕይወት እና በምግብ አቅርቦት ላይ የማይገመቱ ጉዳቶችን በማድረስ ችግሩ ዓለም አቀፋዊ ገጽታ እንዲኖረው ማድረጉን አስረድተዋል። አክለውም በማደግ ላይ የሚገኙ የሰሜን አፍሪካ አገራት 80 በመቶው እህል የሚያገኙት ከዩክሬን ወይም ከሩሲያ እንደሆነ ገልጸዋል።    

ስለዚህ በሁለቱ አገራት፣ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት የችግሩን ዓለም አቀፋዊነት ግልጽ ያደርገዋል ብለው፣ ሁኔታው በዓለም አቀፋዊ እይታ መቅረብ እንዳለበት፣ አንድ ችግር ብቻ ሊፈታ እንደማይችል፣ የሰውን ልጅ ስቃይና መጠነ ሰፊ ማኅበራዊ ቀውስን ከግምት ውስጥ ካላስገቡ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅም በመቀነስ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ማድረግ የማይቻል መሆኑን አስረድተዋል።

የሜዲቴራኒያ ባሕር ተልዕኮ

“የሜዲቴራኒያ ባሕር የዕድገት፣ የልማትና የባሕል ጥሪን በተጨባች ሊጠቀም ይገባል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ አንጡራ ሃብቱ ሦስት አህጉራትን እንደሚያገናኝ እና ግንኙነቱ በታሪክ እና ሰዎች ከአንድ ሥፍራ ወደ ሌላ ስፍራ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በጎ ውጤትን ሊያስገኝ እንደሚችል አስረድተዋል። ቅዱስነታቸው ከዚህም ጋር በማያያዝ የሜዲቴራኒያ ባሕር ዛሬ ሕዝቦች እርስ በእርስ የሚገናኙበት፣ ባሕል የሚለዋወጡበት እና የትብብር መድረክ ለመሆን እየታገለ መሆኑን ተናግረዋል።

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ስምንተኛ ጉባኤያቸውን በሮም ላካሄዱት የሜዲቴራኒያ አካባቢ አገሮች የጋራ ውይይት ተካፋዮች ያቀረቡትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፣ “የወንድማማችነት ስሜት ለመገንባት፣ የኢኮኖሚን ብቻ ሳይሆን ስደተኞችን የሚያካትት ሰብዓዊነት ግንኙነቶችን ለመገንባት የሚያስችል የባሕል ግንኙነትን እንደገና ማደስ ያስፈልጋል” በማለት ምክራቸውን ለግሠዋል።

03 December 2022, 16:15