ፈልግ

ዓለም አቀፍ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት ዓለም አቀፍ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት  

ር. ሊ. ጳ. ፍራንችስኮስ፣ ዓለም አቀፍ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅትን የሚመሩ አባል ሰየሙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ በጎ አድራጎት ድርጅትን በጊዜያዊነት እንዲመሩ ክቡር ዶ/ር ፒዬር ፍራንችስኮ ፒኔሊን መሰየማቸውን ኅዳር 13/2015 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ድንጋጌ አስታውቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅዱስነታቸው ይፋ ያደረጉት ድንጋጌ በተጨማሪም ዶ/ር ማርያ አምፓሮ አሎንሶ ኤስኮባር እና የኢየሱሳውያን ማኅበር አባል ክቡር አባ ማኑኤል ሞሩጃኦን የድርጅቱን ሠራተኞች ግላዊ እና መንፈሳዊ ምክሮችን በመለገስ ዶ/ር ፒኔሊን እንዲያግዙ መሰየማቸውን አስታውቋል። ድንጋጌው በተጨማሪም የበጎ አድራጎት ድርጅቱን በፕሬዚደንትነት፣ በምክትል ፕሬዚደንትነት፣ በዋና ጸሐፊነት፣ በገንዘብ ያዥነት እና በመንፈሳዊ አገልግሎት አስተባባሪነት ሲሠሩ የቆዩት የሥራቸውን ጊዜያቸውን እንዲገባድዱ ጠይቋል። የበጎ አድራጎት ድርጅቱን በፕሬዚደንትነት ሲመሩ የቆዩት ብጹዕ ካርዲናል አንቶኒዮ ታግለ በሚኖራቸው የሥራ ድርሻ ለጊዜያዊ ፕሬዚደንቱ እገዛን እንደሚያደርጉ አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ ካቶሊካዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በቅዱስ ወንጌልና በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊ እና ማኅበራዊ አስተምህሮች በመታገዝ ለድሆች እና እጅግ ለተቸገሩት ሰዎች የሚደረገውን አገልግሎት በማስተባበር፣ ለሰብዓዊ ቀውሶች ተገቢ ምላሾችን በመስጠት እና በመላው ዓለም የበጎ አድራጎት ሥራን በማስፋፋት በቅርብ የሚያግዛቸው መሆኑን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በድንጋጌው ላይ ገልጸዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በማከልም ጊዜያዊ አስተዳዳሪን መሰየም ያስፈለገበት ምክንያት የበጎ አድራጎት ድርጅቱን ደንቦችን እና ሂደቶች በሚገባ ገምግሞ በሚቀጥለው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በሚደረግ ምርጫ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅቶችን ለማድረግ መሆኑን በድንጋጌው ላይ አብራርተዋል።

አዲሶቹን ተሿሚዎች

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅትን በጊዜያዊነ እንዲመሩ የተሰየሙት ዶ/ር ፒኔሊ፣ በመግለጫው ላይ እንደተገለጸው፣ እውቅ የድርጅት አማካሪ እና አስተዳዳሪ እንዲሁም ቴክኒካዊ የሥራ ስልትን በመጠቀም የበለጠ ሰብአዊነት ያለውን ተግባር የማከናወን ብቃት እንዳላቸው ታውቋል። የቅዱስ ኢግናጤዎስ መንፈሳዊነት የተከተሉ የበጎ ፈቃደኝነት ሥራዎቻቸው፣ የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኞች እንዲያገግሙ ማገዝ፣ በልማት ሥራዎች መተባበር፣ ለወንጌል ተልዕኮ ሥራዎች ድጋፍ መስጠትን እና በትምህርተ ክርስቶስ የማስተማር አገልግሎት ላይ መሳተፍን እንደሚያካትቱ ተመልክቷል። በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ለ33 ዓመታት በሥራ እንደቆዩ የሚነገርላቸው ዶ/ር ፒዬር ፍራንችስኮ ፒኔሊ፣ የጣሊያን መንግሥት የባህል እና የኪነጥበብ ድርጅቶች መልሶ ማቋቋሚያ መሥሪያ ቤት ዋና አስተዳዳሪ ሆነው ከማገልገል በተጨምማሪ፣ በልዩ ልዩ ሃይማኖዊ፣ ሕዝባዊ እና ባህላዊ ዘርፎች ሲሠሩ መቆየታቸው ታውቋል።  ዶ/ር ፒኔሊ እንደዚሁም በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለገብ ልማት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች መምሪያ ገምጋሚ ኮሚሽን አባል ሆነው ሰርተዋል።

ባሁኑ ጊዜ ዓለም አቀፍ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅቱን ከዶ/ር ፒኔሊ ጋር በረዳት አስተባባሪነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ማርያ አምፓሮ አሎንሶ ኤስኮባር ሲሆኑ፣ ከእርሳቸው በተጨማሪ የምጣኔ ሃብት አዋቂው ክብር አባ   ማኑኤል ሞሩጃኦ እንደሚገኙበት ተነግሯል። ዶ/ር አሎንሶ በስፔን ከኤክትራማዱራ ዩኒቨርሲቲ የተመረቁ ሲሆን፣ ከዓለም አቀፍ ካቶሊክ በጎ አድራጎት አባል ድርጅቶች ጋር ለ28 ዓመታት ሰርተዋል። ክቡር አባ ሞሩጃኦ በጎዋ እና ኬፕ ቨርዴ፣ እንዲሁም በትውልድ ሀገራቸው ፖርቱጋል በሐዋርያዊ እረኝነት እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ አገልግሎቶች ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን፣ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የምሕረት ሚስዮናዊ ሆነው ተሹመዋል። መግለጫው በተጨማሪም አዲሱ ስያሜው አባል ድርጅቶችን እንደማይመለከት አስታውቋል።

ድንጋጌው የግምገማ ሂደቱን የሚከተል ነው

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የሚገኝበት በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለገብ ልማት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ ይፋ ባደረገው መግለጫው፣ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ውሳኔ ይፋ የሆነው ገለልተኛ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት የሥራ ሂደት ላይ ግምገማ ካካሄደ በኋላ መሆኑን አስታውቆ፣ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች በሚገባ መመልከታቸውን እና የገንዘብ ማሰባሰብ ግቦችን በየጊዜው ማሳካት መቻሉንም አብራርቷል። የግምገማው ዓላማ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ ተግባር ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለእያንዳንዱ ሰው ከምትጠው ሰብዓዊ ክብር እና እሴቶች ጋር የሚጣጣም መሆኑን ለማረጋገጥ መሆኑን አስታውቋል።

በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለገብ ልማት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት ርዕሠ መስተዳድር ብፁዕ ካርዲናል ሚካኤል ቼርኒ በመግለጫው፣ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታገለግላቸው የብዙ ሰዎች ፍላጎት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን አስታውቀዋል። በመጀመሪያው የዮሐንስ መልዕክት ምዕ. 4:8 ላይ፥ “የማያፈቅር እግዚአብሔርን አያውቅም፥ እግዚአብሔር ፍቅር ነውና” የሚለውን በመጥቀስ፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቤተ ክርስቲያን ለበጎነት ተግባር የተጠራች መሆኗን እንድናስብ መጋበዛቸውን አስታውሰው፣“ልግስና የእግዚአብሔር አባታችን ፍቅር የሚገለጥበት፣ ለእያንዳንዱ ሰው በተለይም በስቃይ ውስጥ ለሚገኙት በሙሉ ልዩ ቦታን በልቡ ማዘጋጀቱን የሚገልጽ ነው” ማለታቸውን ጠቅሰዋል።  

ዓለም አቀፍ የካቶሊክ በጎ አድራጎት ድርጅት በዓለም ዙሪያ ከ200 በላይ አገራትና ክልሎች ውስጥ የሚሠሩ የ162 ካቶሊክ የዕርዳታ፣ የልማት እና የማኅበራዊ አገልግሎት ድርጅቶች ኮንፌዴሬሽን እንደሆነ ሲታወቅ፣ ዋና ጽ/ቤቱ በቅድስት መንበር የሰው ልጅ ሁለገብ ልማት ማስፋፊያ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ሥር እንደሚገኝ ታውቋል።

24 November 2022, 16:35