ፈልግ

በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚካሄድ ግጭት በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል የሚካሄድ ግጭት  

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለሥልጣናት የሰላም ውይይት እንዲያካሂዱ ጠየቁ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በእስራኤል እና ፍልስጤም መንግሥታት መካከል ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣው አመጽ እንዳሳሰባቸው ገለጹ። በዚህም የሁለቱም መንግሥታት መሪዎች በመካከላቸው ዘላቂ ሰላም እና የጋራ መተማመን ለመፍጠር የሚያስችል ውይይት እንዲያካሂዱ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 18/2015 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር በኅብረት ካቀረቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጠል ባደረገጉት ንግግር፣ በሁለቱ አገራት ማለትም በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ባለፉት ወራት የተቀሰቀሰው ጦርነት ያሳሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ረቡዕ በኢየሩሳሌም በተፈፀመው አሰቃቂ ጥቃት አንድ እስራኤላዊ ወጣት ለሞት ዳርጎት በርካቶችንም ያቆሰላቸው መሆኑን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ በተመሳሳይ ቀን በናቡስ በታጠቁት ሰዎች መካከል በተነሳው ግጭት የአንድ ፍልስጤማዊ ወጣት ሕይወት ማለፉን አስታውሰዋል።

ሁከት የወደፊት ሕይወትን እንደሚጎዳ የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የወጣቶችን ሕይወት እንደሚሰብርና የሰላም ተስፋ እንደሚያዳክም ጠቁመው፣ ለሞቱት ወጣቶች እና ለቤተሰቦቻቸው በተለይም ለእናቶቻቸው እንዲጸለይላቸው ጠይቀዋል።  

የእስራኤል እና የፍልስጤም ባለስልጣናት ለውይይት እና ለመተማመን ይበልጥ ትኩረትን በመስጠት በቅድስት ሀገር ውስጥ ሰላምን ለማስፈን እንደሚችሉ ተስፋ ያላቸው መሆኑን ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ ገልጸዋል።   

29 November 2022, 16:16