ፈልግ

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል   (Vatican Media)

የር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የብርሃነ ልደቱ ሰሞን የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መርሃ ግብር ይፋ ሆነ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ መጭውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ በሰሞኑ ልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ-ሥርዓቶችን የሚፈጽሙበት መርሃ ግብር ይፋ ሆኗል። የጸሎት ሥነ-ሥርዓት መርሃ ግብሩ የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዘንድ ታኅሳስ 15/2015 ዓ. ም. ምሽት ላይ ከሚቀርብ የብርሃነ ልደቱ የዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ጀምሮ እስከ ታኅሳስ 30/2015 ዓ. ም. ለሕጻናት የሚሰጥ የምስጢረ ጥምቀት ጸጋ ድረስ ያሉ ሥነ-ሥርዓቶችን የሚያካትት መሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ታኅሳስ 15/2015 ዓ. ም. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በሮም የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል ጀምሮ እንደሚያቀርቡ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ይፋ ያደረገውን መርሃ ግብር ዋቢ በማድረግ አስታውቋል። መርሃ ግብሩ ባለፉት ዓመታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ለመከላከል ተብሎ የወጡ ደንቦችን የሚያከብር እንደሆነ አክሎ አስታውቋል።

ለመላው ዓለምንና የሮም ከተማ የሚሰጥ ቡራኬ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ታኅሳስ 15/2015 ዓ. ም. ምሽት ላይ ከሚያሳርጉት የብርሃነ ልደቱ ዋዜማ መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በተጨማሪ እሑድ ታኅሳስ 16/2015 ዓ. ም. ዕኩለ ቀን ላይ ከቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ማዕከላዊ መስኮት በኩል ለሮም ከተማ ነዋሪዎች እና ለመላው ዓለም ቡራኬያቸውን እንደሚያስተላልፉ ታውቋል። ቅዱስነታቸው በተጨማሪም ታኅሳስ 22/2015 ዓ. ም. ከሰዓት በኋላ በአሥራ አንድ ሰዓት ላይ የዓመቱ መጨረሻ የምስጋና ጸሎት እንደሚመሩ ታውቋል።

የጥር ወር የጸሎት ሥነ-ሥርዓቶች (እ. አ. አ.)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ታኅሳስ 23/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ ባዚሊካ ውስጥ በአራት ሰዓት ላይ የሚቀርበውን የእጅግ ቅድስት ድንግል ማርያም የክርስቶስ እናት ዓመታዊ ክብረ በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ መርሃ ግብር አመልክቷል። እንዲሁም ቅዱስነታቸው የላቲን ሥርዓተ አምልኮ የቀን አቆጣጠር በምትከተል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ታኅሳስ 28/2015 ዓ. ም. የሚከበረውን የጥምቀት በዓል መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ ታውቋል። በመጨረሻም እሑድ ታኅሳስ 30/2015 ዓ. ም. የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ለማክበር በቫቲካን ውስጥ በሚገኝ ሲስቲን ጸሎት ቤት ውስጥ የሚቀርበውን መስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በመምራት በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለሚገኙት ሕጻናት የምስጢረ ጥምቀት ጸጋን እንደሚያድሉ የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የአምልኮ ሥነ-ሥርዓት አስተባባሪ ጽሕፈት ቤት ያገኘውን መረጃ ዋቢ በማድረግ አስታውቋል።   

01 December 2022, 10:04