ፈልግ

ር. ሊ. ጳ ፍራንችስኮስ በሰላም ጥረት ወንድማማችነትን መገንባት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እሑድ ኅዳር 11/2015 ዓ. ም. ከአካባቢው ምዕመናን ጋር በከተማው ካቴድራል ውስጥ ካቀረቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ጸሎት በመቀጠል የእኩለ ቀኑን የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በኅብረት አቅርበዋል። ቅዱስነታቸው በዕለቱ ባከበሩት የክርስቶስ ንጉሥ በዓል ላይ የተገኙትን ጨምሮ ለሀገረ ስብከቱ ምዕመናን እና ለከተማው ነዋሪዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ከምዕመናኑ ለተደረገላቸው መልካም አቀባበል ምስጋናቸውን ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፣ አስቲ ከተማን እንዲጎበኙ ከሕዝብ መሪዎች እና የኃይማኖት አባቶች ለቀረበላቸው ግብዣ እና ላደረጉት ቅድመ ዝግጅቶችም ልባዊ ማስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ለሀገረ ስብከቱ ወጣቶች ያላቸውን ልዩ ፍቅር የገለጹት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በዓሉን በከፍተኛ ቁጥር በማክበር የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ምስጋናቸውን አቅርበውላቸዋል። ካለፈው ዓመት ጀምሮ በየአገራቱ የሚገኙ ካቶሊካዊ ቁምስናዎች ዓለም አቀፍ የወጣቶች ቀንን የሚያከብሩት በክርስቶስ ንጉሥ በዓል ዕለት መሆኑ ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣ መሪ ቃሉም በሉቃ. 1:39 ላይ “ማርያም በፍጥነት ተነስታ ሄደች” የሚል እና በሚቀጥለው ዓመት በፖቱጋል ዋና ከተማ ሊዝቦን ለሚከበረው ዓለም አቀፍ የወጣቶች ፌስቲቫል የተመረጠው መሪ ቃል መሆኑን አስታውሰው፣ የሀገረ ስብከቱ ወጣቶች በፌስቲቫሉ እንዲገኙ በማለት ግብዣቸውን በድጋሚ አቅርበውላቸዋል። እመቤታችን ማርያም ይህን ያደረገችው በወጣትነት ዕድሜዋ እንደነበር ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፣

የወጣትነት ምስጢር የሚገለጸው በሁለት ግሦች አማካይነት እንደሆነ፣ እነርሱም መነሳት እና መሄድ የሚሉ መሆናቸውን አስረድተዋል። “በፍጥነት ተነስታ ወደ ኤልሳቤጥ የሄደችውን ማርያምን ማስታወስ ያስደስተኛል” ያሉት ቅዱስነታቸው፣ እርሷ ዛሬም በዓለማችን ውስጥ ለሚታዩ ችግሮች ፈጣን መፍትሄ እንድታስገኝ ብዙ ጊዜ በጸሎት የሚጠይቋት መሆኑን ተናግረዋል። በፍጥነት ተነስቶ መሄድ ማለት በሃሳብ ብቻ ሕይወትን ማባከን ወይም ምቾትን መፈለግ አይደለም ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ነገር ግን በፍጥነት ተነስቶ መሄድ ማለት መንቀሳቀስ መጀመር፣ ፍራቻን በማስወገድ የተቸገረን ሰው ለመርዳት ቶሎ መነሳት ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።

ዛሬም ቢሆን በማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወት ንቁ እና ፈጣን ወጣቶች በእውነት ያስፈልጉናል ያሉት ቅዱስነታቸው፣ ለዘመኑ ቴክኖሎጂ ያልተገዙ ነገር ግን እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዓለምን የሚቀይሩ እና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመሰክሩ፣ ለሌሎች የሚጨነቁ፣ ከሌሎች ጋር የወንድማማችነት ማኅበረሰቦችን የሚገነቡ እና የሰላም ህልሞቻቸውን እውን የሚያደርጉ ወጣቶች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል።

“ዛሬ ሰላም ጠምቶናል!” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፣ በተለይም በጦርነት የተመሰቃቀለች ዩክሬንን በማሰብ በዓለማችን ውስጥ ብዙ ቦታዎች በጦርነት አደጋ የተጠቁ መሆኑን አስረድተው፣ “እጃችንን ዘርግተን ለሰላም መጸለያችንን እንቀጥል!” ብለዋል። ቅዱስነታቸው አክለውም፣ በፍልስጤም ጋዛ ውስጥ በሚገኝ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በደረሰው ከባድ የእሳት አደጋ የተጎዱ ቤተሰቦችን በጸሎት እንድናስታውሳቸው አደራ ብለዋል። በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡትን ነፍሳት እግዚአብሔር በምሕረቱ ወደ መንግስቱ እንዲያስገባቸው እና ለዓመታት ያህል ለግጭት ለተዳረጉት ወገኖቻችን መጽናናትን እንዲሰጣቸው ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ወደ ሰላም ንግሥት በምናቀርበው ጸሎት ለቤተሰቦቻችን፣ በሕመም ላይ ለሚገኙት እና እያንዳንዳችን በልባችን ውስጥ የያዝነውን ጭንቀት እና መልካም ሃሳብ ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በአደራ እናቀርባለን ብለዋል።

21 November 2022, 16:33