ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላምን ማምጣት እንደሚቻል ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“በሩስያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም መውረዱ አይቀርም” ያሉት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግጭት ቆሞ ሰላም እንዲወር ቅድስት መንበር የምትችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። ቅዱስነታቸው ከጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በሰሜን ጣሊያን በምትገኝ አስቲ ከተማ ስለሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እና በቅርቡ ስለሚያከብሩት የር. ሊ. ጵጵስናቸው አሥረኛ ዓመት በማስታወስ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጦርነት ከንቱነት
ዓርብ ኅዳር 9/2015 ዓ. ም. ታትሞ በወጣው ዕለታዊ የጣሊያን ጋዜጣ ላይ ሃሳባቸውን የገለጹት ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ፣ የሰው ልጅ ካለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች ትምህርት እንዳቀሰመ በመጥቀስ የጦርነትን ከንቱነት አጥብቀው ተናግረዋል። "ከእነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች በስተጀርባ ያሉት የኃይል ጥማት እና የጦር መሣሪያ ዝውውር ቁጣን እና ሐዘንን ያስከትላል" ብለው፣ በአንድ ዘመን ውስጥ ብቻ ሦስት የዓለም ጦርነት ቢካሄድም የጦርነትን አስከፊነት መረዳት አልቻልንም ብለዋል።
ለዘላቂ ሰላም ቅድስት መንበር የምታደርገው ጥረት
የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ እና የሰላም ድርድር ለማካሄድ ቫቲካን የምታደርገውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የተጠየቁት ቅዱስነታቸው፣ በጦርነት ለተጎዱት ዩክሬናውያን እና ለጦርነት እስረኞች ከምታደርገው ሰብዓዊ ዕርዳታ በተጨማሪ ቅድስት መንበር ሁኔታውን ያለማቋረጥ እንደምትከታተል እና ሁለቱን ወገኖች ለማስታረቅ እና ግጭቱን ለማስቆም የተቻለውን ሁሉ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆኗን ገልጸዋል። በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል ዘላቂ ሰላም እና እርቅ እንደሚወርድ ተስፋ እንዳላቸው የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ሁሉም ሰው ልቡን ለሰላም እንዲያዘጋጅ፣ በጦርነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ወታደራዊ ኃይልን ተጠቅመው ጥቃትን ከመፈጸም ይልቅ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ በማለት አፅንዖት ሰጥቷል።
“ሁላችንም ሰላም ወዳድ እና ፈላጊዎች መሆን ይገባል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ በጦር መሣሪያ ራስን ለማደራጀት ከማሰብ ይልቅ የውይይት ውጤት የሆነውን እውነተኛ ሰላምን ለማምጣት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ፣ የጦር መሣሪያ ጥላቻን እንጂ ሰላምን እንደማያስገኝ እና አመጽን ከመቀስቀሱ በላይ የበላይነት ጥማትን ለማርካት የሚጠቀሙት መሆኑን አስረድተዋል።
የብሔርተኝነት አደጋ
በዓለማችን ውስጥ የሚታዩ ክስተቶችን በመጥቀስ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የብሔረተኝነት እና የሕዝባዊነት ስሜት እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ይህም በግብዝነት ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ክፋት በመዝራት አደጋን እንደሚያስከትሉ አስጠንቅቀዋል።
የአስቲ ከተማ ጉብኝት
የቤተሰብ ሐረግ ወደሚገኝበት የሰሜን ጣሊያን ከተማ አስቲ ጉብኝት እንደሚያደርጉ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ ጉብኝታቸው የአጎታቸው ልጅ 90ኛ የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ ከዘመዶቻቸው ጋር በግል እንደሚገናኙ እና ከሀገረ ስብከቱ ምዕመናን ጋር የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል። አክለውም ከትውልድ ቤተሰባቸው ጋር ዛሬም ቢሆን ጠንካራ ግንኙነት እንዳላቸው ገልፀው፣ በአካባቢው የሚነገረውን ቋንቋ እና ግጥም ላስተማሩት አያታቸው ወ/ሮ ሮዛ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።
የቤተሰብ ሐረግ መጠበቅ
“ከቤተሰብ ሐረግ ጋር ያለን ግንኙነት ለባሕላዊ፣ ማኅበራዊ እንዲሁም ለስብዕናችን ዕድገት አስፈላጊ ነው" በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደተናገሩት ሁሉ፣ ወጣቶች በተቻለ መጠን ከአያቶቻቸው ጋር ሁል ጊዜ መነጋገር እንዳለባቸው በጥብቅ አሳስበው፣ ጨለማ በዋጠው እና እርግጠኝነት በሚጎድለው በዛሬው ዘመንም ወጣቶች ሕልማቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የረሃብ አሳፋሪነት
በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እና ሕፃናት በረሃብ እንደሚጠቁ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ ሕዝቦችን ከረሃብ ስቃይ ማውጣት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበው፣ ዕለታዊ ምግብ የማግኘት ዕድል ያላቸው በሙሉ ምግብን እንዳይባክኑ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ እና አሳፋሪውን ረሃብ ለማስወገድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተጠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
“እግዚአብሔር ባስቀመጠኝ ቦታ ደስተኛ ነኝ!”
የር. ሊ. ጵጵስናቸው አሥረኛ ዓመት ለማክበር መቃረባቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ ከሁሉ በላይ ለጥሪያቸው እግዚአብሔርን አመስግነው፣ በጥሪያቸው እና እግዚአብሔር ለአገልግሎት በላካቸው እና ባስቀመጣቸው ሥፍራ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። የማኅበራቸው መሥራች የሆነው የቅዱስ ኢግናጢዮስ መንፈሳዊነት እና ሕይወት፣ ክፉን ከደጉ ለመለየት የሚደረግ ዕለታዊ የሕሊና ምርመራ፣ ሕጻናትን፣ አረጋውያንን እና ድሆችን ለማዳመጥ የረዳቸው መሆኑን አስረድተዋል። በመጭው ታኅሳስ ወር 86ኛ የልደት በዓላቸውን እንደሚያከብሩ የገለጹት ቅዱስነታቸው፣ በዚህ ዕድሜ መረጋጋት፣ ታላቅ ሰላም፣ እውነተኛ ደስታ እና ገዳማዊነት እንደሚሰማቸው ተናግረው፣ በግል ማስታወሻ ጽሑፋቸው፣ በጸሎት፣ በመስዋዕተ ቅዳሴ እና በሚያገኛቸው ሰዎች አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚገናኙ አስረድተዋል።
ድሆችን መርሳት አያስፈልግም
ከአዲሷ የጣሊያን የመጀመሪያ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ወ/ሮ ጆርጂያ ሜሎኒ ጋር ኦፊሴላዊ ግንኙነት እንደሚያረጉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው፣ በጣሊያን የፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እንደማይገቡ እና አዲሱ መንግሥት በሕዝብ የተመረጠ እንደሆነ ገልጸው፣ የሁሉም አገራት መሪዎች ድሆችን መርሳት እንደሌለባቸው አደራ ብለዋል።