ፈልግ

በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት የተሰበሰቡት ምዕመናን በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባ ለመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት የተሰበሰቡት ምዕመናን  (Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ ሴቶችን ማጥቃት እንደ ጦር መሣሪያነት እየተስፋፋ መምጣቱን ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 18/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን እና መንፈሳዊ ነጋዲያን ካቀረቡት ስብከት በመቀጥለው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው ከመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኋላ ለምዕመናኑ ባደረጉት ንግግር፣ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለማስወገድ በሚል ዓላማ በየዓመቱ ኅዳር 16 ቀን የሚከበረውን ዓለም አቀፍ ቀን በማስታወስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን እንደ ጦር መሣሪያነት የመጠቀም እውነታ መኖሩን የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በጸሎቱ ማጠቃለያ ላይ በአደባባዩ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታቸውን አቅርበው፣ በቅድስት መንበር የእንግሊዝ ኤምባሲ ባስተባበረው የሴቶች አስገድዶ መድፈር ወንጀል ተቃውሞ ሰልፍ ላይ ለተሳተፉ አባላትም ሰላምታቸውን አቅርበውላቸዋል። በሴቶች ላይ የሚፈጸም ጾታዊ ጥቃት እንደ አለመታደል ሆኖ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች እየተስፋፋ መምጣቱን ቅዱስነታቸው ገልጸው፣ ጥቃቱን እንደ ጦር መሣሪያነት የመጠቀም እውነታ መኖሩን አስረድተዋል።

በዓለም ዙሪያ እንደ ጦር መሣሪያነት የሚጠቀሙት ፆታዊ ጥቃት ዓለም አቀፋዊ ችግር መሆኑን ለማብራራት ታስቦ የተዘጋጀውን ሰልፍ በጋራ ያስተባበሩት ዓለም አቀፍ ካቶሊክ ሴቶች ማኅበር እና የቫቲካን የአትሌቶች ማኅበር መሆናቸው ታውቋል። የሰልፉ ተሳታፊዎች እኩለ ቀን ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ የቀረበውን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ተካፍለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለምዕመናኑ ባደረጉት ንግግር ከሦስት ቀናት በፊት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ዙሪያ አንድ ጀርመናዊ ስደተኛ በብርድ ምክንያት ማረፉን ገልጸው በጸሎት አስታውሰውታል። በሮም ጎዳናዎች ለሚገኙት መጠለያ አልባ ሰዎች ዕርዳታን የሚያቀርብ እና በቫቲካን የሚታገዝ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ መኖሩን የቫቲካን ጋዜጣዊ መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ ብሩኒ ገልጸው፣ ሁኔታ በእነዚህ ቀናት ውስጥ በታየው ቀዝቃዛ እና ዝናባማ ምሽቶች የተነሳ፣ ስደተኛው የነበረው የጤና ችግር በማባባስ ለሞት መዳረጉን አስረድተዋል። የመግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር አቶ ማቴዎ በማከልም፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በሮም ከተማ ውስጥ የሚገኙትን ጨምሮ በመላው ዓለም የሚገኙ መጠለያ አልባ ሰዎችን በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ተናግረው ምዕመናኑም ከቅዱስነታቸው ጋር በጸሎት እንዲተባበሩ አደራ ብለዋል። ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በመጨረሻም ችግሩን ለማቃለል ጥረት በማድረግ የሚበላ ምግብ በማቅረብ ተስፋን በመስጠት ላይ የሚገኙ የጣሊያን ዳቦ አቅራቢ የንግድ ድርጅቶችን አመስግነዋል።

28 November 2022, 16:35